
ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ሀገርን አረንጓዴ እያደረጉ ያሉ እጆች” በሚል ርዕስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉዳዩን የተመለከቱ ጉባዔዎች እና ስብሰባዎች ከማድረግ ያለፈ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሳስበዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ለኾነችው አፍሪካ የሚበጀው ችግሩን ማውራት ሳይኾን እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ባሉ መፍትሔ አምጪ ሥራዎች ላይ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ ነውም ብለዋል።
በቅርብ ጊዜያት ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተለያዩ ክስተቶችን እያስተናገደች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ጎርፍ፣ ሰደድ እሳት፣ የሙቀት መጨመር፣ የበረሃማነት መስፋፋት እና ሌሎችም ችግሮች ዓለምን ለአሳሳቢ ኹኔታ እንደዳረጓት ተናግረዋል።
ምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው ድርቅ እንዳጋጠማቸውና በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎችም የከፋ ድርቅ ማስከተሉን አመልክተዋል።
ለበርካታ ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ የተመለከቱ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ መቆየታቸውን አንስተዋል። አሁን ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ያለበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
“ከጉባዔዎች እና ስብስባዎች ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥ ላመጣብን ፈተና መፍትሔ የሚኾን ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ችግሩን ለመከላከል በኹሉም ደረጃ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፤ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ስኬታማ ሥራ ማከናወን እንደቻለች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 በተፋሰሱ ሀገራት በጎ ተጽእኖ ለማምጣት፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ ከተማን አረንጓዴ ማልበስ እና ሌሎች ተያያዥ ውጤቶችን ለማምጣት አረንጓዴ ዐሻራን መጀመሯን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሱት።
በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በመርሐ ግብሩ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቀዶ 25 ቢሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉንና ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ የደን መመናመንን በመቀነስ፣ አዲስ የደን ሽፋን በመፍጠር እና የአየር ንበረትን ለውጥ ከመከላከል አኳያ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።
የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መብዛት፣ የችግኝ መትከያ ቦታዎችን ቀድሞ መለየት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት አረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማ እንዲኾን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
ቀጣዩ ትውልድ የችግኙን ፍሬ እንደሚያይ ምንም ጥርጣሬ የለኝም ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ከአረንጓዴ ዐሻራ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኀይልን ወደ መጠቀም እየተሸጋገረች እንደምትገኝና ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መፍትሔ እንደሚኾን አመላክተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ሥራቸው እንደ ተሞክሮ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
❝ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች❞ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
