“የጀመርነው የልማት እና የእድገት ጉዞ በተከፈተብን ጦርነት አይደናቀፍም” ርእሰ መሥተዳር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

223

ባሕር ዳር : ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ ከፈርጅ አንድ ወደ ሪጂዮፖሊታን የደረጃ ሽግግር የእውቅና መርሃ ግብር በወልድያ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከተሞች ደረጃቸውን የሚመጥን የደረጃ ሽግግር ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ ወልድያ የፍቅር፣ የታሪክ፣ የመገናኛ እና የንግድ ማዕከል የሆነች ከተማ ናት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የደረጃ ሽግግሩ ውብ፣ ጽዱ፣ የምትለማ እና በእቅድ የምትመራ ከተማ እንድትሆን ያግዛታል ነው ያሉት፡፡
የደረጃ ሽግግሩ ካስፈለገበት ምክንያት አንዱ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ እንድትሆን ለማድረግ መሆኑን ያወሱት ዶክተር ይልቃል፤ በቀጣይም ለሪጂዮ ፖሊታንት የሚመጥን የከተማ አሥተዳደር አመራር ይሰየማል ብለዋል፡፡ አመራሩ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸው የከተማዋ ነዋሪዎች ከአመራሩ ጎን በመቆም ለእድገት እና ለውጥ አብሮ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው በወልድያ ከተማ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ከተጀመሩ ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን አለመጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዋና የልማት ፕሮጀክቶች በተለይም የከተማዋ የውበት መለያ የሆነው የአስፓልት ግንባታ በተያዘው የበጀት ዓመት ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡ ቀሪዎቹ የልማት ፕሮጀክቶችም በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በጋራ እየተነጋገሩ እንደሚሠሩም ርእሰ መሥተዳድሩ ቃል ገብተዋል፡፡
“የጀመርነው የልማት እና የእድገት ጉዞ በተከፈተብን ጦርነት አይደናቀፍም” ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል፤ አራት ዓይና ሆነን እና በአንድነት ቆመን ልማቱንም የተከፈተብን ጦርነትም በአሸናፊነት እንወጣለን ብለዋል፡፡ በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች አሁንም ድረስ በሽብር ቡድኑ ወረራ ስር ሆነው የሕይዎት እና የንብረት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ የገጠመንን ጦርነት በትግላችን፤ ድህነታችንን ደግሞ በልማት እናሸንፋለን ነው ያሉት፡፡
ህውሀት ጦርነቱን ራሱ ከፍቶ መልሶ ደግሞ ጦርነት ተከፈተብኝ በማለት ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ እንደለመደው ለማወናበድ እየሠራ መሆኑንም ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የአማራ ሕዝብ ግማሽ አካሉ በወረራ ተይዞ እንዳለ ሊያውቅ ይገባል፡፡ በተሳሳተ ትርክት አማራ ወራሪ ተደርጎ የሚቀርበው ውንጀላም ሊታረም ይገባል ብለዋል፡፡ ትክክለኛ መረጃ ለሚፈልግ ሁሉ በየደረጃው መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
የትኛውም ሀገር ነጻነቱን የሚያገኘው በራሱ ሕዝብ ጥረት፣ ትግል እና ጽናት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድር ይልቃል፤ አንድ ከሆንን፣ ከተደማመጥን፣ በጋራ ከቆምን እና ከተከባበርን የመጨረሻው አሸናፊዎች እኛ ነን ብለዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ሁለት ጊዜ ጥቃት እና ወረራ ተከፍቶብን በሕዝባችን፣ በመከላከያ ኃይላችን እና በክልላችን የጸጥታ መዋቅር እዳሸነፍን ሁሉ አሁን የተከፈተብንን ጦርነትም በተባበረ ክንድ እናሸንፋለን ብለዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ ጦርነቱ በተከፈተበት አካባቢዎች ያሉ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደርጉትን የደጀንነት ድጋፍ እንደተጀመሩ ገልጸው፤ ተጠንክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ድጋፉ የሞራል እና የስንቅ አቅርቦት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ መረጃን ከተረጋገጠ የመረጃ ምንጭ ብቻ በመውሰድ የጠላት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዳይሆንም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous articleʺ የተባበሩ ክንዶች ያስከብራሉ፣ አንድ የኾኑ ጀግኖች ድል ይቀዳጃሉ”
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አደረጉ።