
ባሕር ዳር: ነሐሤ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለካስ ጥይትም ይናቃል፣ ሞትም ይረሳል፣ አሜካላውና እሾሁም ይዘለላል፣ ጠላቱን ናቀው፣ የጥይት በረዶውን ረሳው፡፡ ምድር ቃውጢ ሆናለች፣ አቧራው ይጨሳል፣ ጥይት ከግራ ከቀኝ፣ ከፊት ከኋላ ይተኮሳል፡፡ የፈረሱ ኮቴ፣ የሰው ጩኸት፣ የጎራዴውና የጋሻው ድምጽ በአንድነት ምድርን አስጨንቋታል፡፡ ጀግና ከጦሩ መካከል ገብቷልና ፈሪ መውጫ ቀዳዳ ጠፍቶበታል፡፡
ወረኃ ነሐሴ ገብቷል፣ የሀገሬው ሰው በፍልሰታ ፆም ሱባኤ ይዟል፡፡ የየአድባራቱ ካህናት በሌሊት እየተነሱ የቤተክርስቲን ደወል ይደውላሉ፡፡ ምመዕኑን በደወል ድምጽ ለጸሎት እንዲበረታ ይጠራሉ፡፡ ሳያቋርጡ ሰዓታቱን ይቆማሉ፣ ኪዳን ያደርሳሉ፣ ቅዳሴ ይቀድሳሉ፡፡
የሀገሬው ሰውም በደወሉ ድምጽ እየተነሳ ወደ አብያተ ክርስቲያናቱ ይቀርባል፡፡ የሸዋ ሊቃውንት በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ጸሎት ያደርሳሉ፣ የሸዋ ባላባቶች ወደ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ይገሰግሳሉ፡፡ ያቺ ታሪክ የመላባት፣ ሊቃውንቱ፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ የሚወለዱባት ምድር በወረኃ ነሐሴ አረንጓዴ ካባ ለብሳ ተውባለች፡፡ ሱባዔው ሳይቋረጥ ምስጋናና ጸሎት ሳይታጎል የፍልሰታ ጾም ተገባደደች፡፡
በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት የሚኖሩ አንዲት እናት የፍልሰታ ጾም ሳትቋጭ ሆዳቸውን ይቆርጣቸው ጀመር፡፡ በሆዳቸው ያለው ጽንስ ቀኑ እንደደረሰ አውቀውታል፡፡ ቀኑ የሚወዱት መላእክ ሚካኤል የሚከበርበት ነበር፡፡ ሕመሙ እያየለ ሄደ፡፡ ወዳጅ ዘመድ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ እኒያ እናት በሰላም እንዲገላገሉ፣ ፈጣሪ ማሕጸናቸውን በጥበብ እንዲፈታ ሁሉም ልመና ላይ ነው፡፡
ፈጣሪ ተመለከታቸው፣ ማሕጸናቸውንም ፈታላቸው፣ ወንድ ልጅ ተወለደ፡፡ በወረኃ ነሐሴ በ12ኛው ቀን የተወለደው ወንድ ልጅ አስራ ሁለት ጊዜ እልል ተባለለት፡፡ በተወደደች ቀን የተወለደ የተወደደ ልጅ፡፡ ለሀገር የተጠራ፣ ወገንን የሚያኮራ ወንድ ልጅ፡፡ በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ክርስትና ተነሳ፡፡ አንዳንዱ በክህነት፣ ሌላው በጦርነት ስሙ ሲነሳ ይኖራል፡፡ በጥበብ አደገ፡፡ ወደ ሸዋ ቤተ መንግሥትም አመራ፡፡
ዘመን ዘመንን ተክቶ ምኒልክ ነገሡ፡፡ በተመረጠችው ቀን የተወለደው ልጅም በምኒልክ ቤተ መንግሥት ታላቅ ስም ያለው ጥበበኛና ጀግና የጦር መሪ ሆነ ጀግናው የጦር መሪ ፊታውራሪ ገበየሁ ( አባ ጎራ)፡፡ በዚያ ዘመን አባ ዳኘው ምኒልክ የሚሳሱላትን ሀገራቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ ደፋ ቀና ላይ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ የተከበረችና የታፈረች ሀገር ትሆን ዘንድ እየታተሩ ነው፡፡ ይህ ዘመን የአውሮፓ የቀኝ ግዛት ዘመን የተፋፋመበት ነበር፡፡
አውሮፓውያን ነፍጥ እያነሱ፣ ሠራዊት እየቀሰቀሱ አቅማቸው የደከሙ ሀገራትን እየወረሩ ያስገብሩ ነበር፡፡ ዋነኛ ትኩረታቸው ደግሞ የጥቁሮች ምድር አፍሪካ ነበረች፡፡ አውሮፓውያን ነፍጥ እያነሱ፣ ውቅያኖስ እየገመሱ፣ የብስ እያሰሱ ወደ አፍሪካ ተሻገሩ፡፡ በአፍሪካውያን ላይም ጦርነት ከፈቱ፡፡ አፍሪካውያን እጃቸውን ለወራሪ አሳልፈው ሰጡ፡፡ ልናሰለጥናችሁ ነው የመጣነው ያሉት አውሮፓውያን የሀገሬውን ተወላጆች እንደ እቃ ሸጡ፣ ለወጧቸው፣ በእርስታቸውና በየቀያቸው አያሌ በደል አደረሱባቸው፡፡
የነጮችን ጦር በአፍሪካ ምድር የሚገዳደረው ጠፋ፡፡ ነጮች አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ ሊውጧት በአፍሪካ ምስራቃዊ ንፍቅ የምትገኝ አንዲት ጥንታዊትና ታሪካዊት ሀገር ቀረቻቸው፡፡ ያችንም ሀገር እንደሚይዟት እርግጠኛ ኾነዋል፡፡ ለምን ጥቁር ነጭን መቋቋም አይችልም ብለዋልና፡፡
ይችን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና የጀግና እናት የሆነችን ሀገር ለመውረር የተነሳችው ደግሞ ጣሊያን ነበረች፡፡ እምዬ ምኒልክ አልደረስንባችሁም አትድረሱብን አሉ፡፡ ሰሚ ግን አልነበራቸው፡፡ የኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ተሻገረ፡፡ ይህን ያዩት ምኒልክ እሳት ለበሱ፡፡ እቴጌ ጣይቱ አራስ ነበር ኾኑ፡፡ ኢትዮጵያን ጠላት እንደማይነካት፣ ከከፍታዋም እንደማያወርዳት ቃል ገቡላት፡፡
አባ ዳኘው በማርያም ምለው ለሚወዱትና ለሚወዳቸው የሀገሬው ሰው አዋጅ አስነገሩ፡፡ የሀገሬው ሰው በቁጣ ተነሳ፡፡ እምዬ ልባቸውን የሚያምኗቸው፣ በጀግንነታቸው የሚኮሩባቸው እልፍ ጀግኖች በፊት በኋላቸው፣ በዙሪያቸው አሏቸው፡፡ ከእነዚህ ጀግኖች መካከል ታዲያ ፊታውራሪ ገበየሁ አንደኛው ናቸው፡፡
ምኒልክ ገሰገሱ፡፡ ጀግና ጦር መሪዎቻቸውን ከፊታቸው አስቀደሙ፡፡ ጠላት አምባላጌ ደርሷል፡፡ ገበየሁ አባ ጎራና ሌሎች ጀግኖች በንጉሳቸው ትዕዛዝ አማካኝነት ጦር እየመሩ ከጠላት ሰፈር ደርሰዋል፡፡ ሌሎች የጦር መሪዎች ንጉሡ እስኪደርሱ ጦርነት አይጀመርም አሉ፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ ግን እኔ ለጌታዬ ለምኒልክ የድል ድግስ እንጂ ጦርነት አላቆይም አለ፡፡ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያንን ሠራዊት አጣደፈው፡፡ ጠላት ተጨነቀ፡፡ በዚሕ ወቅት የገበየሁ ጤንነት ልክ አልነበረም፡፡ ገበየሁ አሞታል፣ ጤንነቱ ጥሩ አልነበረም፣ ነገር ግን ከእርሱ ሕመም በላይ ኢትዮጵያ ታማለች፣ ኢትዮጵያ በጠና ተይዛለች፣ ኢትዮጵያ በጠላት በሽታ ተከብባለች፡፡ ገበየሁ ሕመሙን ረሳ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ʺ ፊታውራሪ ገበየሁ ታመው ነበር፡፡ ነገር ግን ከጦርነት አልቀሩም፣ ከበቅሎ ላይ ተቀምጠው አይዞህ በለው፣ አይርም ያለቀብህ በጎራዴ በለው እያሉ አዋጉ” ብለው ጽፈዋል፡፡ ጣሊያን አምባላጌ ላይ እንዳልነበር ሆነች፡፡
ʺአላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፣
ለምሳም ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው” ተባለለት፡፡ ገበየሁ መብረቅ ሆነባቸው፡፡ የጣሊያን ሠራዊት ነብር እንዳየች ሚዳቋ የተረፈው ደንብሮ መቀሌ ገባ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች ተከታትለው አሳደዱት፡፡ በጥበብ እና በጀግንነት በመቀሌም ድባቅ መቱት፡፡
የማይቀረው ጦርነት ቀርቧል፡፡ የወገን እና የጠላት ሠራዊት በዓድዋ ላይ ተፋጥጧል፡፡ ገበየሁ በአምባላጌና በመቀሌ አያሌ ጀብዱን ፈጽሟል፡፡ ከአንጎለላ እስከ ዓድዋ ያሉ ተራራዎች ገበየሁ ገበየሁ አሉ፣ አባ ጎራ እያሉ ተጣሩ፣ ሠራዊቱም አባ ጎራ አባ ጎራ ሲል ዘመረ፣ የገበየሁ ስም ከተጠራ ጠላት ይርዳል፣ ወኔ ይክደዋል፣ ገበየሁ ጦሩን ከመራው፣ ገበየሁ ጎራዴውን ከሳለው፣ ገበየሁ ፈረሱን ከኮለኮለው፣ ገበየሁ ጋሻውን ካስተካከለው፣ ገበየሁ ፊቱን ካጠቆረ፣ ገበየሁ ፈረሱን ካሰገረ በኋላ ነገር አለሙ አበቃ፡፡ ጠላት አለቀለት፣ ምድር ትደባለቃለች፣ አቧራው ይጨሳል፣ የጠላት አንገት በቀኝ በግራ፣ በፊት በኋላ ይቀነጠሳል፡፡
ሰዓቷ ደረሰች፡፡ የማይቀረው ጦርነት ተጀመረ፡፡
“የጠላቴ ጥይት ከመታው ጀርባዬን፣
ላሞራው ጣሉለት አታንሱት ስጋዬን፣
ላገሬ ስዋደቅ ግንባሬን ከመቱኝ
የወንድ ሞት ነውና አንሱና ቅበሩኝʺ አባ ጎራ ከጦርነቱ አስቀድሞ ለንጉሡ ለምኒልክ አንድ ቃል ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይሄም ቃል በጦርነት ጊዜ በጠላት ጥይት ከኋላው ከተመታ በዚያው ወድቆ እንዲቀር አስከሬኔን እንዳያነሱት፣ እየተዋደቀ ፊት ለፊት ከተመታ ግን ከትውልድ ሀገሩ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት መልሰው እንዲቀብሩት ቃል ሰጥቶ ቃል ተቀበላቸው፡፡ ቃል ለምድር ቃል ለሰማይ የጎራውን ግንባር እንጂ ጀርባ ማን አይቷት፣ አባ ጎራ ወደፊት እንጂ ወደኋላ መች ያውቅና፣ ገሰገሰ፣ ውሽንፈሩን