ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ !!

222

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለንጉሠ ነገሥቱ ብቻ ሳይኾን ለሚወዱት ሕዝብ ጭምር ዘውድ፣ የአዲስ አበባ ቆርቋሪ፣ የሴት ባለመላ እና የጦር አጋፋሪም ጭምር ናቸው፡፡ ጥበብን ከድፍረት፣ እውቀትን ከክህሎት፣ የሀገር ፍቅርን ከእምነት ጋር ታድሏቸዋል፡፡ ለሀገራቸው የዘመናዊነት ጉዞ አሻራ ዘመን የማይሽረው አበርክቶ ነበራቸው፤ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፡፡
ትልቁ ራስ ጉግሳ የጎንደሯን ባላባት ወይዘሮ ማሪቱን አግብተው ወይዘሮ ሂሩትን ይወልዳሉ፡፡ ወይዘሮ ሂሩት ከራስ ገብሬ እና ከወይዘሮ ሳህሊቱ የሚወለዱትን ደጃዝማች ኃይለ ማሪያምን አግብተው ደጃዝማች ብጡልን እንደወለዱ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ደጃዝማች ብጡል ደግሞ የጎጃም ደብረ መዊዕ ባላባት የኾኑትን ወይዘሮ የውብዳርን አግብተው ነሐሴ 12/1832 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ በደብረ ታቦር ከተማ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ይወልዳሉ፡፡
በዚህም እቴጌዋ የአፄ ፋሲል ተወላጅ ከኾኑት ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ፍፃሜ መንግሥት) የሚመዘዝ የዘር ሐረግ አላቸው፡፡ እናም የዘር ሐረጋቸው ከጎንደር፣ ከጎጃም እና ከወሎ ይመዘዛል ማለት ነው፡፡ እቴጌዋ በሳል፣ አስተዋይ እና ተራማጅ ነበሩና የኋላ ኋላ ደግሞ በጋብቻ ሸዋ ድረስ ዘልቀው በመተሳሰርም በዘመነ መሳፍንት የቆሰለችውን ኢትዮጵያ መርምረውና አክመው አንድና ጠንካራ ማዕካላዊ መንግሥት እንዲኖራት አድርገዋል፡፡
እቴጌ ጣይቱ በ13 ዓመታቸው አባታቸው በጦርነት በመሞታቸው ደብረ ታቦርን ለቅቀው ወደ እናታቸው ሀገር ወደ ጎጃም በመምጣት ደብረ መዊዕ በሚገኘው ደብር ቀደም ሲል ጎንደር ውስጥ በማኅደረ ማርያም ጀምረውት የነበሩትን ትምሕርታቸውን እየተማሩ ይቀመጣሉ:: ዳግም ወደ ደብረ መዊዕ ተመልስው ትምሕርታቸውን አስቀጥለው እንደነበርም ይነገራል፡፡
ከብዙ የሕይዎት ውጣ ውረድ በኋላ እቴጌ ጣይቱ በጥበብና በሕይወት ፍልስፍና የላቀ ችሎታ ባለቤት መኾናቸው እየታወቀ መጣ፡፡ ይህንን የጣይቱን ዝና ከሰሙ ልዑላን መካከል ወጣቱ ምኒልክ አንዱ ናቸው፡፡ በወቅቱ የምኒልክ ሞግዚት የነበሩት ደጃዝማች ተሰማ ናደው ከሌሎች ቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ተማክረው ጣይቱን እና ምኒልክን ለማጋባት ሙከራ አድርገው ነበር፤ ምንም እንኳን በወቅቱ በተለያዩ ችግሮች ጋብቻው ቢዘገይም፡፡
ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ፡፡ ንጉሥ ምኒልክ ሚያዚያ 25/1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በቁርባን ጋብቻቸውን ፈፀሙ፡፡ በአራት ዓመታት ልዩነት ነሐሴ 12 /1836 እና ነሐሴ 12 /1832 ዓ.ም ሚስት እና ባል በቅደም ተከተል በተመሳሳይ ቀን እንደተወለዱ የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ የሚገርመው ግን ተመሳሳይ ቀን መወለዳቸው ብቻ ሳይኾን በኢትዮጵያዊያን ወግና ባሕል ብዙም ባልተለመደ መልኩ ሚስት ባልን አራት ዓመታት አስከንድተው መብለጣቸው ነው፡፡
