ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አደረጉ።

563

አዲስ አበባ: ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
አቶ ደመቀ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶችን በስፋት አብራርተዋል።
በገለጻቸውም በመንግሥት ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የተደረገውን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ እና ያልተገደብ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት የተደረጉ ጥረቶችን አስገንዝበዋል።
መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል።
መንግሥት የሦስተኛ ወገን ስምምነት በተመድ ጽሕፈት ቤት በመፈረም እንዲሁም ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የአደጋ ጊዜ እና የማገገሚያ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል ተግባራዊ እንዲደረግ መስማማቱን ተናግረዋል። ይኹን እንጂ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን መንግሥት የወሰዳቸውን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመተው ጦርነት መክፈቱን እና የሚደርሰውን እርዳታም ለጦርነት እያዋለው መኾኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ቡድን በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ የተጀመረውን የሰላም ጥረት በመግፋት ወደ ጦርነት መግባቱን ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይኽን ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝ እንዲኹም ቡድኑ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
መንግሥት በንጹሐን ዜጎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እና ጥፋት እንዳይደርስ ቅድሚያ በመስጠት አሁንም ለሰላም አማራጭ ዝግጁ ነው ያሉት አቶ ደመቀ የሀገሪቱን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መኾኑን እንደገለጹ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous article“የጀመርነው የልማት እና የእድገት ጉዞ በተከፈተብን ጦርነት አይደናቀፍም” ርእሰ መሥተዳር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)
Next articleሰበር ዜና