ሻደይ -የዋግሹሞቹ ሌላኛው ቀለም።

263

ባሕር ዳር: ነሐሤ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ)
አስገባኝ በረኛ – የጌታዬ ዳኛ፤
አስገባኝ – ከልካይ እምቤቴን ልይ …፡፡ በዋግኽምራና አካባቢው በሻደይ-የልጃገረዶች በዓል በቆነጃጅቶች የሚዜም ተወዳጅ የግጥም ዜማ ነው!
ወርኃ ነሐሴ ሲጋመስ ጋራ ሸንተረሩ በሻደይ (አሸንድዬ) ቅጠል ያሸበርቃል፤ በዋግሹሞቹ መናገሻ ሰቆጣና አካባቢው ደጅ ጎራ ካሉ ተደምጦ የማይጠገበው የልጃገረዶች የሻዳይ ሕብረ-ዝማሬ ለጀሮዎ ይደርሳል፡፡
ዓይነ-ግቡ ውበት፣ ባሕልና ትውፊት ነጋሪ አለባበስ ጋር ተዳምሮም ቀልብዎን ይስባል፡፡ ሻዳይ የልጃገረዶች የነጻነት ማሳያ ነው፤ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርና አካባቢው በድምቀት በነሐሴ ወር ይከበራል።
የዘንድሮውን የሻደይ በዓልም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከነሐሴ 16 እስከ 21/2014 ዓ.ም በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል።
ሻደይ ለዋግ ልጃገረዶችም ሆነ ለመላው የዋግ ኽምራ ሕዝብ ልዩ ትርጉም ያለው ባሕል ነው፡፡ በተለይም ዘንድሮ ሻደይን ከሰላም፣ ከአንድነትና ከኢኮኖሚ አንጻር አስተሳስሮ ለማክበር አስቻይ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ከሔረሰብ አሥተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዋግ ኽምራና አካባቢው የሚከበረው የልጃገረዶች በዓል እንደሌሎች አካባቢም ሻዳይ- መሰረቱ ሲታይ ሃይማኖታዊ ውክልና ያለው ነው፤ የድንግል ማርያምን እርገት ምክንያት ያደርጋል፡፡
በአማራ ክልል በየአካባቢው ተመሳሳይ አከባበር የተለያየ ስያሜ ያለው የልጃገረዶች በዓል እየተባለ የሚጠራው በነሐሴ ወር አጋማሽ በድምቀት ይከበራል፡፡
በላስታ ላል ይበላና አካባቢው-አሸንድዬ፣ በራያና አካባቢው- ሶለል፤ በዋግኽምራና አካባቢው ደግሞ ሻዳይ በሚል ይጠራል፡፡
በሻዳይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የልጃገረዶች በዓል ታሪክ፣ አከባበሩና ክዋኔው ዙሪያ ጥናት ያደረጉት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አሥተዳደር መምሕር መስፍን ታደሰ እንደነገሩን የበዓላቱ እሳቤም፣ ክዋኔም ተመሳሳይ መሰረት አላቸው፡፡
ልዩነቱ እንደየ አካባቢው ባሕልና ወግ በአለባበስ፣ የዜማ እና ውዝዋዜ፣ የጸጉር አሠራርና አጊያጊያጥ ላይ ነው ብለዋል መምሕር መስፍን፡፡
መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ይላሉ መምሕር መስፍን ሕዝቡ በዓላቱን ከኖህ ጀምሮ እያከበረ የመጣ መኾኑን ነው፡፡ ይህ በዓል ለዋግኽምራ ልጃገረዶችም የደስታቸው፣ የአንድነታቸውና የፍቅራቸው፣ የነጻነታቸው ምሳሌ ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
የሻዳይ በዓል ዝግጅቱ የሚጀምረው ከእለቱ አስቀድሞ ከሳምንት በፊት ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ሰዎች በመሰባሰብ፣ የሚለብሷቸውን አልባሳት መምረጥ፣ ጌጣጌጦችን በመግዛትና በመጨረሻም ቡድኑን የሚያስተባብር አንድ ሰብሳቢም በመምረጥ ነው፡፡
አከባበሩ በሦስት የእድሜ እርከን ተከፍሎ እስከ 10 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት፤ ከ10 እስከ 15 ዓመት ድረስና ከ15 ዓመት በላይ ይመደባሉ።
ከ15 ዓመት በላይ የሆኑት ድኮት (የእጅ አምባር)፣ ሁለት ዓይነት መስቀል፣ በአንገታቸው ድሪ፣ የብር አልቦ እግራቸው ላይ ያጠልቃሉ፤ በጥልፍ ቀሚስ ተሽቆጥቁጠው ይሄዳሉ።
