
ባሕር ዳር: ነሐሤ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ)
“ሶለል ብየ መጣሁ ሶለል ብዬ
ጌቶች አሉ ብዬ…”
“ሶለል የማንነታችን መገለጫ፤ የባሕላችን አምድ ነው” ይሉታል ራያዎቹ፡፡
ሶለል የራያ መለያ ልዩ ውበት፣ የልጃገረዶች ፍካት መድረክ እና የምስጋና የእልልታ ቃል ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
ሶለል ለራያ ልጃገረዶች ልክ እንደ ሻዳይና አሸንድዬ ልጆች ሁሉ የነጻነት መድረካቸው ነው፡፡ በራያ ሴቶች ከአዘቦቱ በበለጠ የሚዋቡበት፤ ወደ ውጭ ወጥተው የማያውቁም ልጃገረዶች ወጥተው እንዲጫወቱ ከቤተሰብ ፈቃድ የሚያገኙበት ነውና ወቅቱ የሴቶች የነፃነት ቀን በመባልም ይታወቃል።
ሶለል የሚለው ቃል “እሰይ እልል” የሚል ትርጓሜ እንዳለው ይነገራል፡፡
የቆቦ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ስፖርት ባሕል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው የዘንድሮው ሶለል የልጃገረዶች በዓልን ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች ተደርጓል፡፡
የራያ ቆቦ ሕዝብ የበርካታ ቱባ ባሕሎች ባለቤት ነው ያሉት የጽሕፈት ቤት ኀላፊው አበራ አባየ በዓሉ ከነሐሴ 15 እስከ 18/2014 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል፡፡
ራያዎቹ ቀድሞውንም ለታሪክና ባሕላቸው ጥንቁቅ ናቸው፤ በባሕላቸው መዋብን፣ መድመቅን፣ መጠበቅና ማስተዋወቁንም ጭምር ያውቁበታል፡፡
ለሶለል የልጃገረዶች በዓል ደግሞ ልዩ ትኩረት አላቸው፤ ሶለል የማንነታቸው መገለጫ፣ የባሕላቸው አምድ ስለመኾኑ ይገለጻል፡፡
እናም የዘንድሮውን ሶለል በዓል የሚያከብሩት ከወትሮው አከባበራቸው የተሻገረ ዓላማን ያነገበ ይመስላል፡፡
በራያ ቆቦ ከነሐሴ 15 እስከ 18/2014 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ለሚከበረው የሶለል በዓል “ሶለልን በግንባር ለድልና ለነጻነት” የሚል መሪ መልክት ተሰጥቶታል፡፡
በሻዳይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የልጃገረዶች በዓል ታሪክ፣ አከባበሩና ክዋኔው ዙሪያ ጥናት ያደረጉት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አሥተዳደር መምሕር መስፍን ታደሰ እንደሚሉት ሁሉም በዓላት ሲከወኑ ከበዓሉ ታሪካዊ መሰረት ባሻገር የአካባቢውን ባሕል፣ ወግ፣ ፍልስፍና እና ሥነልቦናም ጭምር የሚያስረዱ ናቸው፡፡
የራያ ልጃገረዶች በሶለል በዓል ከየአካባቢያቸው ተሰባስበው ከየትኛውም የቤተሰብ ትዕዛዝ ነጻ ሆነው በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ፡፡
ልጃገረዶቹ የበዓሉ ድምቀት የኾነውን የአሸንድየ ቄጤማ ወገባቸው ላይ አስረው፣ በራያ ትፍትፍ ልብስ ደምቀው፣ የእግር አልቦ እና የጸጉር ሥሬት አምረው ፣ ተውበው ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ።
የራያ ልጆች የሶለል በዓል ግጥሞች የሚነሳው ክብር፣ ሙገሳና ከውብ ዜማቸው ጋር ተደምሮ ልዩ ድባብ ይፈጥራል፡፡
