“ውበትና ፍቅር በወሎ ሰማይ ሥር”

461

ባሕር ዳር: ነሐሤ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ውበት እንደ ዥረት ይፈስስበታል፣ ደግነት ሞልቶበታል፣ ፍቅር ተወልዶ አድጎበታል፣ አድጎ ጎምርቶበታል፣ በደግነት ያቅፋሉ፣ በፍቅር ይቀበላሉ፣ በተድላ ያኖራሉ፡፡ የጨነቀውን ያረጋጉታል፣ የደከመውን ያሳርፉታል፣ የራበውን ያጎርሱታል፣ የጠማውን ያጠጡታል፣ የታረዘውን ያለብሱታል፡፡
በመስጂድ ሳይቋረጥ ሶላት ይሰገድበታል፣ አዛን ይደረስበታል፣ አላህ ለምድር ጸጋና በረከትን ይሰጥ ዘንድ ዱዓ ይደረስበታል።
በቤተክርስቲያኑ ኪዳን ይደረሳል፣ ቅዳሴ ይቀደሳል፣ ሰዓታቱ፣ ማሕሌቱ ሳይታጎል ይቆማል፣ እግዚአብሔር ምድሯን ይባርካት፣ ሰላምና ፍቅር ይሰጣት ዘንድ ጸሎት ይደረስበታል፡፡ አበው ይማጸናሉ፣ እያለቀሱ ለምድር ጸጋና በረከትን ይለምናሉ፡፡ በደግነት የለመኑትን፣ በትሕትና የጠየቁትን የማይነሰው አምላክ የሻቱትን ይሰጣቸዋል፣ ፍቅርና በረከት ያድላቸዋል፡፡
ሼሁና ቄሱ በአንድ ማዕድ ይበላሉ፣ ስሞት አፈር ስሆን እየተባባሉ ይጎራረሳሉ፣ ወሎ ውስጥ ፍቅር የይመሰል አይደለችም፣ ትናንት የነበረች፣ ዛሬም ያለች፣ ነገም የምትኖር ወሎዬዎች የተጋመዱባት፣ የተሳሰሩባት ጥበብ ናት እንጂ፡፡ ልብን በሚያርደው አንደበታቸው፣ ከዘመን ዘመን በማይቀንሰው ፍቅራቸው፣ በከፋም ባመረም ዘመን በማይጎድለው ደግነታቸው ይቀናባቸዋል፣ ያላያቸው ይናፍቃቸዋል፣ ያያቸው ይሳሳላቸዋል፡፡
ወሎን የረገጠ ሁሉ በደስታ ባሕር ውስጥ ይጠልቃል፣ በደግነት ውቅያኖስ ይዋጣል፣ በውበታቸው ይዋባል፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ውበትን፣ ጽናትን፣ ደግነትን፣ መልካምነትንና ሰውነትን ውሎ ውስጥ ያያል፡፡
በአራቱ ቅኝታቸው፣ ልብን እያረሰረሰ በሚፈስሰው ለዛቸው ጨዋታ ያነሱ ጊዜ ምነዋ ወሎ ባልወጣሁ ያስብላሉ፡፡ ቢሻቸው በአንበሳል፣ ቢሻቸው በባቲ፣ ቢሻቸው በአንቺኾዬ፣ ቢሻቸው በትዝታ ቅኝት እየቃኙ ጥበብን ያፈስሳሉ፣ ስንኝ እየቋጠሩ የሰውን ልብ በፍቅር ያስራሉ፣ በትዝታ ያስሄዳሉ፡፡ በናፍቆት ያንገበግባሉ፡፡
ወረኃ ነሐሴ ደርሷል፣ ተራራዎች በአረንጓዴ ካባ ተሸፍነዋል፣ ጉሙ በተራራዎች አናት ላይ እየተጎተተ ነው፡፡ ጉልበት ያልነበራቸው ምንጮች አጎልብተዋል፣ ቅጠል ያልነበራቸው ዛፎች ተውበዋል፣ የደረቁት ሜዳዎቸ ለምልመዋል፣ በሬዎች ግጦሽ ግጠው ጠግበዋል፣ ላሞች ወተት ሰጥተዋል፣ ክረምት ነውና ሁሉም መልካም ኾኗል፡፡
በወረኃ ነሐሴ በወሎ ሰማይ ሥር ድንቅ ነገር ይደረጋል፡፡ ወይዛዝርቱ መዋብ ጀምረዋል፣ ጋሜና ሳዱላቸውን እያሳመሩ፣ ሹርባቸውን ባማረ ጌጥ እየተሠሩ ነው፡፡
ጎበዛዝቱ ጎፈሬያቸውን እየነቀሱ፣ ኩታቸውን እያሳመሩ፣ እረኞች ጉደሯቸውን እያስዋቡ ነው፡፡ ለምን ካሉ አሸንድዬ ደርሷልና፡፡
ወይዛዝርቱ አምረውና ተውበው ደስታ የሚያዩበት፣ ፍቅር እና አንድነት የሚያሳዩበት፣ የኖረውን ባሕል የሚያስቀጥሉበት ነውና ወረኃ ነሐሴ በጉጉት ትጠበቃለች፡፡ አንደኛው ከሌላው ልቆ ለመገኘት እሽቅድድሙ፣ ማመሩና መዋቡ አጀብ ያሰኛል፡፡
