
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በህገ ወጥ የዶላር ዝውውርና በሃዋላ የተጠረጠሩ 70 የተለያዩ ሃገራት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በተለያዩ ህግወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።
70 የተለያዩ የውጭ ሃገራት ዜጎች ኑራቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ አድርገው በህግ ወጥ የዶላር ዝውውር ሲሳተፉ በተደረገ ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል እንደተደረሰባቸው ያመለከተው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ፤ ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የሚላክ ዶላር፣ ዩሮ እና የተለያዩ ሀገራት የውጭ ገንዘቦችንም በየሀገራቱ ለዚሁ ዓላማ ባስቀመጧቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ወደ ግል አካውንታቸው እንዲገባ በማድረግና የኢትዮጵያ የብር ኖቶችን በመስጠት በህገወጥ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ተግባርም ጭምር በመሳተፋቸው ተጠርጥረው ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት የሠጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና ከህገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ህግወጥ የመኖሪያ ፈቃድን እና ፓስፖስርትም ጭምር አጭበርብረው ሲሰጡ የነበሩ 36 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባና ሀዋሳ ከተሞች በኢሚግሬሽንና ኤርፖርት አካባቢዎች ላይ ተመድበው ሲሰሩ ከህገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር የግል ጥቅማቸውን ሲያግበሰብሱ የነበሩ ሰራተኞችና ኀላፊዎች እንዲሁም ህግወጥ ደላሎች በተደረገ ጥብቅ ክትትልና የሕዝብ ጥቆማ ከሲዳማ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላካው መግለጫ ጠቁሟል።
መግልጫው አክሎም፣ተቋሙ በምስራቅ ኢትዮጵያ በድሬዳዋ አካባቢ በህገ ወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎች ላይ ያደረገውን ጥልቅ ጥናት መሰረት በማድረግ፤ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የተቀናጀ ኦፕሬሽን በማካሄድ ግምታቸው ከ100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆኑ የማዕድን ምርቶችን ከ11 ህገ ወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎችር ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል።

በተያያዘ በህገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ በመሰማራት ግምታቸው 70 ሚሊዮን ብር የሆኑ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን፣ልባሽ ጨርቆችን፣ የሲጋራ ምርቶችና መሰል ቁሳቁሶችንም ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን በመግለጫው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት አስፈላጊውን መረጃ በመሰብሰብ ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግም በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 582 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ 58ሺህ ዩሮ ፣10ሺህ ፓውንድ ፣5ሺህ 530 የካናዳ ዶላር 67ሺህ፣ 145 የሳውዲ ሪያል ገንዘቦች እንዲሁም ከ2 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ እና 10 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ወርቅ ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ገልጿል።
አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፉት ወራት ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተካሄዱ ተከታታይ ኦፕሬሽኖች፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከልም ከህወሃት የሽብር ቡድን ተልዕኮ በመውሰድ ለቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ 33 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም እየተወሰዱ ባሉ የህግ ማስከበር እርምጃዎች፣ ከ200 በላይ የሸኔ የከተማ ህዋስ አባላት ወይንም ተላላኪዎች ሲያዙ፤ ለቡድን የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ የ20 ግለሰቦች የባንክ የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቋል፡፡
የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማራመድ የሕዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሃሰትና የውሸት ወሬዎችን በመንዛት ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩ 42 ተጠርጣሪ ግለሰቦችም መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
መግለጫው አክሎም፤ ሃገሪቱ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ዝውውር ለመቆጣጠርና ለመከላከል ያወጣችውን አዋጅ መሠረት በማድረግ በተከናወኑ የተቀናጁ የኦፕሬሽንና የፍተሻ ሥራዎችም 11 ብሬን የቡድን የጦር መሣሪያዎች 524 የነፍስ ወከፍ የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 31 ሽጉጦችና 25 ሺህ 656 የተለያዩ የጦር ማሣሪያ ጥይቶች ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሃገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ፣ ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሽብርተኞቹ፣ በታጣቂዎች እንዲሁም በተለያዩ ህግወጥ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በመግለጫ እያሳወቀ፤ ኅብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት የአገልግሎት መስሪያ ቤቱን ነፃ የስልክ ጥሪ 910 በመጠቀም የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡
