
ነሐሴ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመላው ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባ በቀጥታ ባሰራጩት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት “ዓባይ የእኛ የፈጠራ ውጤት ሳይኾን የፈጣሪ ስጦታ ነው” ብለዋል፡፡ የፈጣሪ ስጦታ የኾነውን ዓባይ ወንዝ በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ደግሞ የተፈጥሮ ሕግ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዓባይ የዓለም ሕዝብ ውድ ስጦታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድቡ ዙሪያ በተፈጠሩት 70 ደሴቶች ደስታን ለመሸመት የሚተሙበት የቱሪስት መዳረሻ ይኾናል ብለዋል፡፡ ከግድቡ በፊት አካባቢው ሞቃታማ ነበር፤ ይህን ቀይሮ የመዝናኛ እና የሐሴት ደሴት ለማድረግ የታተሩ ኹሉ ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ዓባይ የአፍሪካ ሀገራት ልዩ ስጦታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ስምምነት ከተፈራረሙ ዓመታት ላስቆጠሩት አፍሪካዊያን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉልበት ይኾናል ብለዋል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የዓባይ ወንዝ ልዩ እና ነጻ ተጠቃሚዎች መኾናቸውን ያወሱት ዶክተር ዐቢይ ስጦታን በአግባቡ መጠቀም፣ መገንዘብ እና መተባበር ደግሞ ተፈጥሯዊ ግዴታቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓባይ የፈጣሪ ስጦታ መኾኑን ተረድታ የሚገባትን ተጠቅማ የሚገባቸውን ለማሳለፍ ዝግጁ መኾኗን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻየን ልጠቀም ማለት ግን የተፈጥሮ ሕግን መጋፋት ነው ብለዋል፡፡ ዛሬ የተጠናቀቀው ሦስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ግድቡ የሚገባውን አስቀርቶ የሚገባቸውን የመስጠት ተፈጥሯዊ ሂደቱን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

ግድቡ ባለፈው ዓመት ከነበረው 575 ሜትር ከፍታ ላይ 25 ሜትር ከፍታ ጨምሮ 600 ሜትር መድረሱን እና ግራና ቀኝ ባለፈው ዓመት ከነበረው 585 ሜትር ከፍታ ወደ 611 ሜትር ማደጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
