
ባሕር ዳር: ነሐሤ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይነር ኃይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ ፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮነን፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንኳን ለድልና ለእድል አበቃችሁ ብለዋል፡፡
በታሪክ ውስጥ ማለፍና ታሪክ መሥራት እንዳለ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታሪክ ውስጥ ማለፍ እድል ነው፣ ታሪክ መሥራት ግን ድል ነው ብለዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የዚህ እድልና ድል ተቋዳሾች ነንም ነው ያሉት፡፡
ለሺህ ዓመታት ሲታሰብና ሲታለም የነበረውን ግድብ በዓይኑ ያየ፣ በእጁ የዳሰሰ ባለ እድል ትውልድ ነው ብለዋል፡፡ አባቶች ያቀዱትን ዛሬ ልጆች ማየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ለሕዳሴ ግድብ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ሕይወታቸውን የገበሩ ኢትዮጵያን መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
አባቶቻችን ለዚሕ ግድብ አስበዋል፣ እኛ የታሰበውን ተግብረነዋልም ነው ያሉት፡፡ ዓባይ ከምኞትና ከሃሳብ ተሻግሮ ተግባር መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡
የአባቶቻችን ትልምና ፍላጎት በማሳካት ሀገርን በጸና መሠረት ላይ ማቆም የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የጸናች የበለጸገች ሀገር ማውረስ ይገባልም ብለዋል፡፡ ሀገር የሌለው ሀብትና ንብረት መውረስ እንደማይችልም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከጨለማ የማውጣት እንጂ ሱዳንና ግብጽን የመጉዳት ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላትም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኃይል እያመነጨች ሌሎች ሀገራትንም ተጠቃሚ ታደርጋለች ነው ያሉት፡፡
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በንግግርና በውይይት ለውጥ እንደሚመጣ አውቀው እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ያለውን ማንኛውም አማራጭ የጀመርነውን ነገር የማያስቆም በከንቱ የሚያደክም መሆኑን ተገንዝበው ወደ ሰላም ድርድር እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል የሕዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በሕዳሴ የተጀመረው ድል በሁሉም ይቀጥላል ብለዋል፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለትልቁ ድል በጋራ እንቁምም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
