
ባሕር ዳር: ነሐሤ 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ያ የጥበብ ምድር፣ ያ የረቀቀ፣ የጠለቀ የምስጢር አሻራ ማሳያ ምድር- ላስታ መድመቂያው እልፍ ነው።
እጅግ የገዘፈ የሰው ልጅ የጥበብ ከፍታ፣ የወርቃማ ሥልጣኔ ማኅደር፣ መልከ- ብዙ… ላስታ-ላልይበላ።
የዛኛው ዘመን ትውልድ ያስቀመጣቸው ህያው ታሪካዊ ቅርሶች ሁሌም አዲስ፣ የማያረጅ ውበት፣ የማይደረስበት ምስጢር፣ የማይደበዝዝ እውነት፣ የጥበብ ማኅደርነትን የታደለ ነው።
የላስታ ምድር መድመቂያው፣ መደመሚያው ብዙ ነው። በትውልድ ቅብብሎሽ የመጡ የሰው ልጆች ልዩ ልዩ ባሕላዊ እሴቶች ባለቤትም ነው ላስታ ላልይበላ። 
ወቅቱ ነውና የልጃገረዶች መድመቂያ ከኾነው አሸንድዬ ላይ እንደመም።
የላስታ ምድር ሌላኛው የታሪክ ገፅ…. “አሸንድዬ”
የላስታ ላል ይበላና አካባቢው ውብና ድንቅ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች መካከል አሸንድዬ ተጠቃሽ ነው።
በለመለመው የክረምት ወቅት የሚከበረው የልጃ ገረዶች የአሸንድዬ ባሕላዊ ጨዋታ ቀልብ ይሰርቃል፤ ልብ ይማርካል።
ተመሳሳይ አከባበር የተለያየ ስያሜ ያላቸው አሸንድዬ -በላስታ ላል ይበላና አካባቢው፣ ሻዳይ-በዋግኽምራና አካባቢው፣ ሶለል-በራያና አካባቢው የሚከበሩ በአማራ ክልል የነሐሴ ጌጦች ናቸው። 
ዲያቆን አዲሴ ደምሴ በላልይበላ ከተማ አሥተዳደርምክትል ከንቲባ እና የባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት  ኀላፊ ናቸው። የዘንድሮው አሸንድዬ በዓልን ከላስታ ወረዳ ጋር በመተባበር በማዕከል ደረጃ ይከበራል ብለዋል።
“አሽንድዬ ላስታ ላልይበላ የባሕል ግንባታ ለቱሪዝም ልማት” የሚል መሪ መልእክትም ተሰጥቶታል ነው ያሉት። 
ላስታዎቹ አሸንድዬን ዋናው የበዓሉ ምክንያት መነሻ የድንግል ማርያምን እርገት ምክንያት ያደርጉታል። አሸንድዬ ለምስጋና የሚከወን ሃይማኖታዊ ገጽታም ይሰጡታል ብለውናል። እናም ነሐሴ 16 አሸንድዬ በላስታዎቹ ምድር በድምቀት ይከበራል።
ዕለቱም  በቅዱስ ላልይበላ በካሕናት በወረብና በዝማሬ፣ ሰንበት ተማሪ ልጃገረዶች በአሸንድዬ ቅድስት ድንግል ማርያምን ያመሰግኑበታል።
የአሸንድዬ በዓል ስያሜውን የወሰደው ልጃገረዶች በወገባቸው ከሚጠመጥሙት የአሸንድዬ ቄጤማ ነው። 
ሴቶች በላስታ ወርቃማ ኮረብታዎች የሚበቅለውን ሣር መሰል ቀጤማ ቆርጠው በወጉ በመጎንጎን በወገባቸው ይታጠቁታል፤
“አሸንድዬ፣ አሸንዳ ሆይ
እሽ እርግፍ አትይም ወይ” በማለት   እጅግ ውብ የሆነውን ባሕላዊ ዜማ ያንቆረቁሩታል። 
አሸንድዬን የሚያከብሩ ሴቶች በዓሉ “የነፃነታችን ቀን ነው” ይሉታል። በአሸንድዬ በዓል ሴቶች በባሕላዊ መዋቢያ ይዋባሉ፤ ባሕላዊ አልባሳት ይለብሳሉ፤ ባሕላዊ ዘፈኖችና እና ጭፈራዎች እያቀረቡ ደምቀው ይታያሉ።