አሸንድዬን ተጫውታ አድጋለች፣ ወረኃ ነሐሴ በገባ ቁጥር የተጫወተችው ጨዋታ፣ የአበው ምርቃት፣ የአብሮ አደጎቿ ፍቅርና ውበት ውል ይሉባታል፡፡ በማለዳ ተነስተው ወደ ተራራ ወጥተው፣ አሸንድዬ አምጥተው፣ ባመረው ወገባቸው ዙሪያ አሸንድዬውን አስውበው የሚጫወቱት፣ ከአበው የሚመረቁት ምርቃት እና መልካም ምኞት ድቅን ይልባታል፡፡ እንኳን ተጫውቶ ላደገው ይቅርና በአሻገር ላየውስ ውል ማለቱ መች ይቀራል፡፡
ውበት የሚታይበት፣ ነጻነት ያለበት፣ ፍቅርና ተድላ የመላበት ነውና ይናፈቃል፣ አሸንድዬን አብዝታ ትናፍቀዋለች፣ ዛሬም በጉጉት ትጠብቀዋለች፡፡
ትውልድና እድገቷ ወሎ መቄት ሀገረ ገነት ኪዳነ ምህረት ነው፡፡ በሀገረ ገነት ኪዳነ ምህረት ኮረብታማ ስፍራዎች እየተመላለሰች አዚማለች፣ ከአብሮ አደጎቿ ጋር ተጫውታለች፣ በወረኃ ነሐሴ አሸንድዬ እያለች በቀየው ተመላልሳለች፣ በሀገርኛ ዜማ አዚማለች፣ በሀገርኛው ውበት አጊጣለች ድምጻዊት ማዲቱ ወዳይ( እሽክም)፡፡
እሽክም ብላ አዚማለች፣ ወረሀቡል ብላ ተቀኝታለች፣ የአሸንድዬ ትዝታዎቿ አሁንም ድረስ አብረዋት አሉ፡፡ በልጅነት እድሜዋ ማንነቷን የቀረጸችበት፣ ተውባና አጊጣ ያደገችበት ነውና ከእርሷ አይለይም፡፡ አሸንድዬ ብዙ ነገር ነው፣ አሸንድዬ ድንቅ ሃብት ነው ትላለች ድምጻዊቷ፡፡ ወይዛዝርቱ የሚጫወቱት፣ ያገቡና ያላገቡት የሚያጌጡበት፣ እረኞች የሚያደርጉት፣ ጎበዛዝቱ የሚከውኑት ሁሉ ያለ ምክንያት የሆነ የለም ነው የምትለው፡፡
ሁሉም በምክንያት ይሆናል፣ ሁሉም በመክንያት ይዋባል፣ መዋቢያው፣ የሚባለው እና የሚደረገው ሁሉ ትርጉም እንዳለው ነው የነገረችኝ፡፡ በልጅነት ዘመኗ በመቄት ሀገረ ገነት ኪዳነ ምህረት ያሳለፈችውን ስታስታውስ “በማለዳ ወጥተን አሸንድዬ ለማምጣት እንሄዳለን፣ አሸንድዬ በሐምሌ በተለይም በነሐሴ ነው የሚበቅለው፣ እንዳይደርቅ በጠዋት ነው ተነስተን የምንሔደው፣ አሸንድዬ በሚከበርበት ሳምንት ሌላ ሥራ አንታዘዝም፣ አሸንድዬ እንቆርጣለን፣ በእርሱ እንዋባለን፣ በመጀመሪያ ወደ ቤተክርስቲያን እንሄዳለን፣ ከዚያም በየቤቱ እየሄድን እንጫወታለን” ነው ያለችኝ ድምጻዊት ማዲቱ፡፡
ወይዛዝርቱ አምረውና ተውበው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ያመራሉ፣ በአጸዱ ዙሪያ እጅ እየነሱ ይሰግዳሉ፣ ይጸልያሉ፣ በአበውም ይባረካሉ፣ ይመረቃሉ፡፡ በረከትና ምርቃት ይዘው ወደ ቀየው ይመለሳሉ፡፡ እረኞች ልጃገረዶቹ ሊመጡ ነውና ውሾችን ያሥራሉ፣ ወይንም ቆመው ይከላከላሉ፡፡ ልጃገረዶችም እረኞቹ ወይም ጎበዛዝቱ ውሾቹን እንዲያስሩላቸው፣ ከአደጋ እንዲጠብቋቸው እያዜሙ ይመጣሉ፡፡ ዜማውን የሰሙት እረኞችም የተባሉትን ያደርጋሉ፣ በንቃት ይጠብቃሉ፡፡
