
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሕጻናቱ አብዝተው ይናፍቋታል፣ የመድረሷን ነገር እያሰቡ ይጓጓሉ፣ በንጹሕ ልባቸው እያሰቧት ይናፍቃሉ፣ ናፍቆታቸው ለመሳቅና ለመጫወት፣ ለተድላና ተዝናኖት አይደለም፤ ናፍቆታቸውስ ለጾምና ለጸሎት፣ ለምኅላና ለሥርዓት ነው፡፡
ወርሐ ነሐሴ ትናፈቃለች፣ በጉጉት ትጠበቃለች፣ በወርሐ ነሐሴ አፍላጋቱ ባዘቶ ይመስላሉ፣ ተራራዎችና ኮረብታዎች ባማረ ካባ ይዋባሉ፡፡ የተናፈቀችው ወር ስትደርስ ሕጻናቱ ደስታቸው ከፍ ይላል፣ ሌሊቱ ሲጋመስ የየአድባራቱና የየገዳማቱ ደዎል ከየአቅጣጫው ያቃጭላል፣ ተነሱ ለጸሎት ይባላል፣ ካሕኑ ትጉ ወደ ደጅም ቅረቡ ይላል፡፡
የካሕናቱን ዜማ፣ የደብሩን ደወል የሰሙ ምዕምናን ከአንቀላፉበት ይነሳሉ፣ ነጭ እየለበሱ ከቤታቸው ወጥተው ደወሉ ወደተሰማበት በኩል ይገሰግሳሉ፡፡
ጎዳናዎች ነጭ በለበሱ ምዕመናን ይሞላሉ፣ አውደ ምኅረቶቹ በሰዎች ብዛት ይጨናነቃሉ፣ ጽሕናዎች ሿሿሿ ሲሉ ይሰማሉ። ዲያቆናቱ፣ ቀሳውስቱ፣ መነኮሳቱ፣ ኤጵስ ቆጶሳቱና ጳጳሳቱ ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ ከዓይናቸው እንባ እያፈሰሱ፣ ያለቅሳሉ፣ ምድር ትባረክ፣ ሰላምና ፍቅር ይበዛባት ዘንድ ፈጣሪያቸውን ይማጸናሉ፡፡

ሕጻናቱ እንደ ወትሮው በጠዋት ተነስተው ምግብ አይቀምሱም፣ ከአልጋቸው ላይ አያረፍዱም፣ ነጠላቸውን ለብሰው ከወላጆቻቸው እግር ሥር ተከትለው የካህናቱ ድምጽ ወደሚመሰማባት፣ ጸሎትና ምኅላ ወደ ሚቀርብባት ወደ ቤተክርስቲያኗ ያመራሉ እንጂ፡፡ በዚያም ሃይማኖትን ይማራሉ፣ ትኅትናን ያያሉ፣ ሰው ማክበርን፣ ፈጣሪን መፍራትን፣ ለሀገር መጾምና መጸለይን፣ ሀገር መውደድን ያያሉ፡፡
አቤቱ ማረን፣ ይቅርም በለን፣ ፍቅርና አንድነትን ስጠን፤ ኢትዮጵያን ጠብቃት፣ ከፍ አድርገህ አኑራት፣ ጠላቶቿን ፈጥነህ አስገዛላት፣ ወዳጆቿን እንደ ምድር አሸዋ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት አብዛላት፣ ልጆቿን በፍቅር ባሕር ውስጥ አጥለቅልቅላት እያሉ ይማጸናሉ፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን አብዝተው ይጨነቃሉ፡፡ ሀገር መውደድንና ስለ ሀገር መጨነቅን ይመለከታሉ፣ እነሱም ይወዱ ዘንድ ቃል ይገባሉ፡፡
እረኞች ምግብ ሳይቀምሱ ምሳቸውን አስቋጥረው ከቤት ይወጣሉ፣ ላምና በሬዎቻቸውን፣ ፍየልና በጎቻቸውን እየነዱ ወደ ግጦሽ ይሠማራሉ፣ በዋሽንታቸው እያዜሙ፣ የተወደደችውን ሳምንት እያሰቡ ይውላሉ፣ ጀንበር ወደ መግቢያዋ ካላዘቀዘቀች፣ የቀኑን መምሸት ካላበሰረች የተቋጠረችውን ምሳቸውን አይፈቷትም፣ በጎሮሯቸው ምግብ አትወርድም፡፡
ወርኃ ነሐሴ የምትናፈቅ፣ የተወደደች ወር ናት፡፡ ክርስቲያኖች ከሰባቱ አጿማት መካከል አንደኛዋን የሚጾሙባት ፍልሰታ እያሉ የሚጠሯት፣ እረኞች፣ ሕጻናት፣ አዛውንት ኹሉም በአንድነት የሚጾሙባት ወር ናት፡፡