እቴጌ ጣይቱ አጼ ምኒልክን ካገቡ እና እቴጌ ከተባሉ በኋላ ያልተሳተፉበት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ አልነበረም፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው እቴጌይቱን ሲገልጹ ለሸዋ ንጉሥ አድባር፣ ለምኒልክ መንግሥት በሳል አማካሪ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይ እና አርቆ አሳቢ እመቤት ሰጥተው ይላሉ፡፡ አጼ ምኒልክ አዳዲስ ሥልጣኔዎችን ለማስገባት በቆረጡ ጊዜ አጋራቸው እቴጌ ጣይቱ ነበሩ ይባላል፡፡
ዘመናዊ ትምሕርት ቤት ሲያቋቁሙ፣ የባቡር ሃዲድ ሲዘረጉ፣ ውኃ በመዘውር እንዲቀዳ ሲያደርጉ፣ በቀጭኑ ሽቦ በስልክ ግንኙነት በተጀመረ ጊዜ፣ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ቤት ሲያስመጡ፣ የእህል ወፍጮ ሲተከልና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ አጋዣቸው የነበሩት ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ናቸው፡፡ የእቴጌዋን ስም ከፍ ካደረጉ እና አሻራቸውን ዘላለማዊ ካደረጉት ተግባሮቻቸው ግንባር ቀደሙ አዲስ አበባ ከተማን መቆርቆራቸውና መጠሪያ ስሟንም ለመሰየም መቻላቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆቴል መስራች ናቸው፤ የባልትና ሙያን እና የሽመና ጥበብን ለቤተ መንግሥቱ በማስተዋወቅም ግንባር ቀደም መኾናቸው ይነገራል፡፡
“ሴት የላከው ጅብ አይፈራም” እንዲሉ ጣሊያን ከምኒልክ ይልቅ ጣይቱን ትፈራለች ይባላል፡፡ ጣሊያኖች በውጫሌ ውል ካሰፈሯቸው ነጥቦች በአንቀፅ 17 ስር የተቀመጠውን የጣሊያንኛ ትርጉም ኢትዮጵያን በሚጎዳ መልኩ ጥቅም ላይ ውሎ በተገኙ ጊዜ እቴጌዋ የያዙት አቋም የማያወላውል ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ በሌላ መንግሥት ፊት የጣሊያን ጥገኛ መኾኗን ለማሳወቅ ይፈልጋሉ ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም፡፡ እኔ ራሴ ሴት ነኝ ጦርነት አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ” ሲሉ አይቀሬውን ጦርነት በጸጋ እና በጀግንነት ይቀበላሉ፡፡
የተናገሩትን የሚተገብሩት፣ ለሀገራቸው ክብር እና ለሕዝባቸው ፍቅር ጦርነትን ያክል ፈታኝ ዳገት ከመወጣት ያልገደባቸው እመቤት በአይቀሬው ጦርነት በመሪነት ከፊት ተሰለፉ፡፡ የምኒልክ ጦር “ምታ ነጋሪት፤ ክተት ሠራዊት” ብሎ ወደ አድዋ ሲተም የጦር ባለመላዋ 3 ሺህ እግረኛ እና 6 ሺህ ፈረሰኛ አስከትለው ውጣ ውረድ የበዛበትን የጦርነት ጉዞ በድል አድራጊነት አጠናቀቁ፡፡ መቀሌ ላይ በስልት አድዋ ላይ በሰይፍ እና በጎራዴ የሰላቶን ጦር ያሸነፉት እመቤት ሀገራቸውን ከውርደት ሕዝባቸውን ከባርነት በመታደግ አፍሪካ የማትረሳው ውለታን አበረከቱ፡፡
መልካም ልደት ለንግሥቷ !!
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየኢትዮጵያ ኩባንያዎችን ከአሜሪካ ድርጅቶች ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
Next article“የጠላቴ ጥይት ከመታው ጀርባዬን፣ ላሞራው ጣሉለት አታንሱት ስጋዬንʺ