ይህ በዓል ወይዛዝርቱ በነጻነት የሚመላለሱበት፣ በነጻነት ውበታቸውን የሚያሳዩበት ነውና እንደ ነጻነት ጊዜም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ውብ ልጆች፣ በውብ ባሕል፣ በውብ ሀገር ይዋባሉ፡፡ በውብ ጥበብ ይደምቃሉ፡፡ በዚሁ ሰሞን ባል አግብተው ከቀየው የወጡ ሴት ልጆች ተጠርተው ወደ ወላጆቻቸው ይመጣሉ፡፡ ጠላው ይጠመቃል፣ እንጀራው ይጋገራል፣ ሙክቱ ይታረዳል፣ ወጡ ይሠራል፣ ባሎቻቸውን ይዘው የመጡ ሴቶች በቀያቸው የደስታ ጊዜ ያሳልፋሉ ነው ያለችኝ ማዲቱ፡፡ ፍልሰታ ከተፈታች በኋላ ያለው ሳምንት የደስታና የፍቅር ነው፡፡
የማሳውን ሰብል ከጦጣና ከዝንጀሮ የሚጠብቁት፣ ላምና በሬዎች፣ ፍየልና በጎችን የሚያግዱት እረኞች በዚሕ ሰሞን ደስታቸው ልክ የለውም፡፡ ወይዛዝርቱም እንዲሁ፡፡ አሸንድዬ ልዩ ልዩ ዜማዎች ያሉት፣ ውበት የሚገለጥበት፣ አንድነትና ፍቅር የሚታይበት እንደሆነም ነግራኛለች፡፡ ዘመናትን የተሻገረውን፣ ማንነትን የሚገልጸውን ታላቁን በዓል በማስተዋወቅና በመጠበቅ በኩል ግን ክፍተት መኖሩንም ድምጻዊቷ ተናግራለች፡፡
በልጃገረዶች ወገብ የሚውለው አሸንድዬ፣ የሚዜማው ዜማ፣ መዋቢያው ሁሉ ምክንያትና ትርጉም ያለው መሆኑን የምትናገረው ድምጻዊት ማዲቱ አሁን አሁን ምክንያቶቹን እና ትርጉሞችን አውቆ የሚተገብራቸው እየጠፋ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ሁሉም በሰፊው ሊሠራበት እንደሚገባም ገልጻለች፡፡
ድምጻዊት ማዲቱ ወዳይ ያደገችበትን የአሸንድዬን፣ የሶለልንና የሻዴዬን በዓል የሚያስተዋውቅ የጥበብ ሥራ መሥራቷንም ተናግራለች፡፡ በዓላቱን በትክክለኛው የሚገልጹ ሥራዎችን ለመስራት አድካሚ መሆኑን የገለጸችው ድምጻዊቷ በዓሉ እንዲተዋወቅ የሚደረገው ድጋፍ አናሳ መሆኑንም ተናግራለች፡፡ እርሷ ግን በአንድ ሥራ ብቻ እንደማታቆምና በዓላቱን የሚገልጹ ተከታታይ ሥራዎች እንደሚኖሯት ነግራኛለች፡፡ በዓላቱ ሳይበረዙ እንዲተዋወቁ ለሚጥሩት ድጋፍ ሊቸራቸው እንደሚገባም ገልጻለች፡፡
ኢትዮጵያ የምትታወቅበት፣ ዜጎችን የምትስብበት፣ ውበትና እና ማንነት የሚገለጽበት በዓል ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግራለች፡፡ በዓላቱ የሚከበሩበት ነሐሴ ወር ሲመጣ ብቻ ሳይሆን በሌላው ጊዜ ትውልድ እንዲያውቃቸው፣ አውቆ እንዲጠብቃቸው፣ እንዳይበርዛቸው እና እንዳይከልሳቸው መደረግ እንደሚገባውም ገልጻለች፡፡
ወረኃ ነሐሴ ደርሷል፡፡ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ ከየቀያቸው ሊሰባሰቡ ነው፡፡ ጎደናዎች በሚያማምሩ ሰዎች ሊሞሉ ነው፡፡ በዋግኸምራ ሻዳይን፣ በራያ ሶለልን፣ በመቄት፣ በላስታና በሌሎች አካባቢዎች አሸንድዬን የሚያከብሩት ወይዛዝርትና ጎበዛዝት አካበቢውን ያስውቡታል፡፡ በአሻገር ገና ያስቀናሉ፣ በአሻገር የሚመለከታቸውን ምነው ከእነርሱ ጋር ባኖረኝ ያስባለሉ፡፡
ውበትና ፍቅርን በወሎ ሰማይ ሥር ይመልከቱ፡፡ ተመልክተው ያድንቁ፡፡ የቆውን ባሕል አይተው ይደነቁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article#ሻደይ_አሸንድዬ_ሶለልና_ቡሄ_2014_ዓ.ም
Next article❝ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)