
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቀጫጭን ድሮች ተባብረው አንበሳ ያስራሉ፣ ትንንሽ ጡቦች በአንድነት ያማረ ቤተመንግሥት ይገነባሉ፣ የተደጋገፉ ማዕበሉን ያልፋሉ፣ ወንዙን ይሻገራሉ። ከአንድነት ድል አለ፣ ከአንድነት ተስፋ አለ፣ ከአንድነት መከበር አለ፣ ከአንድነት መሻገር አለ።
በአንድነት የቆሙት የገፋቸውን ሁሉ ጥለዋል። በአንድነት የተጓዙ ጨለማውን ሁሉ አልፈዋል፣ በአንድነት የተነሱት ወሰናቸውን አስከብረዋል፣ ድንበራቸውን አስጠብቀዋል። ከታሪክ ላይ ታሪክ እየደራረቡ ኖረዋል።
የተባበሩት በድል ኖረዋል፣ አንድ የኾኑት ጠላትን አሳፍረዋል። የተባበሩ ክንዶች በዓለም አደባባይ ተከብረዋል፣ በጦር ሜዳ ድሉን ወስደዋል፣ ፍትሕና እኩልነትን ሰጥተዋል። ያልተባበሩት ተንቀዋል፣ አንድ ያልኾኑት ተደፍረዋል፣ በሀገራቸው ባይታዋር ኾነዋል፣ ያልተባበሩ ሕዝቦች በጠላት ተንገላትተዋል። ማንነታቸውን አጥፍተው የሰው ማንነት ተቀብለዋል። በማይመስላቸው ባሕልና እሴት ባዝነዋል።
ዓለም አንድ የኾኑ ሕዝቦችን ታከብራለች፣ ዓለም አንድ ለኾኑ ሕዝቦች ታሸረግዳለች፣ ዓለም ለጉልበታሞች እጅ ትነሳለች፣ ዓለም አንድ የኾኑ ሕዝቦችን ትፈራለች። አንድ የኾኑት በድል ኖረዋል፣ በአሸናፊነት ዘመናትን ተሻግረዋል። የተበታተኑት እጅ ሰጥተዋል። ባለሀገሮች ሀገር አልባ ኾነዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነታቸው ተከብረው ኖረዋል፣ በጀግንነታቸው ጠላትን አንበርክከዋል፣ ሠንደቃቸውን በድል አድራጎት አውለብልበዋል።
በእርጅና ቅሌት፣ በመሞቻ ጊዜ ሀጥያት፣ በጉልበት ሲመቱ በምላስ መጎልበት መታወቂያቸው ነው፡፡ ዝም ሲሏቸው ይፎክራሉ፣ ሲገጥሟቸው ዓለምን ይማጸናሉ፣ የሰላም መንገድ አሳዩን ይላሉ፡፡ ለፈራጅ ግራ ያጋባሉ፣ በዋሻ ውስጥ እየዋሉ ድል አደረግን ይላሉ፤ ስለ ሕዝብ የተነሳ እንጂ በሕዝብ ላይ የተነሳ አላሸነፈም፣ ከሚሻው ስኬት ላይ አልደረሰም፡፡ ትህነግ በሕዝብ ላይ ተነስቷልና ድል ከእርሱ ጋር አይደለችም።
ለሀገሩ የሞተን፣ ለሀገሩ የቆሰለን፣ ለሀገሩ የተንከራተተን ሕዝብ አምርረው ይጠሉታል፣ ጠልተው ያጣሉታል፣ በሀገሩ ባይተዋር ያደርጉታል፣ በሕግ አርቅቀው ከርስቱ አፈናቀሉት፣ በሕግ አርቅቀው ዘሩን ከዘር መርጠው አሰቃዩት፣ በሰው መካከል የተከበበ ብቸኛ አደረጉት፡፡
እንደ ተራራ የገዘፈውን፣ እንደ ውቅያኖስ የሰፋውን፣ እንደ ፀሐይ የሚያበራውን ታሪኩን ሊያጠፉት፣ ባልነበረበት እና ባልዋለበት ሊያውሉት ለዓመታት ኳተኑ፡፡ የማይመስለውን ስም ሰጡት፡፡ ኢትዮጵያን ሊያስጠሉት፣ ከታላቁ ከፍታ ከኢትዮጵያዊነት ሊያወርዱት መከራውን አበዙበት፣ ከስቃይ ላይ ስቃይ ደራረቡበት፡፡
ዳሩ ኢትዮጵያን እየሞተ ይወዳታል፣ እየደማ ያጸናታል፣ እየቆሰለ ያክማታል፣ በዱር በገደል እየተንከራተተ ይጠብቃታል፣ ኢትዮጵያን ሲደላው የሚለብሳት፣ ሲከፋው የሚያወልቃት ካባው አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ በመከራም በደስታም የሚጠብቃት፣ ከሕይወቱ አስበልጦ የሚወድዳት፣ ሞትን የሚንቅላት ናት እንጂ፡፡ መከራውን ሲያበዙበት የበለጠ ይወዳታል፣ ስቃዩን ሲያበዙበት የበለጠ ያፈቅራታል፡፡ በስቃዩ ውስጥ ፍቅሩ ሳይቀንስ ያስባታል።
