የሻደይ፣ የአሸንድዬ እና ሶለል በዓላትን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

211

ባሕር ዳር: ነሐሤ 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጎብኚዎች ትክክለኛ እሴታቸውን ጠብቀው በሚከበሩት እነዚህ በዓላት ላይ እንዲታደሙም ጥሪ ቀርቧል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ምክንያት ደብዝዘው ያለፉት በዓላቱ ዘንድሮ በቀደመ ክብራቸው ልክ ይከበራሉ ተብሏል፡፡ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ይዘት ያላቸው የሻደይ፣ የአሸንድዬ፣ ሶለል፣ የቡሔ እና የእንግጫ ነቀላ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ነው ቢሮው ያሳወቀው፡፡
ሻደይ-በዋግ ኽምራ፣ ሶለል-በራያ፣ አሸንድዬ-በላስታ ላል ይበላ የልጃገረዶች የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾኑ ለማስቻል ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡
የሻደይ በዓል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከነሐሴ 16 እስከ 21/2014 ዓ.ም በድምቀት እንደሚከበር የብሔረሰብ አስተዳደሩ ኮምዩኒኬሽን አሳውቋል፡፡
በዓሉ ከጨዋታና ክዋኔ ባሻገርም የቋንቋና የባሕል ሲፖዝዬም ይካሄዳል ብሏል። በዋግ ኽምራ የሻዳይ በዓል ሁሉንም ሁነት በየፈርጁ ባሕላዊ ሥርዓትን ተከትሎ የሚከወን ይኾናል ተብሏል፡፡
እንደ ላልይበላ ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ አሸንድዬን ከነሐሴ 16 እስከ 18/2014 ዓ.ም በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ደብረ ሮሃ እንግዶቿን በአግባቡ ተቀብላ በቀደመው የእንግዳ አቀባበል ባሕሏ ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች። “ይምጡ አሸንድዬን በላስታ-ላልይበላ ያክብሩ” የሚል ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የዘንድሮውን የአሸንድዬ በዓል የላልይበላ ከተማ አስተዳደር እና ላስታ ወረዳ በጋራ በልዩ ሁኔታ ለማክበር ግብረ ኀይል ተዋቅሮ እየተሠራ መሆኑን ነው የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ የተናገሩት፡፡
በራያ ቆቦ ደግሞ ሶለል በዓልን ከነሐሴ 15 እስከ 18 /2014 ዓ.ም “ሶለልን በግንባር ለድልና ለነጻነት” በሚል መሪ መልእክት በደማቅ ሁኔታ እንደሚያከብር አሳውቋል፡፡ በዓሉን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ራያ ቆቦ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል ተቋማትና የሙያተኞች ብቃት ማረጋገጥ ባለሙያ አቶ አዲሱ ታምሩ በሰጡን መረጃም የሻደይ፣ የአሸንድዬ፣ ሶለል በዓላት የአከባበር መርሃግብር ይፋ ኾኗል፡፡
በዚህ መሰረትም ነሐሴ 16 በዋናነት በዞን ደረጃ እና በየወረዳዎቹ ይከበራል፤ በ21 ደግሞ ባሕር ዳር ላይ በክልል ደረጃ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ይከበራል ብለዋል፡፡
የመጨረሻው ማጠቃለያ መርሃ ግብር ደግሞ በ28 አዲስ አበባ ላይ በመስቀል አደባባይ በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡
ይህም በዓላቱን ከማክበር ባሻገር ባሕሉ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲሻገር የማስተዋወቅ፣ በክልሉ በጦርነት እና በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ተቀዛቅዞ የነበረውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ታልሞ እየተሠራ መኾኑን አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡
አቶ አዲሱ ታምሩ እንደገለጹት ሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል በዓላትን በዩኒስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደቀጠለም ነው፡፡
በዓላቱ እሴታቸውን እንደጠበቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩም ብዙኃን መገኛን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና የማሻገር ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል እቶ አዲሱ፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኩር ጋዜጣ – ነሐሤ 09/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተለያዩ ሹመቶችን ሰጥተዋል።