ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር!!

220

“በታሪክ ከብራለች፣ ለበዓለ ደብረ ታቦር ተመርጣለች”
ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የታደሉ አምባዎች መለኮት ይገለጥባቸዋል፣ ምስጢር ይመሰጤርባቸዋል፣ ጽላት ይወርድባቸዋል፣ መስቀል ይቀመጥባቸዋል፣ ደብር ይደበርባቸዋል፣ ገዳም ይገደምባቸዋል፣ ታቦት ያድርባቸዋል፣ መንፈስ ቅዱስ ይከባቸዋል፣ ንጉሥ ያርፍባቸዋል፡፡ የታደሉ አምባዎች ስማቸው ይነሳል፣ ከትውልድ ትውልድ ይወሳል፣ የታደሉ አምባዎች ቅድስናን የሚሰጠው ይቀድሳቸዋል፣ ባራኪው ይባርካቸዋል።
የታደሉ አምባዎች በቅዱሳን ይመላሉ፣ የታደሉ አምባዎች በጥበብ ይዋባሉ፣ በምስጢር ይረቅቃሉ፡፡ ሰዎች ኹሉ ወደታደሉት አምባዎች ይጓዛሉ፣ ዓይኖቻቸውን በታደሉት አምባዎች ላይ ያሳርፋሉ፡፡ የተዋበ ደም ግባት ያለው፣ እጅግ የበዛ ሰው የሚከተለው፣ ታምራትን እያደረገ ሕዝቡን ኹሉ የሚያድነው ጌታ መለኮቱን ሊገልጥ ወደደ፡፡
ታቦርና አርሞንዬም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል ተብሎ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፡፡ ታቦር ላይ ጌትነቱ ሲገለጽ እስከ አርሞኔም አብርቶ ነበር፡፡ ያን የብርሃን ትንቢት ያዩ አበው ትንቢቱን አስቀመጡ፡፡ የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፣ የጸናና የለመለመ ተራራ ነው፣ የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሳሉ እግዚአብሔር ይሄን ታራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው እንዳለ መጽሐፍ ያን ተራራ ወደደው፡፡ የታደለው ተራራ ጌታ መለኮቱን ይገልጥበት ዘንድ ተመርጧል፡፡
ክርስቶስ ምንም ምንም የማይችለውን መለኮቱን ፍጥረታት በሚችሉት ልክ ሊገልጥ ወደደ፡፡ መለኮቱን ማየት የሚቻለው፣ አይቶም የሚቋቋመው ማንም የለም፡፡ ምድር ቻይ ካልተባለች ለእግሩ መረገጫ አትኾንም፣ ሰማይም ለዙፋኑነት አትመጥንም፣ የሚታየውም ኾነ የማይታያው ዓለም እርሱን አይወስንም፣ እርሱ በዚህ ዘመን ጀመረ፣ በዚህ ዘመንም ይጠናቃቃል የሚባል ዘመን የለውም፡፡ ዘመንን ፈጠረ እንጂ፣ በዘመን አልተፈጠረም፣ ዘመንን ይገዛል እንጂ በዘመን አይገዛም፡፡ ዓለምን ይወስናታል፣ ዓለም ግን አትወስነውም፣ ዓለምን ያሳልፋታል እንጂ አታሳልፈውም፣ ዓለም ሳትኖር ነበር፣ ዓለም እያለችም አለ፣ ዓለም ስታልፍም እርሱ ይኖራል፡፡ የመኖሩ ነገር ረቂቅ ነው፡፡ ዓለም አላፊ ጠፊ ናት እርሱ ግን ዘላለማዊ ነው፡፡
ጌታ ጌትነቱን ሊገጥ በወደደ ጊዜ በመቃብር ካለው ሙሴን፣ ሞትን ካልቀመሰው በብሔረ ሕያዋን ከሚኖረው ኤሊያስን ጌትነቱን ያሳያቸው ዘንድ መረጣቸው፡፡
ሕግ ሰጪ የኾነው አምላክ የሙሴና የኤሊያስ ጌታ መኾኑን ሲገልጥ ሙሴን ከመቃብር፣ ኤሊያስን ከብሔረ ሔዋን አመጣቸው፡፡ ሙሴ ሞትን ቀምሷል፣ ኤሊያስ ግን በብሔረ ሔዋን ይኖራል፡፡ ጌታም ሙታንን እና ሕያውያንን የሚገዛቸው እርሱ መኸሸኑን ሲያጠይቅ ኹለቱን በአንድ ላይ አመጣቸው ይላሉ አበው፡፡ ሙታንም እንደሚነሱ ለማጠየቅ ሲሻ ሙሴን ከሙታን አስነስቶ አመጣው፡፡ በታቦር ተራራ ላይም ወሰዳቸው፡፡
