ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሠረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሐሳብ ሰነድ ጸደቀ።

316

ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሠረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሐሳብ ሰነድ መጽደቁን የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ አስታወቀ።
የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ በጉዳዩ ዘሪያ ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
መንግሥት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ፣ እስካሁን የነበረውን እንቅስቃሴ፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አድርጓል።
እንደሚታወሰው ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት ለሰላም እድል ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ለአብነትም የተናጠል የሰብዓዊነት ተኩስ አቁም ማወጅን ጨምሮ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳት፣ እስረኞችን መፍታት፣ የሰብዓዊ ድጋፍን በከፍተኛ ሁኔታ የማሳለጥ እና መሰል እርምጃዎችን ወስዷል።
ከእነዚህ እርምጃዎች በተጨማሪ፣ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እና ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ይታወቃል ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሰላም ንግግር ያለቅድመ ሁኔታ በየተኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር ያለውን ዝግጁነት መግለጹ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት የሰላም አማራጭን በዘላቂነት እውን ለማድረግ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል፣ በተለይም የግጭት ሰለባ እና ተጋላጭ በኾኑ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪ የኾኑ ዜጎች በዕለት ተዕለት ኑሯቸው እየገጠማቸው ያለውን ችግር መቀረፍ እንደሚገባ፤ በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍ አስተማማኝ እና ዘላቂ በኾነ መንገድ ለማድረስ ይቻል ዘንድ፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት እና የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ሥራ ለማስጀመር አስቻይ የኾነ ሁኔታ በፍጥነት ለመፍጠር፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ ላይ መድረስ እንደሚገባ ኮሚቴው አጽኖኦት ሰጥቶ ተወያይቷል።
ይህን ሂደት ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ፣ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሐሳብ ላይ ውይይት በማድረግ የምክረ ሐሳብ ሰነዱን በማዳበር አጽድቋል። እንዲሁም ኮሚቴው ይህ ምክረ ሐሳብ በተቻለ ፍጥነት ለአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ ወስኗል። እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረትን የሰላም ጥረት በሚደግፉ አካላት ትብብር በመታገዝ በአጭር ጊዜ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ምክረ ሐሳቡን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማብራሪያ እንዲሰጥ በወሰነው መሠረት ይህ ተግባር ዛሬ ተከናውኗል።
በተጨማሪም ኮሚቴው፣
▪ ወደተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ፣ አስፈላጊ ቅደመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን፤
▪ የአፍሪካ ሕብረትም የሰላም ንግግሩ በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጥነት ወሰኖ ንግግሩ እንዲጀመር፣ ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በቅርበት እየተሠራ እንደኾነ ገምግሟል።
እንዲሁም የሰላም ዐብይ ኮሚቴው፣ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ፣ የሚመለከታቸው ንዑስ ኮሚቴዎች እና ተቋማት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ከወዲሁ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በተጨማሪም ለሰላም አማራጩ እውን መኾን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየውን ድጋፍ በማድነቅ፣ ይህ ድጋፍ ተጥናክሮ እንዲቀጥል፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ከአፍሪካ ሕብረት ጎን በመቆም የሰላም ጥረቱ የተሳካ እንዲኾን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ኮሚቴው ጥሪ አስተላልፏል።

Previous article“ብርሃን ዘኢትዮጵያ” የእቴጌ ጣይቱ 182ኛ ዓመት ልደት በደብረ ብርሃን ከተማ ተከበረ፡፡
Next articleያለም ጣም ምኒልክ!