ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲከኞች አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባ ተማሪዎች ተናገሩ።

238

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲከናወን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናግረዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች እና ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑም ነባር እና አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሏል። የነባር ተማሪዎች መደበኛ ትምህርትም ቀደም ብሎ ነው የተጀመረው።
የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ደግሞ ዛሬ ጥቅምት 10/2012 ዓ.ም ትምህርታቸውን ይጀምራሉ፡፡ አብመድ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ለሀገር የሚጠቅም ትውልድ የሚቀረጽባቸው በመሆናቸው ስነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለዓላማቸው መሳካት በትጋት እንደሚማሩ ተናግረዋል። ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡት እውቀት ለመገብየትና ልምድ ለማግኘት በመሆኑ ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ሀገርን ሊጠቅሙ ስለሚችሉበት መንገድ በማሰብ እንደሚማሩም አስተያዬታቸውን ለአብመድ ሰጥተዋል፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው ከማዕከላዊ ትግራይ እና ከምስራቅ ሸዋ የመጡት የማነ ነጋሽ እና ሞላ ሲሳይ ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪም አብረዋቸው ከሚማሩ ከተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የተውጣጡ ተማሪዎች ጋር የመተዋወቅ፣ ትስስርን የማጠናከር፣ ባህል እና ልምድ የመለዋወጥ አጋጣሚ እንደሚያገኙም ነው የተናገሩት፡፡ የጎንደር ሕዝብ ያደረገላቸው አቀባበልም በአካባቢው ያለምንም ስጋት አንደሚኖሩ መተማመን እንደጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

የመማር ማስተማሩ ሁኔታ የተሳካ እንዲሆን ቅድሚያ ለሰላም መስጠት ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ተማሪዎቹ የዩኒቨርሲቲውን አስተማማኝ ሰላም ለማስጠበቅ የራሳቸውን አሻራ እንደሚያሳርፉም አስታውቀዋል። በመሆኑም የተለያዬ የፖለቲካ ዓላማ በመያዝ፣ ብሔርን መሠረት በማድረግ እና ሌሎች ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከመገኘት ዓላማ ውጪ በመሆኑ ተገቢነት እንደሌለውም ነው አስተያት የሰጡት፡፡ የተማሪዎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም የዩኒቨርሲቲውን መተዳደሪያ ደንብ ማዕከል ባደረገ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የፖለቲከኞች አለመተማመን በተማሪዎች ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ ሊኖረው እንደማይገባም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትውልድ የሚቀረጽባቸው የፌዴራል መንግስት ሀብቶች እንጂ የፖለቲከኞች አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዳልሆኑ በመገንዘብ ትምህርት ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ኤፍሬም አብርሃም ከቅበላ ጀምሮ ተማሪዎች ያለምንም ስጋት ገብተው ትምህርታቸውን እንዲማሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል። የዩኒቨርሲቲው መሪዎች እና የተለያዩ የተማሪዎች አደረጃጀቶችም በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በተቋሙ ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ዝግጅት ማድረጋቸውን ነግሮናል።
ተማሪዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እና ኃላፊነት በጎደላቸው መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት በሚሰራጩ መሠረተ ቢስ መረጃዎች እንዳይሸበሩ ዩኒቨርሲቲው እንደሚያስገነዝብም ነው ተማሪ ኤፍሬም የተናገረው፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበኩር ጥቅምት 10-2012 ዕትም
Next article“የአማራ ሕዝብ የትግራይ ወንድምና እህቶቹን ይቅርና ድንበር አቋርጠው የሚመጡትን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ነው፡፡” ኤርትራውያን ተማሪዎች