አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፉት ሦሰት ዓመታት ከ3 ቢሊዮን 478 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 650 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ገለጸ፡፡

278

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/ 2014 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የአካባቢን ችግር በራስ አቅም በመፍታት፣ አካባቢን ለማልማት ባለፉት ሦስት አስር ዓመታት አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማስተባበር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዓለማየሁ ሞገስ እንዳሉት ልማት ማኅበሩ ባለፉት 21 ዓመታት ሁለት ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ልማት ማኅበሩ ከ2012 እስከ 2014 ባሉት ዓመታት ደግሞ የለውጥ ዕቅድ አዘጋጅቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡
አልማ በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ሕዝብን በማስተባበር ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ እንዳሉት አልማ ባለፉት ሦስት ዓመታት፡-
✍️ ከ3 ቢሊዮን 478 ሚሊዮን በላይ ብር ወጭ 650 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን አከናውኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ 418 ፕሮጀክቶች ከሞዴል ቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ሥራ ተሠርቷል፡፡
✍️ ከ1 ቢሊዮን 373 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ 389 መማሪያ ብሎኮችና 1 ሺህ 594 የመማሪያ ክፍሎች ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
✍️ በሦስት ዓመት የእቅድ ዘመን ተጀምረው በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን እስከ ጥር/2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል፡፡
✍️ ልማት ማኅበሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን የለውጥ እቅዱ ከጀመረበት ከ2012 ዓ.ም በፊት በነበሩት 20 ዓመታት ካንቀሳቀሰው ገንዘብ ብልጫ እንዳለው ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡
✍️ በሦስት ዓመት የልማት እንቅስቃሴ ግንባታቸው ከተጠናቀቀው ፕሮጀክቶች ውስጥ 64 በመቶ የሚኾኑት ትምህርት ሲኾኑ አጠቃላይ ከልማት ማኅበሩ ሃብት ደግሞ 84 በመቶ የሚኾነው ለትምህርት ውሏል፡፡
ልማት ማኅበሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት እነዚህን ልማት ሥራዎች ቢያከናውንም በክልሉና በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው የኮሮና ወረርሽኝ፣ አንበጣ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ጦርነት ምክንያት ከአባላቱ ገቢ መሰብሰብ ባለመቻሉ እቅዱን ማሳካት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ እንዳሉት የክልሉን ሕዝብ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት አልማ ለቀጣይ ሦስት ዓመት አዲስ የለውጥ ዕቅድ አዘጋጅቷል።
የለውጥ ዕቅዱ “ሕዝባዊ ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት አልማ ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚመራ ነው። በእነዚህ ሦስት ዓመታት 8 ቢሊዮን ብር ከአባላት፣ ከረጅ ድርጅቶችና ከገቢ ማስገኛ ተቋማት በማሰባሰብ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ታስቧል፡፡ በኹሉም ትምህርት ቤቶች ቅድመ መደበኛ ትምሕርትና በክልሉ በሚገኙ ኹሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ ጂጂታል ቤተመጽሐፍት ማሟላት ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በቀጣይ ሦስት ዓመት ልማት ማኅበሩ የጀመረውን አካባቢን በራስ አቅም የማልማትና የአካባቢውን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት በሚደረገው ጥረት መላው የማኅበሩ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉ አቶ ዓለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ በቁሳቁስ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት ፣ ችግሮችን በመለየት ጭምር እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 84 በመቶ የሚኾኑት ከደረጃ በታች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የትምሕርት ቤቶች ችግር ለማሻሻል አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፉት ዓመታት ግብዓት በማሟላት፣ ግንባታዎችን በማከናወን የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡
ልማት ማኅበሩ በቀጣይ የትምህርት ቤቶችን የገጽታ ችግር ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ኹሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleበአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት የደረሰበት የሰቆጣ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት በተሻለ የጥራት ደረጃ መልሶ ሊገነባ ነው።
Next articleየማንነት መገለጫ የኾኑ በዓላትን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባ ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ተናገሩ፡፡