ሐዋርያት በምድር ከእርሱ ሥር ሥር ነበሩ፣ ጌታ ከሐዋርያቱ መካከል ሦስቱን መርጦ ጌትነቱን ወደ ሚገልጥበት ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ የተመረጡት ሐዋርያትም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ናቸው፡፡ በባለሟልነታቸው፣ በጌታ ፍቅር በመጽናታቸው፣ የምስጢር ሐዋርያት ናቸውና ለእነርሱ ተገለጠላቸው ይላሉ አበው፡፡ ሐዋርያቱ ቅናት አልነበረባቸውና ምስጢር እንዲያዩ ተፈቀደላቸው፡፡ ታቦር አምሳለ መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡ ምስክር በሦስት ነገር ይጸናል እና ጴጥሮስን፣ ዮሐንስን እና ያዕቆብን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በዚያ ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ሊገልጥ ነው፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረ ሃና የባሕል ጥናት ዳይሬክተር መምህር እርጥባን ደሞዝ ታቦር ማለት በይብራይስጥ የነጋሪት አምሳል፣ የነጋሪት ቅርጽ ያለው ተራራ ነው ይላሉ፡፡ ጌታ ሩቅ ብሲ መስሏቸው አምላክነቱን እንዳይስቱ ሲሻ ብርሃነ መለኮቱን፣ ጌትነቱን ለመግለጥ ለምስክርነት ይዟቸው ሄደ፡፡ በተመረጠው ተራራ መለኮቱን ገለጠ፡፡ መለኮቱን የሚችለው የለምና ብርሃን በታየ ጊዜ ሙሴ መቃብሬ ትሻለኛለች አለ፡፡ ሐዋርያትም በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ለምን ካሉ አይቻልምና፡፡ ጌታም ይጸኑ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ ጸንተው አዩ፡፡ ባዩትም ጊዜ ተደነቁ፡፡ የታቦር ተራራ የፍቅር ተራራ ነው፡፡ በዘመን የማይገናኙት ተገናኝተበታል፡፡ በጋራ ታይተውታል እና፡፡ የታቦር ተራራ የድል ተራራ ነው፡፡
ቡሔ ከጌታ ዓበይት በዓላት መካከል አንደኛው ነው፡፡ ቡሔ ማለት የበራ፣ የጎላ፣ የደመቀ፣ የተገለጠ ነው ይላሉ፡፡ በሌላም በረዶ መሰለ፣ ነጭ ኾነ ነው ይላሉ፡፡መምህር እርጥባን ቡሔ ቡኾ፣ ሙሉሙሉንም ያመላክታል ነው የሚሉት፡፡
ጌታ የጌትነቱን የገለጠው በወርኃ ነሐሴ በ13ኛው ቀን ነበር፡፡ ይህ ታላቁ የጌታ በዓል በኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በታላቅ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ምስጢራትን የሚያሜሰጥሩ ኢትዮጵያውያንም በታቦር የተገለጠውን የጌታን በዓል ያከብሩታል፡፡ ወርኃ ነሐሴ ሲገባ እረኞች ለበዓለ ደብረ ታቦር ይዘጋጃሉ፡፡ ድምፁን የሚያሰሙበት ጅራፍ ይፈትላሉ፣ ብርሃን የሚያበሩበት ችቦ ያዘጋጃሉ፡፡
