ያለም ጣም ምኒልክ!

173

ባሕር ዳር: ነሐሤ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሥልጣኔ ቀንዲል፣ የሥልጡን ሕዝብ መሪ፣ አማኝና ታማኝ፤ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ቀያሽ፣ የኩሩ ሀገር እና ሕዝብ ባለቤት፤ የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ባለአደራ፤ የጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክ አንጥረኛ፤ የአድዋ ድል አውራ እና የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አብሪ ኮኮብ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ መሪ ብቻ ሳይሆኑ ታታሪ፣ ንጉሥ ብቻ ሳይሆኑ የልብ አድርስ፤ አዛዥ ብቻ ሳይሆኑ ታዛዥ እንደነበሩ ድፍን ሀገር ዘመን ተሻግሮ እስከ ዛሬም ድረስ ይመሰከርላቸዋል፤ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ፡፡
ቅንነትን ከትህትና፣ ጀግንነትን ከትዕግስት፣ አርቆ አሳቢነትን ከአስተዋይነት የታደሉ ስለነበሩ ብዙዎች “በምኒልክ አምላክ” ሲሉ በስማቸው እስከመማጸን ደርሰዋል፡፡ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕሪ ውጭ እና ከመንግሥት ሥሪት ባሻገር ጸባያቸው በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ናቸው፡፡ አቀራረባቸው ተመራጭ ነው፡፡ አመራራቸው በሳል፣ ይቅርታቸው ወሰን አልባ እና ለሀገሬው ሕዝብ የልብ ሰው ተደርገውም ይወደሳሉ፡፡
“የመድኃኒት ጥቂት ይበቃል እያለች፤
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች” እንዲሉ ሐበሾች አንድ ሆነው ተፈጥረው ሳለ ብዙ የፍቅር ስሞችን ከታደሉ ጥቂት መሪዎች መካከል ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አንዱ ናቸው፡፡ “እምየ ምኒልክ” ሲሉ በፍቅር የሚጠሯቸው እንዳሉ ሁሉ “ርሃቤ ምኒልክ” ሲሉ በስስት እና በናፍቆት የሚያቆላምጧቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡
ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እውን መሆን ምክንያት የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ የማይዘነጋቸው እና ዘመን የማይሽራቸው አበርክቶዎቻቸው ዛሬም ድረስ ህያው ምስክሮች እንደሆኑ ዘልቀዋል፡፡
አባታቸው የንጉሥ ሣኅለ ሥላሴ ልጅ የነበሩት አቤቶ በሻህ ወረደ በኋለኛው ዘመን የንግሥና መጠሪያቸው ልዑል ኃይለ መለኮት ሣኅለ ሥላሴ ናቸው፡፡ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ እጅግአየሁ ለማ አድያም ይባላሉ፡፡ ከደብረ ብርሃን ከተማ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው ገጠራማዋ አንጎለላ ውስጥ ነሐሴ 12/1836 ዓ.ም ብላቴናው ምኒልክ እና የመጻዒዋ ኢትዮጵያ ንጉሥ ይህችን ምድር ተቀላቀለ፡፡
ምኒልክ የኋላ ኋላ በአካል ዳጉሶ፣ በአዕምሮ ጎልምሶ እና በዙፋን ነግሶ በሚመራው ሕዝብ ዘንድ ሞገስ የተቸረው የጥቁር አፍሪካውያን ሁሉ አርነት ይሆናል ብሎ ያሰበ ባይኖርም ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ ምኒልክ አሉት፤ ዳግማዊ መሆኑን በማመን፡፡