ስለ እርሷ ሞትን ይንቃል፣ ስለ እርሷ ረሃብና ጥሙን ይረሳል፡፡ እነርሱ የሚጠሉት የአማራ ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ በሰሜን ንፍቅ ሞቷል፣ በደቡብ ንፍቅ ተሰውቷል፣ በምስራቅ ራሱን ሰጥቷል፣ በሰሜን ለዓመታት ዋጋ ከፍሏል፣ በኢትዮጵያ ላይ የተነሱትን ሁሉ ጥሏቸዋል፣ በኢትዮጵያ ላይ የመጡበትን ሁሉ ከወንዝ ማዶ አስቀርቷቸዋል፣ ጎዳናዎቹ ለጠላት አይመቹም፣ ለሰላቶ አያረማምዱም፡፡
የሚወዳትን የሀገሩን ሠንደቅ ሊያስጥሉት አማራቸው፣ እርሱ ግን በመከራውም በደስታውም አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋን ሠንደቅ ካላስቀደመ አይራመድም፣ እርሷን አስቀድሞ ይገሰግሳል፣ እርሷን አስቀድሞ ጠላቱን ይመልሳል፡፡ በሀዘኑም በደስታው ጊዜ ሠንደቁን ከፍ ያደርጋታል።
አሸባሪው ትህነግ በሚጠላውና በሚፈራው ሕዝብ ላይ ለዓመታት የዘለቀ በደል አድርሷል፣ በየጥጋጥጉ በግፍ የንጹሐንን ደም አፍስሷል፣ በጨለማ ቤት ውስጥ ዘግቷል፣ ርስት ቀምቶ ኖሯል፣ ሀብትና ንብረት ዘርፏል፣ አውድሟል፡፡ ወደ በረሃ ሲወርድ በጥላቻ ነበር የወረደው፣ በቤተ መንግሥት ሳለም ይጠለዋል፣ ከቤተ መንግሥት ተባርሮም ይጠለዋል፡፡ ለውደቀቶቹ ምክንያት ሁሉ ይሄን ሕዝብ ያነሳል፡፡
የወደመው ጨርሶ ሳይተካ፣ የተዘረፈው ሳይመለስ፣ በግፍ የሞቱት ሀዘን ሳይወጣ ትህነግ ሌላ ጠብ ጭሯል። ትህነግ ጦርነቱን ከበረደበት ቀስቅሶታል። ተስፋ የተደረገበትን ሰላማዊ ውይይት አክሽፈውታል። እየተገፋ ለሠላም እጁን የዘረጋውን ሕዝብ ዳግም ለጦርነት ጋብዞታል።
የተዘናጋ ሕዝብ ካገኘ መውረር፣ ለመዝረፍና ለማውደም አስቧል። ሀሳቡን ለማሳካትም ጦርነት ጀምሯል። አትንኩኝ ሲሉት ነክተውታል፣ ሰላም ይሻላል ሲል ጦርነት ይሻለናል ብለውታል። የትግራይ እናቶች ችግርን ሽሽት ወደ አማራ ክልል በየቀኑ ይመጣሉ። የአማራ ሕዝብ ከትግራይ የወጡት፣ ዘርፈውናል፣ ከድተውናል፣ ልጆቻችን ገድለዋል፣ ንብረታችን አውድመዋል አላለም።
አቅፎ ተቀበላቸው። መጠለያ ሠርቶ አስጠለላቸው፣ የተራቡትን አጎረሳቸው፣ የተጠሙትን አጠጣቸው፣ የታረዙትን አለበሳቸው። ስለ ጤንነታቸው ተጨነቀላቸው። ጠላትና ወዳጁን ጠንቅቆ ያውቃልና ደገኛው ሕዝብ አይጥለንም፣ አያስርበንም፣ አያስጠማንም ብለው የመጡትን ተቀበላቸው። በፍቅር የመጣውን በፍቅር፣ በጦር የመጣውን በጦር መቀበል ያውቅበታል።
ታዲያ የታረዘ የሚያለብሰውን፣ የታመመ የሚጠይቀውን፣ የተቸገረን የሚደግፈውን፣ መድረሻ ያጣውን የሚያስጠልለውን ሕዝብ እርሻ በሚያርስበት፣ ማሳውን በዘር በሚሸፍንበት ወቅት ጦርነት ጎሰሙበት።
ጀግና ሕዝብ ጀግኖችን ይፈጥራል፣ ለሀገር ከሚዋደቁት ጋር ይተባበራል። በአንድነት ይቆማል። በአንድነት ጠላቱን ይጥላል። የተባበሩ ክንዶች ያስከብራሉ፣ ይከበራሉ፣ አንድ የኾኑ ጀግኖች ድል ይቀዳጃሉ። አበው በራስ ትጥቅና በራስ ስንቅ ተጉዘው ሀገር አስከብረዋል። ያልተደፈረች፣ ትውልድን ያኮራች ሀገር አቆይተዋል።
ዛሬም በአንድነት ለሀገርህ ቁም፣ አንድ ስትኾን ያከብሩሃል፣ ደጅ ይጠኑሃል፣ እጅ ይነሱልሃል። አንድነትክን እና ጀግንነትክን ደጋግመህ አሳያቸው፣ ” ሞኝ ማለት የጠላቱን አጀንዳ የራሱ መስሎት የሚያስፈፅም ነው” እንዳሉ አበው በክብርህና በሕይወትህ የሚመጡትን አትቀበላቸው።
ችግር የማይፈታው አንድነት ካለህ ተከብረህ ትኖራለህ። በውስጥህ ከተከፋፈልክ ለመሸነፍ ዝግጁ ነህ። ጠላት ቢዝትም፣ ነፍጥ ቢያነሳም በአንድነት ከፀናህ ድል ከአንተው ጋር ናት። እውነት ፣ መገፋት፣ ጀግንነት እና አይደፈሬነት ከአንተ ጋር እንደኾኑ አትርሳ። እውነት አሻጋሪና አሸናፊ ናት።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