
ባሕር ዳር: ነሐሤ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ መዝሙር እና ስም ብቻ ሳይሆን ሕልም እና ትልም ሆኖ ለዘመናት ነጉዷል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ የመሪነትን እርካብ የተቆናጠጡት ነገሥታት እና መንግሥታት ሁሉ ዓባይ የእግር እሳት ሆኖባቸው አልፏል፡፡ ዓባይ ለጥንት ኢትዮጵያዊያን ነገሥታት እንዳይተውት ሃብት እንዳይገድቡት ድግሞ ድህነት እንቅፋት ሆኖባቸው ሃሳባቸውን እንጂ ክቡር አሻራቸውን እንዳያሳርፉ አድርጓቸዋል፡፡
ከካይሮ እስከ ካርቱም የተዘረጉ የደባ እና የሴራ እጆችም ዓባይ በሀገሩ እንዳያድር ከጥንት ጀምረው ብዙ ሰርተውበታል፡፡
ዓባይ ከኢትዮጵያ ማህጸን የፈለቀ አንድያ ልጅ ሆኖ ሳለ በተጭበረበረ ሰነድ መጠሪያው ግን ግብጽ ሆና ቆይታለች፡፡ ግብጽ የዓባይ ስጦታ ናት የሚለው የተሳሳተ ተረክም የዚሁ ሴራ ብሔራዊ መዝሙር ሆኖ አገልግሏል፡፡
የዓባይ ጉዳይ ከአፍሪካዊያን አልፎ እስከ ካሪቪያን፣ ከመከካለኛው ምሥራቅ ተሻግሮ እስከ ምዕራባዊያን የንትርክ እና የአሻጥር ርእሰ ጉዳይ ከሆነ ክፍለ ዘመን አስቆጥሯል፡፡
በዓለም ታሪክ ሃብቷን ተጠቅማ ራሷን በማልማቷ ብቻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከደርዘን ጊዜ በላይ ጉዳይዋ የታየ ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡
ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ተራራማ አካባቢዎች እየተነሳ ያለከልካይ የሚንደረደረው ዓባይ የኢትዮጵያን የዘመናት ህልም እና ትልም ከሚንደው አፈር ጋር አጥቦ ሲጓዝ ቆይቷል፡፡ ግንድ ይዞ የሚዞረው ዓባይ የተባበሩ ክንዶች አጥረውት ማደሪያ አልባ ሲባል ኖሯል፡፡ ያ ግን የዓባይ ታሪክ እንጂ የዓባይ ወንዝ የዘመናት እውነት አልነበረም፡፡
ታሪክ ሊቀየር እና እውነት ሊገለጥ ሲቃረብ ጫናዎቹ ከትናንቱ በርትተው ዛሬ ከየአቅጣጫው አየሉባት፡፡ የሴራ እጆች እና የተንኮል ክንዶች ውስብስብ ሆነው እንደ አዲስ በአዲስ ተቀነባበሩ፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቿ ታሪክ የማይሽረው እና ፈጽሞ ይቅር የማይለው ፈተና ተደራረቡባት፡፡ ጠመዝማዛው ወንዝ በጠመዝማዛ መንገድ ዳግም እጆቹን ለሀገሩ ገበረ፡፡
ይህ ሁሉ እስኪሆን ግን ነገሮች ሁሉ ቀላል አልነበሩም፡፡ ውድ ሃብት፣ ክቡር ሕይዎት እና መራር መስዋእትነት ተከፍሎበታል፡፡ የዓባይ ዙሪያ ልጆች ለዘመናት በጭስ ዐይናቸው ተጎድቶ የኤሌክትሪክ ብርሃን ሳያይ እና የኢትዮጵያን አሸናፊነት ሳይመለከቱ የተልዕኮ ጦርነት ሰለባ ሆነው እስከወዲያኛው አሸልበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በመከራ ዳገቶቿ እና በፈተና መንገዶቿ ሁሉ አበቃላት ስትባል ብዙ ጊዜ እንደገና አንሰራርታ ታሪክ ቀይራለች፡፡
ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ጮቤ የረገጡበት ወዳጆቿ የሞት ሽረት ትግል ያደረጉበት የትናንቱ ጊዜ ብዙ ነበር፡፡ መከራዎቿን ላስታወሰ ኢትዮጵያ የዛሬው ደስታዋ እና ስኬቷ ትክክለኛ መንገዷ እንጂ የመጨረሻ መዳረሻዋ እንዳልሆነ ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለመጨረስ እና ፈተናዎቿን ለመቀነስ እምነቷ እና ጉልበቷ በዜጎቿ ነውና ከምን ጊዜውም በላይ ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆምን ዛሬ ይጠይቃቸዋል፡፡ ፈተና ለበረታባት እና ውጣ ውረዱ ለበዛባት ኢትዮጵያ ኃይል እና ጉልበት የሚሆን እልፍ ስኬት ትፈልጋለች፡፡
ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