ጾም መለየት፣ መተው፣ መከልከል ነው ይላሉ አበው፡፡ ሰውነትን ክፉ ከኾነው ነገር ያርቁታል፣ ከጣመና ከጣፈጠ ምግብ ይከለክሉታል፣ አንደበታቸውን ክፉ እንዳይናገር ያቅቡታል፡፡ ዓይን ክፉ ከማየት ይከልከል፣ ምላስም ክፉ ከመናገር ትከልከል፣ ጀሮም ክፉ ከመስማት ትከልከል እንዳለ መጽሐፍ፡፡
ጾም የግል ሕይወትን፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን፣ የሀገር ሰላምን ያስተካክላል፡፡ ጾም የነብስን ቁስል ትፈውሳለች፣ የስጋን ክፉ ምኞት ታደርቃለች፣ መረጋጋትን ማስተዋልን ትሰጣለች ይላሉ አበው፡፡ ጾም ሃይማኖትን ታስተምራለች፣ ሃይማኖት ደግሞ መልካምነትን ትሰብካለች፣ መልካምነትም ጽኑ ሀገርን ትገነባለች፡፡
አሁን በክርስቲያኖች ዘንድ ፍልሰታ እየተባለች የምትጠራው ጾም የሚጾሙባት ጊዜ ናት፡፡ መፍለስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስን፣ ከምድር ወደ ሰማይ ማረግን፣ ከጌቴ ሴማኒ ወደ ገነት መሄድን፣ ወደ ፀርዓያ አርያም መገስገስን ያመላክታል ይላሉ፡፡
ክርስቲያኖች እናታችን፣ አማላጃችን፣ መመኪያችን፣ የመከራው ዘመን መሻገሪያችን የሚሏት ማርያም ያረገችበትን ዘመን እያሰቡ የሚጾሙባት የሚማፀኑባት ናት፡፡ ማርያም ስታርግ መላእክት ይቀበሏት ዘንድ ወረዱ፣ ሐዋርያት በወርቅ ማይጠንት አጠኑ፣ ሱራፌልና ኪሩቤል ሲያመሰግኑ ታዩ፣ የክብር መብረቅ ታየ ተሰማ፣ ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ አረገች እንዳሉ፡፡

በዚሕ በተወደደች ሳምንት የተወደደች ነገር ያደርጋሉ፡፡ ብዙዎች ከቤታቸው ወጥተው ወደገዳማት ያቀናሉ፣ በዚያው ስለ ሀገርና ስለ ሕዝብ ሱባዔ ይገባሉ፡፡ ሕጻናት በንጹሕ ልባቸው ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይማጸናሉ፡፡
በዚህ ሰሞን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አድባራትና ገዳማት ኪዳን ይደረሳል፣ ቅዳሴ ይቀደሳል፣ ስለ ሀገር ይጸለያል፡፡
በፍልሰታ ሕጻናቱ ሃይማኖትን የሚማሩበት፣ መልካም ነገርን የሚያውቁበት፣ ወደ ፈጣሪ የሚቀርቡበት፣ ኢትዮጵያን አብዝተው የሚያስቡበት፣ የመልካምነት፣ የደግነት፣ የኢትዮጵያዊነት መሠረት የሚጥሉባት ናት፡፡ ሰው ማክበርን፣ ሀገር መውደድን፣ ጥላቻን መጣልን፣ መልካምነትን ማንሳትን፣ መስጠትን፣ ለተራቡት ማጉረስን፣ ለተጠሙት ማጠጣትን፣ ለታረዙት ማልበስን የሚማሩበት የሚያውቁበት፣ የሚተገብሩበት ሳምንት ናት፡፡

በተወደደችው ሳምንት የተወደደውን አድርጉ፣ ሀገራችሁን አብዝታችሁ ውደዱ፡፡ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ ኢትዮጵያን በአንድነት ጠብቁ፣ ስለ አንድነትም ተማጸኑ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እግራቸውን የሚያነሱት፣ ኢትዮጵያውያንንም የሚያጋጩት፣ የሚያጣሉት፣ በተከበረችው ምድር ፈተና የሚያበዙት ይወድቁ ዘንድ በአንድነት ለምኑ፡፡
በወርሐ ነሐሴ በኢትዮጵያ ድንቅ ነገር የሚከወንባት፣ ፍቅርና ደስታ የሚታይባት ናት፡፡ በአንድነት ኢትዮጵያን አድምቁ፣ በዓላቱና ሥርዓቱ ወደ ሚከናዎንባቸው ሥፍራዎች እየሄዳችሁም ኢትዮጵያን እወቁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