ቡሔ የብርሃን በዓል ነውና፡፡ ቡሔ ደስታ፣ ፈስሐ ነው፣ ጌታ በታቦር ተራራ ላይ በተገጠለ ጊዜ በብርሃን ተመላ፡፡ የጌታን ብርሃን ያዩ እረኞች በዚያው ቆዩ፡፡ሰዓቱ ግን መሽቶ ነበር፡፡ ብርሃን በርቷልና እረኞች መምሸቱን አላወቁም፣ ወደቤታቸውም አልተመሰሉም፡፡ ወላጆቻቸው ግን በልጆቻቸው መቅረት ተደናገጡ፣ ልጆቻቸውንም ለመፈለግ ወጡ፡፡ ለጨለማውም ችቦ እያበሩ ነበር፣ ለእረኞችም ምግብ ይኾን ዘንድ ሙል ሙል ይዘው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የኾነው በበዓለ ደብረ ታቦር ቀን በምስጢርና በአምሳል ይደረጋል፡፡
ለዚህ በዓል የተዘጋጀች፣ የተመረጠች፣ በታሪክ የከበረች፣ በሊቃውንት የተመላች፣ የታደለች ከተማ በኢትዮጵያ አለች፡፡ ስሟን መለኮት ከተገለጠበት የታቦር ተራራ ወስዳለች፡፡ ታሪክን፣ ሃይማኖትን፣ ጀግንነትን እና ሀገር ወዳድነትን አስተባብራ ይዛለች፡፡ በዚኽች ከተማ ታሪክ ያከበራቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ የከበሩ ቅርሶች፣ የተክሌ አቋቋም የምስክር ተማሪ ቤትና ሌሎች የበዙ ታሪኮች አሉባት፡፡ ለበዓለ ደብረ ታቦር የተመረጠች፣ ለታላቁ በዓል የታጨች፣ ታላቁን በዓልም ስታከብር የኖረች – ደብረ ታቦር ከተማ፡፡
በዚኽች ከተማ ነገሥታቱ እና መሳፍንቱ ሕዝብ በተሰበሰበበት፣ ሊቃውንት በመሉበት፣ ጠቢባን በተገኙበት፣ ጀግኖች በከበቡት በዓለ ደብረ ታቦርን ሲያከብሩ ኖሯል፡፡ አባቶች ያቆዩት፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚከወንበት በዓለ ደብረታቦር እነኾ ዛሬም በዛችው ከተማ ይከበራል፡፡
በዓለ ደብረ ታቦር ደርሷል፡፡
በታሪክ የከበረችው፣ ለበዓለ ደብረ ታቦር የተመረጠችው ታላቋ ከተማ ሽርጉድ ላይ ናት፡፡ እንግዳን መቀበል፣ ተቀብሎ ማቀማጠል ታውቅበታለች። እንግዶቿን በጉጉት ትጠብቃቸዋለች፣ በሄዱም ጊዜ ስጋጃ አንጥፋ ትቀበላቸዋች፡፡ ባማረው መቀመጫ ታስቀምጣቸዋለች፣ እንጀራውን በመሶብ፣ የሚጠጣውን በገንቦ ታቀርብላቸዋለች፡፡ ወይዛዝርቱ ተውበዋል፣ ያማረው ቀሚሳቸውን አዘጋጅተዋል፣ ያመረው ሹርባቸውን አገማሽረዋል፣ ጎበዛዝቱ ተዘጋጅተዋል ነው፡፡ ጎፈሬያቸውን ያሳምራሉ፣ መውዜራቸውን ይወለውላሉ፡፡
በታቦር ተራራ ላይ ብርሃኑን ያስታዋሉ፣ እያመሰገኑ ይገሰግሳሉ፡፡ ሊቃውንቱ ድንቁን ነገር ያደርጋሉ፣ ዲያቆናቱ፣ ቀሳውስቱ በልብሰ ተክኽኖ ይደምቃሉ፣ የደብረ ታቦር ጎዳናዎች ነጫጭ በለበሱ ምዕምናን ይመላሉ፣ ደብረ ታቦር በደስታ ትዋጣለች፤ በሕብረ ዝማሬም ትናጣለች፣ ከፍ ከፍም ትላለች፡፡ ይሂዱ የጌትነቱን በዓል በታሪኳዊቷ ከተማ ያሳልፉ፡፡ ሃይማኖቱን፣ እሴቱን፣ ጀግንነቱን እና ኢትዮጵያዊነቱን ይዩ፡፡ መልካም በዓል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleከሰሞኑ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ተጓዦች ላይ የተደረገው ቁጥጥር የህወሀት ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ነው ሲል የፌደራል መንግስት ገለጸ።
Next articleሶለል-የራያዎቹ የባሕል አምድ!