አኹንም ትኩረት የሚሹት የመናገሻዋ ከተማ እንቁዎች!!

246

ጎንደር፡ ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እፁብ ያስባሉ አብያተ መንግሥታት ተገንብተውባታል፤ አጀብ ያስባሉ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ታንጸውባታል፤ ጎብኚዎች መዳረሻቸው አድርገዋታል፤ ብዙዎች የአፍሪካ መናገሻ እያሉ ይጠሯታል፤ ለዓለም ስልጣኔን አሳይታለች፤ ለሀገር የማይናወጽ ቃል ኪዳን አስራለች፤ ለኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ኾናለችና መናገሻዋ ይሏታል፤ ጎንደር።

ጎብኚዎች አብያተ መንግሥታቱን፣ አብያተ ክርስቲያናቱን፣ ጥንታዊ ድልድዮችን እና ሌሎች የረቀቁ ጥንታዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት ዓይናቸውን ጎንደር ላይ ይጥላሉ፡፡ ከየዓለም ሀገራት እየተጠራሩ ወደ ጎንደር ይጓዛሉ፡፡ በጎንደርም የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔ ያያሉ፤ የታሪክ አሻራውን ይከትባሉ፤ ኢትዮጵያውያን ምን ያክል ቀደምትና ስልጡን ሕዝቦች መሆናቸውን ይረዳሉ፡፡

ጎንደር በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ በርካታ የተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ በጎንደር ነገሥታት የተሠሩ አብያተ መንግሥታት፣ አድባራትና ድልድዮች አሁንም ድረስ የኢትዮጵያውያን ቀደምት የጥበብ ምልክቶች ናቸው፡፡ ቅርሶቹ በ1971 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የባሕልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ ጀምሮ ደግሞ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ በመሳብ ሀገሪቱ ነወየነበረችበትን የሥልጣኔ ደረጃ ከማስተዋወቅ ባለፈ ለአካባቢው እና ለሀገሪቱ ውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ኾነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ቁጥርመነ የኢትዮጵያውያን ቀደምት ሥልጣኔና ጥበብ አሻራ የኾኑት የጎንደር አብያ ተመንግሥታት ታሪካዊነታቸውን የሚመጥን እንክብካቤ ባለመደረጉ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የአካባቢው አስጎብኝ ሄኖክ አበበ ነገረውናል፡፡ አቶ ሄኖክ እንዳሉት የጎንደር አብያተ መንግሥታት በተለያዩ ጊዜያት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በ1704 ዓ.ም በመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት አስተናግደው ነበር። በ1888 ቅርሶቹ በድርቡሾች ተቃጥለዋል፤ ተዘርፈዋል፡፡ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ደግሞ እንግሊዞች ጣሊያኖችን ለማስወጣት በተካሄደው ጦርነት የቤተመንግሥታቱ ግንባታዎች በአየር ተመትተው ፈርሰዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በጊዜ ሂደትና በአየር ንብረት መቀያየር ቅርሱ በመሰነጣጠቅና በመፈራረስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ አብያተ መንግሥታቱን የሚመጥን መሰረተ ልማት አለመሟላቱን ነው አስጎብኝው ያነሱት፡፡ በተለይም ደግሞ የአጼ በካፋ ቤተ መንግሥት የኢጣሊያ ወራሪ ጣሪያውን በሲሚንቶ በተሠራ ኮንክሪት በመሥራት መኖሪያና የጦር መጋዝን አድርገውት እንደነበር ነግረውናል፡፡

አቶ ሄኖክ የግንቡ ግድግዳ በሲሚንቶ የለበሰውን ጣሪያ ክብደት መሸከም ባለመቻሉ ለጉዳት መጋለጡን አንስተዋል፡፡ ይህ በሲሚንቶ የለበሰው ጣሪያ ተነስቶ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ መሥራት እንደሚገባ ነው አስጎብኝው የገለጹት፡፡ የአጼ እያሱ ቤተ መንግሥትም ጣሪያ በመፍረሱ የግንቡ የውስጥ ክፍል ጭምር ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀበት ይገኛል፡፡ አስጎብኝው እንዳሉት የጎንደር አብያተ መንግሥታት በ1971 ዓ.ም ከተመዘገበ ጀምሮ ሳንድሮ አንጀሎኔ በሚባል ጣሊያናዊ አርክቴክት አንድ ጊዜ ከተደረገው ጥገና ባለፈ ጥገና አልተደረገም፤ በዚህም ምክንያት ታሪካዊው ቤተ መንግሥት አደጋ ተጋርጦበታል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት ወደ ከተማዋ ከመጡ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 1 ቢሊዮን ብር በከተማዋ ኢኮኖሚ ውስጥ ገቢ ማስገኘቱን ከተማ አስተዳደሩ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ታዲያ ይሕን ያህል ገንዘብ በከተማዋና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አቅም መፍጠር ከተቻለ እንዴት ይህንን የሀገር ቅርስ መታደግ አቃተን የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችል ይኾናል፡፡ ይህ ጥያቄ ለሄኖክም እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቶ ቻላቸው ዳኛቸው ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) እንደገለጹት የፋሲል ግንብ በ1971 ዓ.ም የተደረገለት ጥገና ቅርሱን ከ40 ዓመታት በላይ አሻግሮ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ አድርሷል፡፡ በአርባ ዓመታት ውስጥ በየጊዜው በተናጠል ከሚደረግ ትንንሽ ጥገናዎች ውጭ በተሟላ መንገድ የጥገና ሥራ ተደርጎላቸው እንደማያውቅ ነግረውናል፡፡

በጎንደር የሚገኙና በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የቅርስ እንክብካቤ ለማድረግ ከተማ አሥተዳደሩ ከዓለም አቀፍ ቅርሶች አሥተዳደር፣ ከፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በመኾን ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ ሂደቱ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ነው የነገሩን፡፡
ኀላፊው እንዳሉት ጥናቱ ተጠናቅቆ እንክብካቤ እስኪደረግላቸው ድረስ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከተማ አሥተዳደሩ ቅርሶችን የዝናብ መከላከያ ፕላስቲክ የማልበስና ሌሎች ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፤ በቀን ብቻ የነበረውን ጉብኝት በማታ ጭምር ክፍት ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው አራት ትራንስፎርመሮችን በነጻ መስጠቱን አንስተዋል፡፡

አቶ ቻላቸው የዝርጋታ ሥራ ለማከናወን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር ጥናት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ጥናቱ እንዳለቀ በሚመለከተው አካል የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲገባ ተደርጎ ማታ ጭምር ለጉብኝት ክፍት እንደሚደረግ ነግረውናል፡፡ በቅርሱ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥርን የተሸርካሪ ፍሰት ለመገደብ ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየኢትዮ- ቻይና በወታደራዊ ዲፕሎማሲና ትብብር ከፍተኛ ዕድገት ላይ መድረሱን ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
Next articleበህገ ወጥ የዶላር ዝውውርና በሃዋላ የተጠረጠሩ 70 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።