
ባሕር ዳር: ነሐሤ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ይህን አካባቢ መጎብኘት በራሱ ብዙ መጽሐፍ ያነበቡ ያክል እንዲሰማዎ ያደርጋል።
የአማራ ክልል በታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶች የታደለ ነው። ክልሉ ባለብዙ እድሜ ጠገብ የሃይማኖት ተቋማት ባለቤትም ነው።
የደቡብ ጎንደር ዞን እንደሌሎቹ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ በበርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ መስህቦች የበለጸገ ነው። በዞኑ በኹሉም ወረዳዎች ውስጥ በርካታ እድሜ ጠገብ መስህቦች ይገኛሉ።
አሚኮ በዚህ ዘገባ በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ የሚገኘውን ታሪክ ነጋሪውን የአምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳምን ይዳስሳል።
መነሻችንን ከውቢቷ ባሕር ዳር አድርገን ጉዟችንን ቀጠልን። በፎገራ ወረዳ እየለሙ ያሉ የሩዝ ማሳዎችን እንዲኹም ከአዲ ዘመን እስከ እብናት ከተማ በግራና በቀኝ ያለውን ጥቅጥቅ ደን እየተመለከትን ጉዞአችንን ቀጠልን።

መዳረሻችን ከኾነው የእብናት ከተማ ደርሰን ጥቂት እረፍት ካደረግን በኋላ ከከተማው በስተ ደቡብ አቅጣጫ በ8 ኪሎሜትር ርቀት ወደሚገኘው፣ የወረዳው መገለጫ ከኾኑ መስህቦች ውስጥ አንዱ ወደ ኾነው የአምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳም ጉዞ ጀመርን። ከገዳሙ ከደረስን በኋላ ወደ ዋናው ግቢ ለመድረስ ተራራዎችን ለመውጣትና ለመውረድ ትንቅንቅ ጀመርን።
ከእኛ ጋር የነበሩት የአካባቢው ማኅበረሰብና የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የሥራ መሣሪያዎቻችንን በመሸከም ድካማችንን አቅልለውልን ነበር። አቀበቱን ለመውጣት በምናደርገው ጉዞ በጥቅጥቅ ደን ውስጡ የሚኖሩ የተለያዩ እንስሳትና አእዋፋት የሚያሰሙት ድምፅ ድካማችን አቀለለው።ገዳሙ ወደ ተመሰረተበት ስፍራ ስንደርስ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳት ተቀብለው በሚታወቁበት የእንግዳ አቀባበል ሥነ ሥርዓት አስተናገዱን።
የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደረጉልን የገዳሙ ሰብሳቢ ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም ስለ ገዳሙ ታሪክ በዝርዝር አጫውተውናል።

የአምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳም የተመሰረተው በ12ኛው ክፍለ ዘመን መኾኑን ያስረዱን ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም በዩኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ንጉሡን ቅባተ መንግሥት ቀብተው ማንገሳቸውን አጫውተውናል። ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት በአሁኑ የገዳሙ አጠራር በአምስትያ ገዳም ከስውራን ጻድቃን ጋር በመገናኘት ከጻድቃኑ ቡራኬን ይቀበሉና ቡራኬንም ሲሰጡ እንደነበረ አስረድተዋል። በወቅቱ የገዳሙ ስያሜ “ወንበርምካ” ተብሎ ይጠራ እንደነበረ ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም ገልጸዋል።
ከአቡነ ተክለሃይማኖት በፊትም ቢኾን ገዳሙ በጫካ የተሞላና በውስጡ ስውራን ጻድቃን ይገኙበት እንደነበርም ጠቁመዋል። “እግዚአብሔር ስፍራው ወደፊት ምን እንደሚመስል ለአቡነ ተክለሃይማኖት ገለጸላቸውም። አቡነ ተክለሃይማኖትም ገዳሙ ወደፊት በእሳቸው ስም እንደሚመሰረትና በእጃቸው የሚገኘውን የባታን ጽላት ለስውራን ጻድቃን ትተውላቸው ወደ እየሩሳሌም ሄዱ። ስውራን ጻድቃንም የተቀበሉትን የባታን ጽላት በማጠር በስፍራው ተቀምጠዋል” በማለት ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም ስለ ገዳሙ ምስረታ አስረድተዋል።
ታቦተ ባታም በስውራን ቅዱሳን በዋሻ ውስጥ በስውር በሰሌን ተጋርዳ እየተገለገለች እስከ አጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆይታለች ብለዋል። በአጼ ዳዊት ክፍለ ዘመን አምስቱ ቅዱሳን በአምደብርሃን እየተመሩ ወደ ገዳሙ መምጣታቸውን ነበር ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም ያጫወቱን። የገዳሙ ስያሜም ከወንበርምካ ተለውጦ በአምስቱ ቅዱሳን ስም አምስትያ ተብሎ መሰየሙን ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም ገልጸዋል። ስያሜውን ገዳሙንና አካባቢውን እንደሚያካልልም ነው የነገሩን።
“እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአምስቱ ቅዱሳን ተገልጻላቸው የገዳሙ ስያሜ አምስትያ እንዲባል ከነገረቻቸው በኋላ ቅዱሳኑ አመስግነዋት በክብር አርጋለች” በማለት ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም ገለፃ አድርገዋል። ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ገብረማርያም የአሁኑ ትውልድ ታሪኩን በአግባቡ እንዲረዳና ሃይማኖቱንም ኾነ ገዳሙን በአግባቡ እንዲጠብቅ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የገዳሙ አስጎብኚና አገልጋይ የኾኑት አባ ገብረመስቀል ገብረማርያም ጎብኚዎች ወደ አምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳም በሚመጡበት ወቅት የገዳሙን ሙሉ ታሪክ እንደሚሰሙ፣ የሰባቱን አጽመ ቅዱሳን እንደሚመለከቱና በረከቱን እንደሚያገኙ አስረድተዋል። በገዳሙ ውስጥ ገዳሙን የመሰረቱ የጻድቃን አጽም እንደሚገኝና ለጎብኚዎች ክፍት እንደኾነም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በብቸኝነት የምትገኝ ዕጸ ሮማን በገዳሙ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸዋል። ዕጸ ሮማኗ ቅዱሳን ለብራና መጻፊያ ሲገለገሉባት እንደነበረችና አሁን ደግሞ በገዳሙ ውስጥ ለሚኖሩ መነኮሳት ለምግብነት እያገለገለች እንደምትገኝ አባ ገብረመስቀል ገብረማርያም ገለፃ አድርገውልናል። ጎብኚዎች አምስቱ ቅዱሳን ያረፉበትን ስፍራ እንደሚመለከቱም ገልጸዋል። ከገዳሙ ከሚገኘው በረከት በተጨማሪም ጎብኚዎች በእናቶች የሚሠሩትን እደ ጥበባት እንደሚቃኙም አስረድተዋል።
የአምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳም መገለጫቸው መኾኑን የአካባቢው ነዋሪዎችም መስክረዋል። አንዳርጌ መለሰ የተባሉት ነዋሪ በጉልበታቸውም ኾነ በገንዘባቸው
ገዳሙን እያገዙ እንደኾነ ተናግረዋል። በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳትም የሚሰጧቸውን ትእዛዝ በአግባቡ እያከናወኑ እንደሚገኙም ነዋሪው ጠቁመዋል።
አምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳም እድሜ ጠገብና ባለብዙ ታሪክ ባለቤት ቢኾንም እድሜ ጠገብ እንደመኾኑ መጠን የመሰነጣጠቅ ችግር ገጥሞታል። ወደ ገዳሙ የሚወስደው መንገድም በሚፈለገው መጠን አመቺ ባለመኾኑ የተሟላ ሥራ እንደሚያስፈልገው አሚኮ ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል።

አቶ አንተነህ የተመኝ የእብናት ወረዳ ባሕል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ናቸው። ጽሕፈት ቤታቸው አምስትያ ተክለሃይማኖት የወንዶችና የሴቶች ገዳምን እንደ አንድ ታላቅ መስህብ በመመዝገብ እየሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል። ከገዳሙ አስተዳዳሪዎች ጋር በመነጋገር ገዳሙ የኤሌክትሪክ ኀይል አገልግሎት እንዲጠቀም መደረጉንም ኀላፊው ገልጸዋል። ጽሕፈት ቤታቸው በቻለው አቅም ከንግስ ቀን ጎብኚዎች በተጨማሪ ዓመቱን ሙሉ የሚጎበኝ መስህብ ለማድረግ ማቀዱን አቶ አንተነህ አስረድተዋል። በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩ ከ250 በላይ የሚኾኑ መነኮሳት የእደ ጥበባት ውጤታቸውን ወደ ከተማ አውጥተው እንዲሸጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውንም ኀላፊው ገልጸዋል።
የገዳሙን መንገድ የጥገና አገልግሎት ለመስጠት በ2015 በጀት ዓመት በእቅዱ ማካተቱን የደቡብ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል። መምሪያው የአካባቢውን ኅብረተሰብና ባለሀብቶችን በማስተባበር ለገዳሙ አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ማቀዱን ነው በመምሪያው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ገደፋው ወርቁ ያስረዱት። ቡድን መሪው እንዳሉት ገዳሙን ለመንከባከብና ለመደገፍ በተያዘው በጀት ዓመት ከክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ጋር በቅንጅት ለመሥራት አቅደዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
