
ከሰሞኑ በክልላችን ክብረ በዓላትን የት ለማክበር አስበዋል?
የአማራ ክልል ሕዝብ እጅግ ውብ፣ በርካታ እና የተለያዩ ባህላዊ ትውፊት ያለው ሕዝብ ነው። ታዲያ ከሰሞኑ የአማራን ክልል ሕዝብ ባህልና ዕሴት የሚገልፁ የተለያዩ ክብረ በዓላት ከነሐሴ 12 እስከ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች የሚከበሩ ድንቅ ክብረ በዓላት አሉ።
እርስዎም በቦታው በመገኘት የዚህ እጅግ ውብና ማራኪ እንዲሁም ትውፊታዊ በዓል ታዳሚ እንዲኾኑ በአክብሮት ተጋብዘዋል፡፡
የክብረ በዓላቱ መርሐ ግብሮች፦
1.  ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር
የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት የሚከበር ልዩና ሃይማኖታዊ ትውፊት ያለው በዓል ነው። በዓሉ ነሐሴ 12 በሚካሄድ ደማቅ የዋዜማ ዝግጅት ይጀምራል፡፡ በዋዜማ ዝግጅቱ የቡሄ እና አሸንድዬ የሚጫወቱ ልጃገረዶች በደብረ ታቦር ከተማ ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር የእንኳን አደረሰን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡
ነሐሴ 13 ረፋድ ጀምሮ የቡሄ በዓል በታላቁ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ገዳም የሚከበር ሲኾን በሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን የጠበቀ ወረብ እንዲሁም ታዳጊዎች እና ልጃገረዶች ቱባውን የቡሄ ጨዋታ የሚያሳዩ ይኾናል፡፡ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ሰለቡሄና አሸንድዬ ምሁራን የሚሳተፉበት ታላቅ ጉባዔ ይካሄዳል፡፡
2.  የሻደይ በዓል በሰቆጣ ከተማ
የሻደይ በዓል ከአማራ ክልል ቱባና ትውፊታዊ ባህሎች አንዱ ሲኾን በልጃ ገረዶች የሚከበር ልዩና ደማቅ በዓል ነው። በዓሉ በኹሉም የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሚገኙ ወረዳዎች ሲከበር ከቆየ በኋላ “ሻደይ ኢትዮጵያ ለነጻነትና ለድል!” በሚል መሪ መልዕክት ከነሐሴ 15-18 በዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል፡፡ በሰቆጣ ከሻደይ ጨዋታ በተጓዳኝ ባህላዊ የቁንጅና ውድድር፣ የቋንቋና ባህል ጉባዔ እና የንግድ ትርዒት የሚካሄዱ ይኾናል፡፡

በዋናነት ነሐሴ 16 የሚከበረው የሻደይ በዓል የጠዋትና ከሰዓት መርሐ ግብሮች ይኖሩታል፡፡
በጠዋት መርሐ ግብር የሻደይ በዓል ከሰቆጣ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይከበራል፡፡ በዚህም ከሻደይ ጨዋታው ጎን ለጎን በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠራችው የውቅር መስቀለ ክርስቶስ በእንግዶች ትጎበኛለች፡፡
የጠዋቱ መርሐ ግብር እንደተጠናቀቀ በዋግሹም ወሰን ሰገድ ትምህርት ቤት በተዘጋጀ አደባባይ ልጃገረዶች ታይቶ የማይጠገብ የሻደይ ጨዋታዎችን ለታዳሚዎች ያቀርባሉ፡፡ እርስዎም በቦታው በመገኘት በዚህ በዓይነቱ ለየት ባለው በዓል ላይ እንዲታደሙ በአክብሮት ተጋብዘዋል።
3.  የአሸንድዬ በዓል በላልይበላ ከተማ
የአሸንድዬ በዓል በላስታ ላልይበላ በልዩ ዝግጅት የሚከበር ውብ በዓል ነው። በዓሉ ከነሐሴ 15-17 በልዩ ድምቀት የሚከበር ሲኾን የላልይበላን የአሸንድዬ በዓል ነሐሴ 15 በተለያዩ ትርዒቶች ይጀመራል፡፡ ነሐሴ 16 ደግሞ የላስታ ላልይበላ ልጃገረዶችና ታዳጊ ወጣቶች በአስደናቂዎቹ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥር ተሰምቶ የማይጠገብ ዝማሬ እያሰሙ የአሸንድዬ በዓልን ያከብራሉ፡፡
ነሐሴ 17 የአሸንድዬ በዓል በታዳሚዎች ፊት በአደባባይ ይከበራል፡፡ በዕለቱ ከአሸንድዬ ጨዋታ በተጨማሪ የቅዱስ ላልይበላ ሊቃውንት ልዩ ወረብ ለበዓሉ ታዳሚዎች የሚቀርብ ይኾናል፡፡ እርስዎም በቦታው በመገኘት የዚህ ውብና አስደማሚ በዓል ታዳሚ ይኹኑ።

4.  የሶለል በዓል በቆቦ ከተማ
ሶለል በሻደይና አሸንድዬ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የራያ ልጃገረዶች የነጻነት በዓል ነው፡፡በዓሉ “ሶለልን በግንባር ለድልና ለነጻነት!” በሚል መሪ መልዕክት ከዋዜማው ነሐሴ 15 ጀምሮ መከበር የሚጀምር ይኾናል፡፡ ነሐሴ 16 በቆቦ ከተማ በሚከበረው ሶለል በዓል የራያ ልጃገረዶች ጨዋታቸውን የሚያሳዩ ሲኾን የጎረምሶች ጅራፍ ግርፊያ ትዕይንትን ጨምሮ ራያን የሚገልጹ ተጨማሪ ባህላዊ ዝግጅቶች በዕለቱ የሚቀርቡ ይኾናል፡፡
5.  የአሸንድዬና ሶለል በዓል በወልድያ ከተማ
የአሸንድዬ በዓል ከላስታና ላልይበላ በተጨማሪ በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በስፋት የሚከበር ደማቅ በዓል ነው፡፡ ይሄን በዓል ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት የአንድነት መንፈስን ለማሳደግ ለመጀመሪያ ጊዜ በዞን ደረጃ ነሐሴ 19 የአሸንድዬ-ሶለል በዓል በወልድያ ከተማ በልዩ ኹኔታ የሚከበር ይኾናል፡፡
እርስዎም በቦታው በመገኘት የነዚህ ውብ በዓላት ታዳሚ ይኹኑ። የአማራን ክልል ሕዝብ የተለያዩ ባህሎችና ዕሴቶችን ይመልከቱ። በክብርና በፍቅር ልናስተናግዳችሁ – ልናስደስታችሁ ተዘጋጅተናል! ይምጡ! የማይረሳ ጊዜን በአማራ ክልል ያሳልፉ!
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
            
		