
ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸንድዬ በዓል በላልይበላ ከተማ “አሸንድዬ የማንነታችን እና የአንድነታችን መስተጋብር ነው” በሚል መሪ መልዕክት በድምቀት ተከብሯል።
ላልይበላ አኹንም ድረስ ዓለም የሚደመምበት እና ኢትዮጵያ ይበልጥ የምትታወቅበት ውብ የኪነ ጥበብ ማእከል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ታሪክን ማንሳት እና ማውሳት ብቻውን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህንን ድንቅ የታሪክ፣ የባሕል፣ የሃይማኖት እና የቀደምትነት ማእከል ይበልጥ አልምቶ ሕዝብንም ሀገርንም ተጠቃሚ ማድረግ በዚህ ትውልድ ትከሻ ላይ ያረፈ ኅላፊነት መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አበርክቶዋ ብዙ ነው ያሉት አቶ ደመቀ በትብብር እና በመቀራረብ ጸጋዎችን አልምቶ የገቢ ምንጭ ማድረግ ደግሞ መንግሥት በዘርፉ ላይ ያስቀመጣቸው የሥራ ኀላፊዎች ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው ብለዋል፡፡ ዛሬ የአሸንድዬ በዓልን በላልይበላ ለማክበር የተገኙ የፌደራል እና የክልል የቱሪዝም እና የባሕል ተቋማት ኅላፊዎች ተልዕኮዎቻቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ኹለት ዓመታት በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት አካባቢው መጎዳቱን የገለጹት አቶ ደመቀ ከጦርነቱ ማግስት ልደትን በላልይበላ ማክበራችን ኢትዮጵያዊያን ያለንን የሥነ ልቦና ጥንካሬ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡ ልደትን ትናንት እና አሸንድዬን ዛሬ በአደባባይ ወጥተን እንድናከብር የሕይዎት እና የአካል መስዋእትነት ለከፈሉ ጀግኖች፤ ለሃይማኖት አባቶች ክብር እና ፍቅር አለን ነው ያሉት፡፡
በጦርነት ተወልደው በጦርነት ጥቅማቸውን ለማስከበር ትናንት ኢትዮጵያ ላይ ክህደት የፈጸሙ ኅይሎች ዛሬም ዳግም ጦርነት በመጎሰም ላይ ናቸው ያሉት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ የሰላም አማራጮችን እስከ መጨረሻው ትጠቀማለች ብለዋል፡፡ ነገር ግን ተገቢ ላልኾነ የበላይነት እና ለኢ-ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የምንደራደርበት ትዕግስት የለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጦርነት ይበቃታል፤ ኢትዮጵያዊያን ጦርነት ይበቃቸዋል ያሉት አቶ ደመቀ የሕዝብን ሕይዎት የሚለውጡ እና የሀገርን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ብዙ ተስፋዎች ስላሉን ተረጋግተን የምንሠራበት እድል እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡
የቅዱሳን እና የንጉሣን መናገሻ የኾነችውን ላልይበላ ከተሰጡን ጸጋዎች መካከል አንዷ ናት ያሉት አቶ ደመቀ ❝ላልይበላን የቱሪዝም ማዕከል እና የዓለም ሕዝብ መዳረሻ ለማድረግ እንሰራለን❞ ብለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J