ልጃ ገረዶች በአሸንድዬ ደስታቸውን፣ ጨዋታቸውን፣ ፍቅራቸውን በነጻነት ይገልጹበታል። አሸንድዬ የነጻነት ምሳሌ ሃሳብን በነጻነት፣ ማኅበራዊ ሂስን በነጻነት የሚገለጽበት የልጃገረዶች ውብ በዓል። የአብሮነት ማሳያ፣ የሞራል ግንባታ ማሳያ ነው፤ ክብር፣ ፍቅር፣ መቻቻል፣ ትብብር ይጎላበታል፡፡
በአሸንድዬ ወቅት ልጃገረዶች አምረውና አሸብርቀው የሚታዩት ነሐሴ ሲገባ ጀምረው ነው። ልጃገረዶች እርስ በእርስ እየተገናኙ በየእድሜ እርከናቸው ከአቻዎቻቸው ጋር ቡድን መስርተው የአሸንድዬው ቀን ነሐሴ 16 እስኪደርስ ድረስ ልባቸው ስቅል ብሎ ይከርማል። ሴቶች በየእድሜ ደረጃቸው ከነሐሴ 1 ጀምሮ ይዘጋጃሉ። የተጣሉ ይቅርታን ያወርዳሉ፤ አለቃ ይመርጣሉ። ያለው አዲስ ገዝቶ ካልሆነ ያለውን አጥቦ ይዘጋጃል፤ የመዋብ ሥራው ይቀጥላል፤ የፀጉሩ አሠራርና አጊያጊያጥ በመልኩ ይከወናሉ።
በነሐሴ በ15ኛው ቀን ተራሮች የለገሱትን አሸንድዬን ለመቁረጥ ወጣቶች ወደተራሮች ይወጣሉ፤ ይቆርጣሉ፤ የአሸንድዬ ቅጠሉን ጫፎቹን እርስ በርስ በማያያዝ ይጎነጉናሉ፤ የተፈለቀቀ ጥጥ የሚመስለው የአሸንድዬው ታችኛው ክፍልም እጅግ ባማረ መልኩ ይዘጋጃል።
በቅድመ ዝግጅቱ የጸጉር መሠሪያ፣ የመዋቢያ፣ የማጌጫ ቁሳቁስ እንደ ኩል፣ ልብስ፣ ጌጣጌጦች እና ሌሎችም ቅድመ ዝግጅቶች ይከወናሉ። በዓሉ መቃረቢያ ኩል መኳል፣ ጸጉር መሠራት፣ መዋብ ይጀመራል። የጸጉር ሥሬቱ እንደየ እድሜ ክልላቸው የልጆች፣ የወጣቶች እና የእናቶች ይፈረጃል።
ለልጆች ጋሜና ቁንጮ፤ ለወጣቶች ቅልስ፤ ለአገቡና ለወለዱት ግልብጭ፣ አፈሳሶ የጸጉር ሥሬትን ይሠራሉ። 
ከአዘቦት ቀን በተለየ እንደየእድሜ እኩዮቻቸው የሚደምቁበት ቀን ነው አሸንድዬ ለላስታዎቹ።
ያገቡት በድሪ፣ ብቻ መስቀሉም፣ አምባሩም እንደየ አድሜያቸው ይዋቡበታል። የበዓሉ ዕለት ጠዋት ልጃገረዶች የተዘጋጀውን ጉንጉን የአሸንድዬ ቅጠል በወገባቸው ያስራሉ፤ ሌላ ውበት። 
ዲያቆን አዲሴ እንዳብራሩት ልጃገረዶች እንደየ ሁኔታውና ባሕሉ ይገጥማሉ፤ ያዜማሉ።
ለሃይማኖታዊ ሁነቶች  ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ግጥሞች ይገጥማሉ፤ ወደ ታላላቆች ደጅ ጎራ ብለው ደግሞም እማወራዋንና አባወራውን  ያወድሳሉ፤ ያሞጋግሳሉ።
የአሸንድየ ክዋኔ ነሐሴ 16 በቤተ ክርስቲያን ይጀመራል፤ በሃይማኖታዊ  ምስጋናዎች…
“ተወረወረች ኮከብ፤
ተወረወረች ኮከብ፣
በጊዮርጊስ ክበብ”…. እና ሌሎችንም ሥነ-ግጥሞች በመደርደር በዓሉን እጅግ ባማረ መልኩ ይከውናሉ።  
“እንደ ነአኩተለአብ እንደላልይበላ፤
ቤት ሠራች ይሉኛል ዲንጋዩን ፈልፍላ፤
ዲንጋዩን ፈልፍላ የሠራችው ቤት፤
አልባብ አልባብ ይላል ማርያም ገብታበት፡፡
ማርያም የገባችለት  ስለቴ ሰመረ ፤
እንግዲህ መባዘን መንከራተት ቀረ..” 
