❝ኢትዮጵያ ልጇን አዘዘችው፣ በቤቷም አሳደረችው❞

169

ነሐሴ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መንገደኛው አድሯል፣ ተጓዡ አርፏል፣ ከርታታው ዘመድ አግኝቷል፣ ማደሪያ የለሹ በእናቱ ጉያ ታቅፏል፣ በእናቱ ባድማ ጎጆ ቀልሷል፣ ለዘመናት ተንከራተተ፣ ለዘመናት ድንጋይና እንጨት፣ አፈርና ቅጠል ጎተተ፡፡ እረኞች እያዜሙ ሸኙት፣ ባለቅኔዎች እየተቀኙ ተሰናበቱት፣ ጠቢባን አንድ መልካም ቀን እንደሚመጣ እያሰቡ እያለቀሱ ተለዩት፡፡

እርሱም እያዘነ ተለያቸው፣ አንድ ቀን በእናት ሀገሩ የሚያድርበትን ዘመን እያሰበ ራቃቸው፣ የፈለቀበት፣ የተገኘበት ምድር ሰዎች እያዜሙ ሲሸኙት፣ ድርቅ በበዛበት፣ ሀሩርና በረሃ በአየለበት ምድር የሚገኙ ሰዎች እየጨፈሩ ተቀበሉት፣ እየደለቁ እንኳን ደኅና መጣህ አሉት፤ ማደሪያ አዘጋጅተው እደር አሉት፣ እርሱም በሀገሩ ያላገኘውን ክብር በተጓዘበት አግኝቷልና በሰጡት ማደሪያ ላይ አረፈላቸው፡፡ ከእናት ሀገሩ የተሸከመውን ድንጋይና እንጨት፣ አፈርና ቅጠል ያለ ስስት ሰጣቸው፡፡

የደረቁትን አለመለማቸው፣ የተራቡትን አጠገባቸው፣ የታረዙትን አለበሳቸው፣ የተጠሙትን አጠጣቸው፣ በጠኔ የነበሩትን በጮማ አቀማጠላቸው፣ በወይን እና በሻምፓኝ አራጫቸው፣ ሥልጣኔ ያልነበራቸውን ሥልጣኔ አሳያቸው፣ ከፍ ከፍም አደረጋቸው፡፡ ይህን ኹሉ ሲያደርግ ግን የእናቱ መከፋት፣ የእናቱ ብርሃን ማጣት እንደቀጠለ ነበር፡፡

የወለደችው እናቱ ተከፋች፣ የወላድ መካን ኾና ኖረች፣ በጭስ ተሰቃየች፣ በጨለማ ዳበሰች፣ በእሳት ተገረፈች፣ በጨለማ ውስጥ ኾና የልጇን ብርሃን ፈለገች፣ ልጅና እናት የሚስማሙበት፣ ልጅ እናቱን የሚታዘዝበት፣ እናቱን የሚያከብርበት፣ የእናቱን ጉልበት የሚስምበት፣ በእናቱ ጉያ የሚታቀፍበት ዘመን ይመጣ ዘንድ ለዘመናት ጠበቀች፡፡

ዘመኑ ደረሰ፣ ከርታታው ልጇ እናቱን ታዘዛት፤ ከተመረጡት አፍላጋት የተመረጠው፣ በተመረጠችው ምድር የፈለቀው፣ ረቂቁን ምስጢር ታቅፎ የያዘው፣ በምስጢራዊ ሐይቅ ታዝሎ ያለፈው ታላቁ አፍላግ ከእናቱ ጋር ተወዳጅቷል፣ የእናቱን ምክር ሰምቷል፡፡ እናቱ አዝዘዋለች፣ እርሱም ሰምቷታል፡፡ እናቴ ኾይ ምን ላድርግልሽ ? ምንስ ትሺያለሽ ? ብሏታል፡፡

እርሷም ብርሃን ስጠኝ፣ ተከብረህ አስከብረኝ፣ አዘምነኝ፣ ከሀብት ላይ ሀብት ደራርብልኝ አለችው፡፡ እርሱም እንዳልሽ አላት፡፡

ኢትዮጵያ መንገደኛ ልጇን አሳደረችው፣ ጎጆ መውጫ ሥፍራ ሰጠችው፣ ጎጆ ቀልሳ ወግ ማዕረግ አሳየችው፡፡ ልጇም በተቀለሰለት ጎጆ አደረ፣ በእናቱ ጉያ ታቀፈ፣ ከእናቱ ጋር ላይለያይ ቃልኪዳን አሠረ፡፡ ብርሃን ኾኖ ሊያኖራት፣ ብርሃን ኾኖ የጨለማውን ዘመን ሊገፍላት፣ ከጭስ ሊያላቅቃት፣ በእሳት ከመገረፍ ሊያድናት ልጇ የማይሻር ቃልኪዳን ገባላት፡፡

ኢትዮጵያ ኾይ የበኩር ልጅሽን ወግ ማዕረግ አሳይተሻልና እንኳን ደስ ያለሽ፣ ኢትዮጵያ ኾይ ጭስ ሊርቅሽ ነውና እንኳን ደስ ያለሽ፣ ልጅሽ ወግ ማዕረግ ሊያሳይሽ፣ ፈቃድሽን ሊሞላልሽ፣ የጨለማውን ካባ አንስቶ በብርሃን ሊመላሽ ታዝዞሻልና እንኳን ለዚህ አበቃሽ፡፡ ከረዘሙት የሚረዝመውን፣ ከተመረጡት የተመረጠውን፣ ከረቀቁት የረቀቀውን አፍልቀሽዋልና ክብር ኹሉ ላንቺ ይሁን፡፡