እየጣሰ፣ የሚወርደውን ማት እያለፈ የጠላትን አንገት ይቀነጥስ ገባ፡፡ በጠላት ከባድ መሳሪያ ጩኸት የተደናገጠውን ጦረኛ ጎራው ተመለከተ፡፡ ይህን ድርጊት ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ አጤ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው ʺ ተዋጊው የጦር ሠራዊት ወደፊት ለመግፋት እንደ አመነታ ባየ ጊዜ ቀይ ልብስ የለበሰው ፊታውራሪ ገበየሁ ወደ ሰዎቹ ፊቱን አዙሮ የአምባላጌው አሸናፊ ፊታውራሪ ገበየሁ በምን አኳኋን እንደሞተ ወደ ሸዋ በሕይወት የሚመለሱት ይናገሩ ብሎ ተናግሮ እንደ አንበሳ ወደ ጣሊያኖቹ መስመር ገብቶ ሲዋጋ በሶስት ሰዓት ላይ በመትረጌስ ተመትቶ ኪዳነ ምህረት እበሩ ላይ ወደቀ” ብለዋል፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ እንዴት እንደሞተ ለጌታየ ለምኒልክ ንገሩ ብሎ ገስግሶ ገብቶ ጠላትን እየወቃው እያለ በጥይት ተመትቶ ወደቀም የሚሉም አሉ፡፡
አንጎለላ ኪዳነ ምህረት የተገኘው ቃል አጥባቂው ጀግና በዓድዋ ኪዳነ ምህረት በር ላይ ወደቀ፡፡
ʺየዓድዋ ሥላሤን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” የተባለለት ጀግና በደሙ ሀገርን ቀደሳት፣ በቃል ኪዳን አሠራት፣ በጽኑ መሠረት ላይ አቆማት፡፡ እርሱን ያዩ የኢትዮጵያ ጀግኖች ሞትን አብዝተው ናቋት፡፡ ገበየሁ ለሞተላት ኢትዮጵያ እነርሱም ሊሞቱላት ተሸቀዳደሙ፡፡ እንደ መብረቅ በሚያበራው ጎራዴያቸው የጠላትን አንገት እየቀነጠሱ ጣሉ፡፡ ድል ለባለ ድሎቹ ሆነች፡፡ ጣልያን በዓድዋ ተራራ ላይ እንደ ዱቄት ተበተነች፡፡ የኢትዮጵያ ሠንደቅ በእነ ገበየሁ ደም ላይ ከፍ አለች፡፡
ገበየሁ የኢትዮጵያን ሕመም ታመመላት፣ ሞቷን ሞተላት፣ ትንሣኤዋን በሞቱ አሳያት፣ በደሙ ማሕተም፣ በአጥንቱ መሰሶነት አጸናት፡፡ አጼው ቃላቸውን አጸኑ፣ የጀግናውን አጽም ከዓድዋ ወደ አንጎለላ አመጡት፡፡ በዚያም አሳረፉት፣ በሕይወት ከገበየሁ የተቀበሉትን ቃል ፈጸሙት፡፡ ገበየሁና ምኒልክ በአንድ ቀን ተወለዱ፣ በአንድ ቀን ክርስትና ተነሱ፣ ተጣምረው ወደ ዓድዋ ገሰገሱ፤ በዓድዋም ጠላትን ደመሰሱ፣ ዳሩ ገበየሁ ከእነፈረሱ ወደ አንጎለላ ዳግም አልተመለሰም፡፡ በቃላቸው እና በማይፈታው ጀግንነታቸው ሀገራቸውን አስከበሩ፡፡ እነሆ ፊታውራሪ ገበየሁን ያስገኘች ቀን ዛሬ ናት፡፡
አባ ጎራ ኾይ ተራራዎች ዛሬም ገበየሁ፣ ገበየሁ ይላሉ፣ ልጆችህም ስምህን ይጣራሉ፣ ጠላቶችህም እስከዛሬ በስምህ ይደነብራሉ፡፡ ስለ ሞትክላት ሀገርህ እንሞታለን፣ ሞትን ስለናቅክላት ኢትዮጵያ ሞትን እንነቃለን፣ የማይሻረው ቃል ኪዳንህን እንቀበላለን፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
