የመከላከያ ሠራዊትን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ባልተረጋገጡ፣ ባልተገቡ መረጃዎችና አሉባልታዎች የመዘገብ ወይም የማራገብ አሉታዊ ሙከራዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ መከላከያ ሚኒስቴር አሳሰበ።

336

ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሠራዊትን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ባልተረጋገጡ፣ ባልተገቡ መረጃዎችና አሉባልታዎች የመዘገብ ወይም የማራገብ አሉታዊ ሙከራዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ
አሳስቧል።
ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
የሕዝባችን ድጋፍ እና ተሳትፎ ጠንካራ መኾን፤ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ወሳኝ መኾኑን በፅናት ያምናል፡፡ በሕዝባችን እና በሠራዊታችን የተገነባው መተማመንና መደጋገፍ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ በመኾኑ፣ ፈተናዎች በጋራ እያለፍን የሀገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት አስከብረን ቆይተናል፡፡ ወደፊትም ጠላቶቻችን የሚደግሱልንን ሴራ እና ወጥመድ አውቀን በማክሸፍ ለዕኩይ ዓላማቸው የማንበገር መኾናችንን በተግባር እያሳየን እንቀጥላለን፡፡ ይኽ የጋራ ታሪካችንና ተስፋችን አይቀሬ ቢኾንም ለድላችን የምንከፍለው ዋጋ እንዲቀንስ ግን ጠንካራ ሥራ ያስፈልገናል፡፡
ጠላቶቻችን ከሰሞኑ ግልፅ አደጋ ለመፍጠር አስበው በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ሰርጎ የገባው አልሸባብ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኃይሉ መደምሰሱ ይታወቃል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም አሸባሪው የህወሓት ቡድን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል፡፡ በተለይ የአሸባሪው ህወሓት አፈ ቀላጤዎች ሰሞነኛ ሰበካቸው የሠራዊታችን ስም ማጥፋት ሥራዬ ብለው ተያይዘውተዋል፡፡ ተቀባይነት የሌላቸውን ሰበቦች በመደርደር መከላከያ ሠራዊታችንን በመወንጀል ዘመቻ መሰማራታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እየለፈፉ ያሉት፤ “…የሰላም ድርድሩ ቴክኒካል ፈርሷል…፣ …መከላከያ ኃይሉን እያስጠጋ ነው…፣ …መከላከያ በከባድ መሳሪያ እየደበደበን ነው…፣ …ከላይ እስከታች የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ እየተፈፀመ ያለ ጥቃት ነው…” ወዘተ በማለት የቅድመ ግጭት ጩኸታቸውን በስሙልኝ ፕሮፖጋንዳቸው እያስተጋቡት ይገኛሉ፡፡
የሀገራችን ሚዲያዎች፣ የጠላትን ሴራ እና አጀንዳ በውል ተገንዝበው የሚሞግቱ የመኖራቸውን ያህል፣ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘገባዎችና መረጃዎች ይህንኑ አፍራሽ ውንጀላ ባልተገባም መልኩ እየተቀባበሉት መኾኑን አስተውለናል፡፡
ያለበቂ መረጃ የጠላትን እንቅስቃሴ መዘገብ በራሱ የሕዝባችንን የዕለት ከዕለት ኑሮ ያውካል። ጠላት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ ፤ የወገን ሠራዊት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ የሚለው ወሬ በፍፁም ዜና እና የዜና ትንታኔ ሊኾን አይችልም። ጦርነቱን እንዲዘግቡ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውጭ በሀገር ኅልውና ላይ የተቃጣን ጦርነት የሚያክል ነገር በማኅበራዊ ሚዲያ ገቢ ማስገኛነት ተቆጥሮ ምንም የተረጋገጠ መረጃ ሳይኖር ወሬውን ማናፈስ የሕዝባችንን መረጋጋት የሚነሳ ጉዳይ ነው ፤ የፀጥታ ኀይሎችን ተግባርንም ያውካል።
የሠራዊታችን ወቅታዊ ሁኔታ እና እንቅስቃሴ አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ ለሕዝባችን ይፋ ስናደርግ እንደነበረው ወደፊትም በዚሁ አግባብ የሚከናወን ተግባር ኾኖ ሳለ፤ ሠራዊታችን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት በፅናትና በጥንቃቄ፤ ተዘጋጅቶ በተጠንቀቅ በቆመበት በአኹኑ ወቅት ጠላት ባሰናዳው ፕሮፖጋንዳ ወጥመድ የተጠለፉ አሉታዊ መረጃዎች በማስተጋባት እና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የሠራዊታችንን እንቅስቃሴ በማሰራጨት ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት እንዳሉም አይተናል፡፡ ይኽ ድርጊት በሠራዊታችን የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ምንም አወንታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው አይችልም።
በመኾኑም ይህን አሉታዊ ተግባር በማወቅም ኾነ ባለማወቅም የተዛባ፣ ተገቢና የማይመለከታቸውን ዘገባ የሚዘግቡ የማኅበራዊ ሚዲያ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
ይህንን ተግባር በግዴለሽነት ወይም በማንአለብኝነት የሚቀጥሉና የማይታረሙ ካሉ መከላከያ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ከመኾኑም በላይ የሠራዊቱን ምስጢር በመንዛት፣ የጠላትን አጀንዳ በማራገብ የሀገር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉትን እንደ አስፈላጊነቱ የወንጀል ክስ በመመስረት ተጠያቂ ለማድረግ እንደምንገደድ በጥብቅ እናሳውቃለን፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous article❝ላልይበላን የቱሪዝም ማዕከል እና የዓለም ሕዝብ መዳረሻ ለማድረግ እንሰራለን❞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
Next articleለአሸባሪው ህወሃት የጦር መሳሪያ ጭኖ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ጥሶ የገባ አውሮፕላን በአየር ኃይል መመታቱ ተገለጸ።