እንኳን ለበዓለ ደብረ ታቦር አደረሳችሁ!! “ዶሮ ከጮኽ የለም ሌሊት ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት”

173

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጨፍጋጋማ ወራት አልፈዋል፤ ብርሃን ሊገለጥ ቀናት ከፊታችን ቀርተዋል የሚል መልእክት አለው፡፡ የእረኞቹ የጅራፍ ጩኽት የተለያየ ሊገናኝ፣ የተነፋፈቀ ሊተቃቀፍ፣ የተራራቀ ሊቀራረብ እና የተጠፋፋ ሊጠያየቅ ቀኑ ቀርቧል የሚል ይመስላል፡፡ የቡሄ ጭፈራ፣ የአዕዋፍት ዝማሬ እና የጅረት ድምጽ አዲስ ዓመት ስለመቃረቡ ምስክር ይሆናሉ፡፡ በተለይም ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር “ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠበት ቦታ ነውና” ብርሃናማው ዘመን ስለመምጣቱ አብሳሪ ነው፡፡
ምድር አረንጓዴ ለብሳ፣ ሰማይ ጠርቶ፣ ጥጆች እየቦረቁ፣ እረኞች እየደለቁ፣ የልጅአገረዶች ኅብረ ዝማሬ እየተሰማ፣ የእናቶች ስጦታ እየተሰበሰበ፣ የአባቶች ምርቃን እየተዥጎደጎደ፣ የካህናት ቅዳሴ፣ የዲያቆናት ውዳሴ እና የልጆች ምስጋና እየተስተጋባ የአዲስ ዓመት መንፈስ እና ተስፋ በምድሪቱ ሁሉ ይናኛል፡፡
ልጆች ተሰባስበው
“መጣና መጣና ደጅ ልንጠና፤
መጣና በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ…”
በማለት ክራሞታቸውን ይጠይቃሉ፡፡
በበጋው ወቅት አስቀድሞ “እህልና መሬትን፤ ሰኔና ግንቦትን አስማማልን” ብሎ የለመነ ሕዝብ ከሰኔ አጋማሽ እስከ ነሐሴ እኩሌታ ጆሮውን ቢቆርጡት አይሰማም፡፡ ውሎው እርሻ ለእርሻ የቅርብ ጓደኛው ማረሻ ነው፡፡ በወንዝ ሙላት፣ በጭቃው ብርታት፣ በእርሻ ሥራ፣ በጉልጓሎው ውሎ፣ በአረም እና በጭጋጉ ተለያይተው እና ተነፋፍቀው የከረሙት ሁሉ ከተራራ ላይ በሚገረፍ የእረኞች የጅራፍ ጩኽት እንዴት ከረማችሁ ይባባላሉ፡፡ አዲስ ዘመን እና የብርሃን ወቅት ሊመጣ ቀርቧልና እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
ጨፍጋጋማው ወቅት ሲለቅ ቡቃያውን እያዩ፤ ከእሸቱ እየተገናኙ የጎመን ምንቼት የሚወጣበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡ ከነሐሴ መባቻ ጀምረው በፍልሰታ ጾም ሁሉ አድርሽኝ ሲባባሉ የቆዩ ጓደኛሞች በቡሄ የተለየ ትዝታ አላቸው፡፡
“ዶሮ ከጮኽ የለም ሌሊት፤
ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት” እንዲሉ ወጣቶች በቡሄ እለት ደመራ ደምረው ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም “በደብረ ታቦር ተራራ ለታየው ብርሃነ መለኮት መገለጥ” ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ታላቁ መጽሐፍ “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም!” እንዳለ ደብረ ታቦር እና ቡሄ በደብረ ታቦር የተለየ ድባብ አላቸው፡፡ ማማው ደብረ ታቦር የደብረ ታቦርን በዓል በተልየ መልክ ያክብራል፡፡ ኢየሱስ ተራራ ላይ የሚጮኽው ጅራፍ ፎገራን አልፎ ይደመጣል፡፡
ጉና ተራራ ላይ የሚጮኸው የእረኞች ሕብረ ዝማሬ ጥጥራን አልፎ ለራስ ጋይንቶች የእንዴት ከረማችሁ መልዕክት ያደርሳል፡፡ የደብረ ታቦር እና ቡሄ በዓል በደብረ ታቦር የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ክረምቱን ከላይ ውኃ ከታች ጭቃ ለበረታበት የሀገሬው ሰው ጭጋጉ ተገልጦ ያያልና ትርጓሜው ከሕይዎት ዑደት እና ከተፈጥሮ ለውጥ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ደብረ ታቦር የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ በዓሉ ከዘጠኙ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን እና ክብረ መንግሥቱን ለሐዋሪያቱ መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉ በክርስቲያኖች ዘንድ ቡሄ በመባልም ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት መላጣ ገላጣ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ቡሄ ማለት ልጆች ጅራፍ የሚያጮሁበት፣ በዋዜማው ችቦ የሚበራበት፣ ሙልሙል ተዘጋጅቶ ለልጆች የሚታደልበት፣ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበር በዓለ ደብረ ታቦር ሲል ይገልጸዋል፡፡
ቡሄ የክረምቱን ማለፍ፣ የጭጋጉን መልቀቅ እና የብርሃኑን ዘመን መገለጥ የሚያበስር በዓል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምስጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምሕሮቻቸው ጋር በመሆን በዓለ ደብረ ታቦርን ወይም ቡሄን በተለየ መልኩ ያከብሩታል፡፡
እንኳን ለበዓለ ደብረ ታቦር አደረሳችሁ!!
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleሶለል-የራያዎቹ የባሕል አምድ!
Next article