የጠሉሽን ወደድሻቸው፣ የገፉሽን ደገፍሻቸው፣ የወጉሽን አከምሻቸው፣ በጨለማ እንድትኖሪ የፈለጉትን ብርሃን ሰጠሻቸው፣ ክፉውን በመልካም መለስሽ፣ መከራውን በትዕግስት ተሻገርሽ፣ ጨለማውን በጽናት ገለጥሽ፡፡

ትዕቢት ወጥሮት፣ ጥቅም አስክሮት የተነሳብሽን፣ ትዕግስት ፍራት የመሰለውን ደግሞ በክንድሽ ቀጣሽው፣ ከድንበር ማዶ አስቀረሽው፣ በኃያልነትሽ አሳፈርሽው፣ አንችን ነክቶ የሚኾንለት የለምና አቅምሽን አሳየሽው፡፡ ኢትዮጵያ በሰላምም ታሸንፋለች፣ በጦርነትም ድል ትቀዳጃለች፡፡ እርሷ በእውነት፣ ለእውነት እና የእውነት የፀናች፣ ለድል አድራጊነት፣ የተመረጠች ኃያል ናትና ማሸነፍ የባሕሪዋ ነው፡፡ ድል እያደረጉ መጓዝ መለያዋ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለልጇ ለዓባይ ጎጆ መቀለስ በጀመረች ጊዜ በዓባይ ብርሃን ያዩት፣ በዓባይ ሥልጣኔን የጀመሩት፣ በዓባይ ረሃባቸውን ያስታገሱት፣ በዓባይ ጥማቸውን ያረኩት፣ በዓባይ የተቀደደ ልብሳቸውን የቀየሩት፣ በዓባይ ማንነታቸውን የለወጡት፣ በዓለም ፊት የኮሩት አርፈሽ ተቀመጭ አሏት፡፡ እናቱን ሳይጠቅም የሚኖረውን ልጇን እየተገለገሉበት፣ ከሥልጣኔ ላይ ሥልጣኔ እየደራረቡበት፣ አብዝተው እየወደዱት እና እየተመኩበት እናቱን ግን ጠሏት፡፡ ልጅሽ የእኛ እንጂ የአንቺ አይደለም አሏት፡፡

ኢትዮጵያ ልጇን የምታዝዝበት፣ ከልጇም ፀጋ የምትቋደስበት ዘመን መድረሱን፣ እርሷ እያበራች ሌሎቹን ቆሞ የማብላቱ፣ በብርሃን እጦት የመሰቃየቱ ዘመን ማብቃቱን ለወዳጅ ለጠላቶቿ አስረግጣ ተናገረች፡፡ ለዓባይ ማደሪያ የሚኾን ጎጆም መቀለስ ጀመረች፡፡

የሚያስፈራሯትን እረፉ አለቻቸው፡፡ እነርሱም በጦርነት እንደማይችሏት፣ በጥበብም እንደማይረቷት ያውቃሉና እየመረራቸው ዋጡት፣ እየከፋቸው ተቀበሉት፣ መነሳታቸው የእርሷ ማደግ አስቀንቷቸው እንጂ ከእነርሱ ላይ የሚቀንሰው እንደሌለ አብዝተው ያውቁት፣ ይረዱት ነበር፡፡

አይደረግም የተባለው፣ ተደርጎ፣ አይኾንም የተባለው ኾኖ፣ አይቻልም የተባለው ተችሎ ለዓባይ የተሠራው ቤት ታላቅ ኾኗል፡፡ ዓባይ ብርሃን መኾን ጀምሯል፡፡ ለዘመናት በዋሽንት የሸኙት እረኞች፣ በቅኔ የተሰናበቱት ባለቅኔዎች፣ በጥበብ ያሰቡት ምስጢረኞች ደስታቸው ከፍ ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች በብርሃን ሊሞሉ፣ ጭስ ያጠገባቸው ጎጆዎች በብርሃን ሊጎበኙ ዘመኑ ደርሷል፡፡ ለምን ዓባይ ብርሃን ኾኗልና፡፡

በረሃ የበዛባት፣ ሃሩርና ወበቅ የሚያስቸግራት ጉባ በሐይቅ ታጥራለች፣ በፏፏቴ ተሞልታለች፣ የዓለምን ዓይን ስባለች፣ ዓለምን አጓጉታለች፣ የኢትዮጵያ ብርሃን አድሮባት፣ አድሮም ይነሳባት ዘንድ ተመርጣለች፡፡

አንድ የኾኑት ያሸንፋሉ፣ በጋራ የሠሩት በጋራ ያድጋሉ፡፡ ጨለማውን ጥለው በብርሃን ውስጥ ይኖራሉ፡፡

አሁን ❝ዓባይ ዓባይ፣ የሀገር ለምለም የሀገር ሲሳይ❞ እየተባለ ነው፡፡ ዓባይ ለእናቱ እንደታዘዛት ኹሉ እናንተም ታዘዟት፣ አንድ ኹኑና በአንድነት አጽኗት፣ ለቅሶና መከራን ከእርሷ አርቁላት፣ ደስታና ተድላውን አብዙላት፡፡ ዓባይ በእናቱ እቅፍ እንደገባ ኹሉ እናንተም በእናታችሁ እቅፍ ግቡ፡፡ ያን ጊዜ ደስታ ኹሉ ከእናንተ ጋር ይኾናል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“በቃላችን መሠረት፣ ማንም ላይ ጉዳት ሳናደርስ እነሆ 3ኛውን ዙር ውኃ ሙሌት በታሰበው ጊዜ ማጠናቀቅ ስለቻልን የዓባይ ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ ያለን!!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Next article‟ከወልቃይት ጠገዴ ወንድሞቻችን ጋር የሚያገናኘን የአሥፓልት መንገድ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው” የአጅሬ ጃኖራ ነዋሪዎች