አሸንድዬ ከቤተ ክርስቲያን መልስ በእድሜ የገፉ ታላላቅ ሰዎች ቤት የበዓሉ ክዋኔ ይቀጥላል….የሥነ-ግጥም ድርደራውም እንደየ በዓሉ የሚከወንበት ቦታ የሚለይ ቢሆንም፤
” አስገባኝ በረኛ…አስገባኝ ከልካይ  እመቤቴን ላይ፣
ጌታዬ አሉ ወይ…
አሉ  እንጅ  አሉ እንጂ፤
ግቡ ይላሉ እንጅ፤
ተዘንብሏል ጠጅ…” እያሉ ግጥም ከዜማ  ተዋህዶ በልጃገረዶች ውብ ድምጽ ይንቀረቆራል። 
በአሸንድዬ ልጃ ገረዶች በግጥሞቻቸው በማወደስ እንዴት ከረማችሁ ከሚለው መልዕክት ባለፈ ትልቅን ማክበር የሚታይበት ድንቅ የበዓል አከዋወን ነው።
በዓሉ በሌላ መልኩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሰነፍ የሚተችበት፣ ጠንካራው በበጎ የሚወደስበት መልከ ብዙ ሥነ-ግጥሞች የሚከወኑበትም ነው። 
አሸንድዬ ነገን አብሮ ለመኖር ወጣቶች እርስ በርስ የሚፈቃቀዱበትና ተስፋን የሚሰነቁበት ነው።
አሸንድዬ ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ነው ያለው  ይላሉ ዲያቆን አዲሴ፤ ለላስታዎቹ  “አሸንድዬ ባሕልና ታሪክ ብቻ አይደለም፤ መልከ ብዙ ነው። የአብሮነት መስተጋብራችን  የሚገለጽበት፣ የኢኮኖሚ ምንጭም ጭምር ነው” ይሉታል። 
በመሆኑም ባሕሉን ማጠናከርና ካሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ሌላኛው መስህብ ማድረግ ያስፈልጋል።
በዘንድሮው የአሸንድየ ዝግጅትም የፓናል ውይይቶች፣ የአደባባይ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት ተጠናቆ እንግዶችን እየተጠባበቅን ነው ብለዋል ዲያቆን አዲሴ።
በዕለቱ አባቶች እናቶች  ታሪካዊ ትውፊቱን፣ ሃይማኖታዊ እሳቤውንም ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሻግሩ፣ አሸንድዬን የሚያከብሩ ልጃገረዶችን ያመሰግናሉ፤ ይመርቃሉ፤ ይሸልማሉ፡፡
መልካም ምኞታቸውንም በከርሞሰው ይበለን ምርቃት ከዓመት ዓመት ያድርሳችሁ ይሏቸዋል። 
ከምርቃት እስከ ስጦታ የተቸሩት ልጃገረዶችም ” አሜን መጠን አንጣችሁ፣ በሰላም ያድርሳችሁ ያድርሰን” ግብረመልስ ነው።
ኑ! ይላሉ ላስታዎች  አሸንድዬን በላስታ ቅዱስ ላል ይበላ ያክብሩ፤ የልጃገረዶች ተሰምቶ የማይጠገብ ዝማሬ፣ ታይቶ የማይረሳ ጨዋታን ይካፈላሉ። 
ከልጃገረዶች ዝግጅት በተጨማሪም የደብረ ሮሃ ሊቃውንት የሚያካሂዱት ልዩ ወረብ፣ የሰንበት ተማሪዎች በመንፈሳዊ ይዘት በአሸንድዬ እመቤታችን ሲያመሰግኑ ይካፈሉ ብለዋል።
እግረመንገድዎንም አስደናቂዎችን የላልይ በላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጉብኝት ያደርጋሉ።
ከገዘፈው የሰው ልጅ የጥበብ ከፍታ፣ ከወርቃማ ትውልድ የሥልጣኔ ማኅደር፣ ያን ህያው የታሪክ  አሻራ በአሸንድዬ ታደሙ የኛም ግብዣ ነው። 
መልካም የአሸንድየ በዓል!
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
            
		