ከ15 ዓመት በታች የሆኑት ከብር የተሠራ ድሪ፤ ትልልቅ ክብ ቀለበት ጆሮ ጌጥ፤ ከ10 ዓመት በታች የሆኑት ቁንጮና ጋሜ (መሀል ፀጉራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩን ያደገ) የፀጉር ቁርጥ ይቆረጣሉ።
በልጃገረዶች ወገብ የሚታሰረው የአሸንድዬ ቄጤማ ከሌሎቹ መዋቢያዎቹ ጋር ተዳምሮ የሻደይ በዓል ልዩ መልክ ነው፡፡
በዓሉ ነሐሴ 16 በቤተ ክርስቲያን ይጀመራል፤ በሃይማኖታዊ ምስጋናዎችን ያቀርባሉ፡፡
“ሻደይ ሻደይ ብየ ከቤቴ ገባሁኝ ፤
የማርያም ሙጌራ ተጋግሮ አገኘሁኝ፡፡
ያነን እየበላሁ ከቆላ እስከ ደጋ ፤
ክረምቱም አለፈ አዲስ ዓመት ነጋ” እያሉ ያዜማሉ፤ የፍካት የተስፋቸው ምሳሌ ሻዳይ ለዋጎች፡፡
“አሽከር አበባየ አሽከር ይሙት፣
ይሙት ይላሉ የኔታ፣
አሽከር አይደለም ወይ የሚሆነው ጌታ” የሻዳይ ድምቀት ነው፡፡
በር ተከፍቶላቸው ከገቡ በኋላ የቤቱን ባለቤቶች ማወደስ ይጀመራል።
መምሕር መስፍን እንዳብራሩት በዋግኽምራ በሻደይ በዓል ለድምቀቱ ወንዶችም ሚና አላቸው፡፡ ሴቶች በወገባቸው የሚያደርጉትን ቄጤማ ቆርጠው ለሴቶች ያበረክታሉ፤ ከሌሎች ተንኳሽ ወንዶችም ይጠብቃሉ፤ ከክብረ በዓሉም በኋላ ልጃገረዶችን በሰላም ወደየቤታቸው ያስገባሉ፡፡
በዕለቱ በፍቅር ያሰባትን ፈቃዷን የሚፈልግ ወንድ ጠባቂ ወንዶች ከአላግባብ ተንኳሾችን እንጂ ፍቅሩን በፍቅር ከሚጠይቅ ግድ የላቸውም፡፡
አንድ የፍቅር ምርኮኛ ከሚፈልጋት ሴት ወገብ ላይ የሻደይ ቄጤማውን ለመበጠስ ቀኑን ሙሉ ባይኑ እያማተረ፣ የከጀላትን ልጅ እየተከተለ ቀንቶት ሻደዩን ሲቆርጥ ፈገግ ብላ ካየችው ድል ማድረጉን ያረጋግጣል፡፡
ሴቶቹ ‹‹ሻደይ!›› እያሉ ከሚጫወቱበት ቦታ በሴቶች ዐይን ለመግባትና ተመራጭ ለመኾን ጥንካሬያቸውን ለማሳየት በትግል እና በንጥቂያ ውድድር ፉክክር ያሳያሉ፡፡
የአደባባይ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ ልጃገረዶቹ እና ወንዶች በሻደይ ጨዋታው ጊዜ ያጠፉት ጥፋት ካለ ይቅርታ በመጠያየቅ ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርሰን›› በማለት ለቀጣይ ዓመት ጨዋታ ቃል ገብተው ይለያያሉ፡፡
መምሕር መስፍን እንዳሉት ሻደይም፣ አሸንድዬም ኾነ ሶለል በማኅበራዊው ዘርፍ መልካም ግንኙነት እንዲኖር፣ ፍቅርና አብሮነት እንዲጎላ ሚናቸው የላቀ ነው፡፡ በመስህብነታቸውም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላቸዋል። በፖለቲካው ዘርፍም ቢኾን ሴቶች ነፃነት ተሰምቷቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲያደርጉና በራስ መተማመንን እንዲገነቡ የጎላ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡
ምሑሩ በዓሉ ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገር የባሕል ቱሪዝም ዘርፉ፣ ምሑራን በዘርፉ ላይ ምርምር በማድረግ ወላጅ፣ ልጆች እና ሌሎችም የድርሻቸውን መወጣት ይገባል የሚል ማሳሰቢያ አላቸው፡፡
የሻደይ በዓል “ሻደይ ኢትዮጵያ ለነጻነትና ለድል!” በሚል መሪ መልዕክት ከነሐሴ 16 እስከ 21/2014 ዓ.ም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር መዲና ሰቆጣ ከተማ በድምቀት ይከበራል።
ሻዳይን በዋግኽምራ እንድትታደሙ ተጋብዛችኋል፡፡
እኛም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታችን ይድረሳችሁ ብለናል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous article“አሸንድየ፣ ሻደይና ሶለል በዓልን ጠብቆ ማቆየት የሁሉም ኀላፊነት ነው” የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ
Next article“ስለ ብሔራዊ ጥቅም የማያገባው የመንግሥትም ኾነ የግል ሚዲያ የለም” የመንግስት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)