‟ከወልቃይት ጠገዴ ወንድሞቻችን ጋር የሚያገናኘን የአሥፓልት መንገድ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው” የአጅሬ ጃኖራ ነዋሪዎች

304

ደባርቅ፡ ነሐሴ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በሰሜን ጎንደር ዞን እየሠራቸው ከሚገኙ መንገዶች መካከል ከዳባት – አጅሬ – ጠገዴና ማክሰኞ ገበያ እየተሠራ የሚገኘው የአሥፓልት መንገድ ተጠቃሽ ነው።

99 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ይህ የአሥፓልት መንገድ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከዳባት – አጅሬ – ጠገዴና ማክሰኞ ገበያ ከሁለት ተከፍሎ ፓወር ኮን በተባለ ተቋራጭ እየተሠራ ይገኛል። መንገዱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚሰጥ ነው።

በዳባት ወረዳ የአጅሬ ጃኖራ አካባቢ ነዋሪው አቶ ማሙሽ ከፍያለው “የመንገድ አለመኖር እናቶች በወሊድ ምክንያት በመንገድ ላይ እንዲቀሩ፤ ምርት ለገበያ እንዳይቀርብ፤ ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በክፉም በደጉም እንዳንገናኝ አድርጎን ቆይቷል”ብለዋል።

የአሥፓልት መንገዱ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው ለመንገድ ሥራው ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነ አስረድተዋል።

አቶ ረዲ ዳውድ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው መንገዱ ብዙ መስዋእትነት ተከፍሎ ወደ ቀደመ ማንነቱ ከተመለሰው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ኅብረተሰብ ጋር የሚያገናኝ መኾኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል። የመሬት ካሣ ክፍያዎችም በጊዜ እንዲፈጸሙ ጠይቀዋል፡፡

የዳባት አጅሬ ጠገዴና ቅራቅር አሥፓልት መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ አዲሱ ጌታሁን፤ የአሥፓልት መንገድ ሥራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸው የመንገድ ቆረጣና የማገናኘት ሥራው 80 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።

የሲሚንቶና የነዳጅ እጥረት ለሥራው ማነቆ እንደኾነባቸው የጠቆሙት ሥራ አሥኪያጁ መንግሥት ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ በመኾኑ የአሥፓልት መንገድ ሥራውን በ2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የፕሮጀክቱ አማካሪ ግርማ ነጋሽ “ሀገሪቱ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ የመሬት ካሣ ክፍያዎች ቢጓተቱም መንግሥት በሂደት ክፍያውን እየፈጸመ ነው” ብለዋል። ለመንገድ ሥራው የማኅበረሰቡ ተሳትፎ እገዛ እያደረገ እንደኾነም አስረድተዋል።

የዳባት ወረዳ አሥተዳዳሪ ገብረሕይወት መኳንንት የአሥፓልት መንገድ ሥራውን በቅርበት እንደሚከታተሉ ገልጸው አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት ለሥራው እንቅፋት የሚኾኑ ችግሮችን እየፈቱ ሥራው እንዲቀጥል እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የአሥፓልት መንገድ ሥራው ሲጠናቀቅ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለረጅም ዓመታት ለያይቶ እንዳይገናኝ ካደረገው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጋር በማገናኘት ትልቅ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝ኢትዮጵያ ልጇን አዘዘችው፣ በቤቷም አሳደረችው❞
Next article#ሻደይ_አሸንድዬ_ሶለልና_ቡሄ_2014_ዓ.ም