“ሶለል ብየ መጣሁ ሶለል ብዬ
ጌቶች አሉ ብዬ…
ሶለለ ይኼ የማን ነው ቤት፣
ሶለል
የጸዳ የኮራ፣
ሶለል
ከነ ባለቤቱ፣
ሶለል
ስሙ የተጠራ…” እያሉ ያዜማሉ።
መምሕር መስፍን እንደሚሉት የሶለል በዓል በራያ እና አካባቢውም በየዓመቱ ነሐሴ 16 ሲከበር ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎችን መሰረት አድርጎ ነው፡፡
የራያ ቆነጃጅት የሶለል እለት መዋቢያቸው ብዙ ነው፤ እንኳንስ ተውበሽ እንዲያውም እንዲያው ነሽ እንዲሉ የሶለል ልጃገረዶች እንደየ እድሜያቸው የጸጉር አሠራራቸውና አጊያጊያጣቸው ደግሞ ሌላ ውበት ያጎናጽፋቸዋል፡፡
ጋሜና ቁንጮ፣ ጎበዝና ቆንጆ ፣ አንድግራ እና አፈሳሶ በሚባሉ የፀጉር ሥሬቶች አምረውና ተውበው ብቅ ሲሉ ውብ ናቸው፡፡
የጸጉር ሥሬታቸው በእድሜ እና በትዳር ሁኔታ ይለያያል፤ ጋሜ እና ቃሪ (ሳአፈሳሶ) እስከ ዘጠኝ ዓመት እድሜ ያሉ ልጆች የሚሠሩአቸው ናቸው፡፡ አሳስር ለልጃገረዶች ማለትም እድሜአቸው ከ14 እስከ 16 ዓመት ያሉ ይሠሩታል፤ “እጩኝ፤ ለትዳር ደርሻለሁ” እንደማለትም ነው፤ አንድግራ 16 እስከ 20 እድሜ ያሉ እና ያገባችም ያላገባችም ሴት የምትሠራው የፀጉር ሥራ ዓይነት ነው፡፡ ጊጫ፣ አለባሶ፣ ውስጠ ወይራ፣ ሹርባ፣ አሳ ስር፣ ጎበዝ እና ቆንጆ፣ አፈሳሶ እና ሌሎችም አሠራሮችን ፀጉራቸውን ተሠርተው ይዋባሉ፡፡
ፀጉራቸውን ቅቤ ይቀባሉ፣ ዐይናቸውን ኩል ይኳላሉ፡፡ ካላቸው ልብስ ማለትም ስቦ ግጥም፣ ትፍትፍ፣ አምሾ፣ ዋሾ ሸማ ይለብሳሉ፡፡ እንሶስላው ደግሞ የእጃቸው መድመቂያ ነው፡፡
በተለያዩ ክሮች ያሸበረቀ መቀነት ወገባቸው ላይ ሸብ ያደርጋሉ፡፡ የብርድንብል ጌጥ በደረታቸው ላይ ጣል አድርገው ጧት የወጣች ጀንበር መስለው በዓሉን ያከብራሉ የራያ ውቦች።
የሶለል መለያው የኾነውን የአሸንድዬ ቄጤማ ልጃገረዶች በወገብ ታጥቀው በኅብረት ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ሲዘሙ፣ በዝግታ ወገባቸውን ሲያንቀሳቅሱት፣ አብሮ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ እየተወዛወዘ ሌላ ውበት ያጎናጽፋቸዋል፡፡
የራያዎቹ የማይጠገብ ጭዋታ ተደምሮበት ሶለል ተናፋቂ ነው፡፡
“ሶለል ከጎታ ላይ ሆና፣
ሶለል
ታሽካካለች ዶሮ፣
ሶለል
እረ እነየ እገሌ፣
ሶለል
ደልዳላ ወይዘሮ –አሸንድየ፡፡” እያሉ ያወድሳሉ፡፡
በእያንዳንዱ ሁነት የራሱ ግጥምና ዜማ ያለው የራያዎቹ የሶለል የልጃገረዶች ጨዋታ ከምርቃት እስከ ስጦታ ይበረከትላቸዋል፡፡ ስንብታቸውም ምስጋናቸውም በዘፈን ነው፡፡ በታላላቆቹ ቤት በሚያደርጉት
“ከብረው ይቆዩ ከብረው፣
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው፣
ሰላሳ ጥጆች አስረው፣
ከብረው ይቆዩ ከብረው…” እያሉ ይሰናበታሉ፡፡
ሶለል የራያዎቹ ልዩ መልክ፤ የባሕል አምባ፤ ከባሕላዊ ሃብቶቻቸው መካከል ተወዳጁ መለያቸው ነውና በድምቀት ሊያከብሩት ተዘጋጅተዋል፡፡ ተጋበዙልን ጥሪያቸው ነው፡፡
እኛም እንኳን አደረሳችሁ- መልካም በዓል ብለናል!
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
