“ስለ ብሔራዊ ጥቅም የማያገባው የመንግሥትም ኾነ የግል ሚዲያ የለም” የመንግስት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)

283

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተካሄደው ዘጠነኛው የኢፕድ “ስለ ኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት ትኩረቱን በሚዲያ ሚና ላይ አድርጎ ተካሂዷል።
ውይይቱን የመሩት የመንግስት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በማጠቃለያ ንግግራቸው፤ “ስለ ብሔራዊ ጥቅም የማያገባው የመንግሥትም ኾነ የግል ሚዲያ የለም” ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ሲባል ብዥታ መፈጠር የለበትም፤ ብሄራዊ ጥቅም የወንድማማችነትና የአንድነት ጉዳይ ነው፤ በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፓለቲካ መሥኮች ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው በጋራ የሚቆሙበት ጉዳይ ነው፤ ከዚህ አንጻር ማንኛውም ሚዲያ ይሄንን በውል ተረድቶ መሥራት ይገባዋል ብለዋል።
በየትኛውም ዓለም ያለ ሚዲያ ለተመሰረተበት አገርና ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ይወግናል ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ መንግሥትና ሚዲያውም በዚህ ልክ ተግባብተው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር መሥራት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የትኩረት መጠኑ መለያየት ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ሚዲያ ለብሔራዊ ጥቅም ይሠራል፤ መስራትም ይገባዋል። የሁሉም ጥቅም የሚከበረው ሁሉም ሲሳተፍ ነውና።
ሚዲያ ዜና ከማምረት በላይ ተልዕኮ እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ መረጃን ከመስጠት ባሻገር ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ የሚያደርጉ እሴቶችን መኮትኮትም አለባቸው ብለዋል።
የሚዲያ ነጻነት ሲባል እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ነው መታየት ያለበት ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ በአሜሪካም በአውሮፓም ያለው ነጻነት እንደራሳቸው ባህልና ፓለቲካል ኢኮኖሚ የተቃኘ ነው፤ ስለዚህ የእኛም አገር የሚዲያ ነጻነት በራሳችን ባህልና አውድ ልክ መታየት አለበት ሲሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው በሰጡት የማጠቃለያ ንግግር፤ የሳይበር ሚዲያው ማደግን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት ልንጠቀምበት ይገል ብሎ ማሰብ ያሥፈልጋል፤ ይህ እድገት ኢንቨስትመንትም መሆኑን አምነን መሥራትም ይጠበቅብናል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት “ማህበራዊ ሚዲያ አደገኛ ነው” እያሉ መቀመጥ አይጠቅምም ያሉት አቶ መሀመድ፤ ዘመኑ ለደረሰበት ደረጃ የሚመጥን ፓሊሲና ስትራቴጂ በማዘጋጀት ዘርፉን መምራት ይገባል ሲሉም ነው ያስታወቁት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህሯ ዶክተር አጋረደች ጀማነህ በበኩላቸው፤ መረጀን በፍጥነት ለህዝብ ማድረስ ከሚዲያዎች ይጠበቃል፤ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የኮምንኬሽን ቢሮዎች መረጃን ቶሎ ቶሎ መስጠት ሲችሉ በመሆኑ ይህንን ሃላፊነት መወጣት ይገባል ብለዋል።

“የሚዲያ ነጻነት ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ነጻነት ያለገደብ ሊሆን አይችልም” ያሉት ዶክተር አጋረደች፤ ትልልቅ አገሮች ላይ ያለው ተሞክሮም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ነጻነት ሁልጊዜም በኃላፊነት ውስጥ መሆን አለበት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት መምህሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ጠንካራ ሚዲያ መኖር የጠንካራ መንግሥት መገለጫ ነው፤ ስለዚህ መንግሥት የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች እንዲጠናከሩ አብክሮ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
መንግስት ሚዲያን ባፈነ ቁጥር የገደል መሚቶ ይሆናል ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ሚዲያዎችም የጋዜጠኝነት ሙያ በሚጠይቀው ልክና አግባብ ሥራቸውን መሥራት አለባቸው፤ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ዓለም ከደረሰበት መድረስ ይቻላል ቀላል ነውና ብለዋል። ዘገባው የኢፕድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous articleሻደይ -የዋግሹሞቹ ሌላኛው ቀለም።
Next articleከሰሞኑ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ተጓዦች ላይ የተደረገው ቁጥጥር የህወሀት ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ነው ሲል የፌደራል መንግስት ገለጸ።