የማንነት መገለጫ የኾኑ በዓላትን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባ ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ተናገሩ፡፡

141

ነሐሤ 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸንድዬ በዓል በላልይበላ ከተማ አስተዳደር እየተከበረ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በበዓሉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ድንቅና ብርቅ የኾኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩባት መኾኗን ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላትን በአግባቡ በመንከባከብ ማንነትን በሚገልጽ መልኩ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያን ጸጋዎች በአግባቡ ባለመጠቀማችን አሁንም በድህነት እንኖራለን ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ድኅነት ክፉ በሽታ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ድኅነትን ለማስወገድ የሁሉንም ትግልና ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ድህነትን ለማስወገድ ልዩ ልዩ ፖሊሰዎችን ነድፎ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ አንደኛው ድህነትን የመታገያ መንገድም ቱሪዝምን ማስፋፋት እንደኾነ ነው ያነሱት፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የአሸባሪው ትህነግ ወረራ በዓላት እንዳይከበሩ እንቅፋት ፈጥረው መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ ታላቅ ሥነ ልቦና ያለው፣ አሸናፊነትን የተላበሰ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የደረሰበትን ውድመት በትግልና በጥረት እተከዋለሁ የሚል ታላቅ ሕዝብ ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በትጋት ከሠሩ ድህነትን እንሻገረዋለን ነው ያሉት፡፡
ልማትን ለማፋጠን እና ድህነትን ለመቅረፍ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ ያለ ሰላም ልማት እንደማይኖርም አስገንዝበዋል፡፡ ያለ ሰላም በዓላትን ማክበርና ውብ የኾነውን ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ሥርዓትን ለዓለም ማሳየት እንደማይቻል ነው ያስገነዘቡት፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ ሰላምን የማስጠበቅ ኀላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሰላምን በማረጋገጥ ድህነትን ለመቅረፍ በትጋት መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡
ላስታና አካባቢው በአሸባሪው ትህነግ ወረራ ምክንያት በመብራት እጦት እየተሰቃዬ ያለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የሚያዋጣን በአንድነት መቆም ነውም ብለዋል፡፡ በአንድነት በመቆማችን ወረራውን ቀልብሰን ሕልውናችንን አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡ በአንድነት ከቆምን የሚደፍረን ውጫዊም ኾነ ውስጣዊ ኀይል የለም ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡ ከመጣም እንደተለመደው አከርካሪውን ሰብረን መመለስ እንችላለን ነው ያሉት፡፡ ለአንድነት ትልቅ ዋጋና ክብር በመስጠት መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡
መለያየት የግጭት መንገድ ነው፣ ግጭት የድህነት መንገድ ነው፣ ግጭት ባሕላችንና ሃይማኖታችንን በድምቀት እንዳናከብር የሚያደርግ በጥላቻ የተመሠረተ አክሳሪ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ ከግጭት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡
ከግጭት ሞት፣ ስደትና ንብረት ውድመት ብቻ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ግጭትን መጸየፍ አለብን ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ተከባብረን እና ተደማምጠን ከሠራን የማንሻገረው ፈተና የለም ብለዋል፡፡ የአሸንድዬ በዓል ማደግና መስፋት እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡
በዓሉን በዓለም ማስተዋወቅ ይገባል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ዓለም በዓሉን እንዲያውቅ እናደርገዋለንም ነው ያሉት፡፡ በዓሉን ሃብት እንፈጥርበታለን፣ ልማት እናፋጥንበታልንም ብለዋል፡፡ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ከችግር መውጣት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በዓሉ ሕዝቡ በተስፋ እንዲኖር የሚያደርግ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሕልና እሴትን በመጠበቅ በኩል እያደረገችው ላለው ተግባር ምሥጋና ይገባታልም ነው ያሉት፡፡ በዓሉን ሌሎች እንዲመጡና እንዲጎበኙት ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ በዓሉ የኢትዮጵያን መጪ ዘመን ብሩህ እንደኾነ ተስፋ የሚሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፉት ሦሰት ዓመታት ከ3 ቢሊዮን 478 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 650 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ገለጸ፡፡
Next article❝ላልይበላን የቱሪዝም ማዕከል እና የዓለም ሕዝብ መዳረሻ ለማድረግ እንሰራለን❞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን