
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ፎረም ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ መኩሪያ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ግብ በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም፣ በክልል፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር ፍትሐዊነት በነገሠበት፣ ከብዝበዛ ነፃ በሆነ ግንኙነት፣ የብዙኃኑን ፍላጎት የሚያሞላ ማኅበራዊ ስልት መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ለሠላም ቅድመ ሁኔታ ራሱ ሠላም ብቻ ነው፡፡ ያለሠላም ትምህርት፣ ልማት እና የሰው ልጆ አይኖሩም›› ያሉት ፕሬዝዳንቱ ካለመግባበት ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን እንደማይቻልም አመልክተዋል፤ አለመግባበት ወደ ግጭት ከማደጉ በፊት ለመፍታት የሚያስችል እሴት መገንባት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
እንደሀገር እየታዬ ያለው የሠላመ እጦት ክፉ በሽታ መሆኑንም ዶክተር አባተ ተናግረዋል፡፡ ለበሽታው ሀገር በቀል መድኃኒት እንደሚያስፈልገውም አሳስበዋል፡፡ ጦርነት የሚፀነሰው በሰው ልጆች አዕምሮ ውስጥ በመሆኑ የመከላከል ሥራው ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ ባለው የሰው ልጆች አዕምሮ መለወጥ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
‹የቅርብ ጸበል የልጥ መንከሪያ ይሆናል› ያሉት ዶክተር አባተ ኢትዮጵያውያን በርካታ እሴቶች ያሏቸው ቢሆንም ዘመኑን የዋጀ ዕድገትን ለማፋጠን፣ ፍቅርን ለማጎልበት ፣ ይቅርታን ለመፈፀምና ሠላምን ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ መዋል አለመቻላቸው ችግሩን እንዳባበሰ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አባተ ‹የሀገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ› የሚለው ብሂል በተግባር ባለመሠራቱ ‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር እንዲቆረጥ› ዕድል ሰጥቶ ሰው ሠራሽ ተግዳሮቶች ኅልውናን እየተፈታተኑ በመሆኑ ከተኛንበት ልንነቃ ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹አሁን አሁን ወሎን የመሠሉ የሠላም ተምሳሌቶች ደፍርሰዋል፡፡ በነገድ፣ በቋንቋ፣ በጎጥ፣ በመንጋ ተቧድኖ የውሸት ትርክት እና የመንጋ ፍርድ ነግሶ፣ ባልተኖረ ተረክ ተከልሶ፣ ባልሠራው ተወቅሶ፣ ማስተዋል ርቆ፣ በአብሮነት መሸመንን እና መደመርን ኅብረ ብሔራዊነትን ጠልቶ ጥላቻ እና መጥበብ ክፉ በሽታ ሆኗል›› ብለዋል፡፡
በስልጣኔ ዘመን ሰው መሆን በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከልዩነት ሰበዞች የተሠራ ኅብረ ቀለማዊ ማንነት ነው፤ በመሆኑ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለበለጸገ የማኅበረሰብ ለውጥ ሽግግር ማዕከል አድርጎ መሥራት እንደሚስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች እንጂ ክልል፣ ድንበር እና ወሰን የሌላቸው የሰው ልጆችን ተስፋ የሚቀርፁ እንጂ የክፋት እና የፀረ ሠላም ድርጊቶች መፈልፈያ እንዳይሆኑ የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በገቢር ማሰልጠን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ድኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ‹‹የሀገር በቀል ዕውቀቶች በታሪክ ፣ በፍልስፍና፣ በዳኝነት፣ በሕክምና፣ በንግድ፣ በፍልስፍና፣ በሽምግልና፣ በአመራር ጥበብ፣ በትምህርት አሰጣጥ፣ የጎለበተ ኢትጵያዊ ማንነት ነው›› ብለዋል፡፡
የሀገር በቀል ዕውቀቶች የብዙ ዓመታት የሕይወት ተሞክሮዎች እና አስተውሎቶች ሆነው ለብልፅግና፣ ለችግር መፍቻ፣ ለመዝናኛ፣ለቀብር ማስፈፀሚያ፣ ለደስታ ማጌጫ፣ ለግጭት መፍቻ፣ ለውሳኔ መስጫ፣ ለፍትሕ ማረጋገጫ፣ ለሠላም ማስጠበቂያ፣ ለወራሪ ጠላት መመከቻ የሆኑ የኢትዮጵያውያን የአዕምሮ ውጤቶች ናቸው እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡
እነዚህን ዕውቀቶች በተግባራዊ ምርምር በማስደገፍ ለላቀ የዕውቀት ሽግግር እና ለገቢራዊ የማኅበረሰብ ለውጥ ማንቂያ ለማዋል በቀጣይ ዓመታት በትኩረት መሥራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ሀገር በቀል ዕውቀት ለሠላም እና ለልማት›› በሚል ሐሳብ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተዘጋጀ መርሀ ግብር በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
ዘጋቢ ፡- ግርማ ተጫነ