ሕጻኑ ምኒልክ ገና 12 ዓመት እንደሞላው አባቱ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፡፡ ኅዳር 1/1848 ዓ.ም የአባቱ ኃይለ መለኮት የቀብር ሥነ ስርዓት እንደተፈፀመም አልጋውን በይፋ ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን የምኒልክን ታሪክ አንቱ እያልን እናቀርብ ዘንድ እንገደዳለን፤ ምክንያቱም ንጉሥ ዘ ሸዋ ከዚህ ይጀምራልና፡፡
የመጻዒዋ ኢትዮጵያ መሪ የሚሆኑት ብላቴናው ንጉሥ የሸዋ ንጉሥ በመሆን ይለማመዱ ዘንድ ሕዝብ አምኖ ቀባቸው፤ ወዶ እና ፈቅዶም ሾማቸው፡፡
የሕዝብ ፍቅር እና ክብር የተቀቡት ምኒልክ ንጉሥ ዘ ሸዋ ገና የሀገሪቱ ንጉሠ ነገሥት ሳይሆኑ ታላላቅ እና ዐይነ ግቡ በጎ ተግባራትን ለሀገራቸው አበረከቱ፡፡
በመጨረሻም ጥቅምት 25/1882 ዓ.ም በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተዉ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለዉ በእንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲያን ነገሡ፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክን በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የተለየ ክብር እና ቦታ ካሰጧቸው ተግባራት አንዱ የአድዋ ድል ነው፡፡ ወራሪዋ ጣሊያን በቅኝ ግዛት የባርነት ቀንበር ኢትዮጵያን ለመግዛት እስከ ጦርነት የደረሰ እርምጃ ብትወስድም በሀገራቸው ድርድር የማያወቁት ምኒልክ እና ለንጉሣቸው ቀናዒነት ሞልቶ የተረፈላቸው ኢትዮጵያዊያን እሽ ብለው ቅኝ የሚገዙ አልሆኑም፡፡ በመጨረሻም ጣሊያን በምኒልክ ጦር እስከ ሮም አንገት የሚያስደፋ ሽንፈትን ተከናንባ ተመለሰች፡፡
አጼ ምኒልክ ከአድዋ ድል በተጨማሪም ሀገራቸውን ሥልጡን እና የማትደፈር ለማድረግ እልፍ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያን አበርክቶዎች ፈጽመዋል፡፡ ከባቡር እስከ ስልክ፣ ከፖስታ እስከ ኤሌክትሪክ፣ ከአውቶሞቢል እስከ ቧንቧ፣ ከዘመናዊ ሕክምና እስከ ባንክ፣ ከገንዘብ እስከ ማተሚያ ቤት፣ ከህትመት እስከ ፖሊስ፣ ከሆቴል እስከ ሲኒማ፣ ከወፍጮ እስከ መንገድ፣ ከቀይ መስቀል እስከ ሚኒስትሮች ሹመት ድረስ ዘመናዊነትን ተግተው አስተዋወቋት፡፡
ይህንን የምኒልክን በጎነት ያስተዋሉት ኢትዮጵያዊያንም፡-
ይቁረጡኝ ይፍለጡ ይህው ቆምኩለዎ፣
ያለም ጣም ምኒልክ ብየ ሰደብኩዎ። ብሎ እስከመቀኘት ተደርሷል፡፡
ከልጅነት እስከ እውቀት ሀገራቸውን ተግተው ያገለገሉት አጼ ምኒልክ በጠና ታመሙና ከኅዳር 1902 ዓ.ም ጀምሮ ከቤት ዋሉ፡፡ ታኅሣሥ 3/1906 ዓ.ም በእለተ አርብ አረፉ፡፡ ሕዝቡ የምኒልክን ሞት ከሰማ ይረበሻል ተብሎ በሕይወት አሉ! እየተባለ እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ሁለት ዓመት ከ10 ወር ድረስ ሞታቸው ተደበቀ፡፡ በምኒልክ ሁኔታ ግራ የተጋባው ሕዝብም እንዲህ ሲል የንጉሡን ሁኔታ ይጠይቅ ነበር።
“46 ዓመት የገዛኸው ንጉሥ፤
እንዳለህም ስጠኝ ከሌለህም ላልቅስ” ሲል የሚወዳቸውን ንጉሡን እርም አወጣ፡፡
መልካም ልደት ለንጉሥ ምኒልክ!
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous articleወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሠረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሐሳብ ሰነድ ጸደቀ።
Next articleየኢትዮጵያ ኩባንያዎችን ከአሜሪካ ድርጅቶች ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