
ነሐሴ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶች የኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋ ለማበላሸት የሚሠሩ ኀይሎችን ሴራ በመታገልና አብሮነትን በማጽናት በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ ወጣቶች ከመልካም አሥተዳደር፣ ሥራ አጥነት፣ የሰላምና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ወጣቶቹ ለውጡን ተከትሎ የተገነቡ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም የኢትዮጵያ መጻኢ ጉዞ ብሩህ መኾኑን ተመልክተናል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወጣቶቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ብታልፍም ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የገበታ ለሀገር፣ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶችና መንገድን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
እነዚህ የልማት ሥራዎች ለወጣቶች ተስፋ የሰነቁ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህ አኳያ ወጣቶች አብሮነታቸውን ጠብቀው በተጀመሩ የልማትና የሰላም ሥራዎች ንቁ ተሳታፊ መኾን አለባቸው ነው ያሉት።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ይሠራል ብለዋል።
መንግሥት የመልካም አሥተዳደር ችግር መሠረት የኾነውን ሌብነት ለመከላከል በተደራጀ መልኩ ጠንካራ ሥራዎችን እንደሚያከናውንም ነው ያረጋገጡት።
የበጎ ፈቃድ አገልሎትን ከማጠናከር አኳያ ወጣቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ያላቸውን የእረፍት ጊዜ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተሠማርተው በፈቃደኝነት ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት ኹኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል።
ወጣቶች የነገ መጻዒ እድሎቻቸውን ለማበላሸት የሚሠሩ ኀይሎችን ሴራ በጋራ በመታገል የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባቱ ሂደት ላይ ንቁ ተሳታፊ ሊኾኑ እንደሚገባም ነው ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J