
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) ታሪክ የማስተዋዎቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የህያው የጥበብ ጉዞ አባላት ተናገሩ፡፡
“6ኛው ህያው የጥበብ ጉዞ በታሪካዊቷ የሸዋ ምድር’’ በሚል መሪ ሐሳብ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ታሪካዊ እና የመስህብ ሥፍራዎች ጉብኝት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ጥቅምት 5/2012 የተጀመረው ጉብኝቱ እስከ ጥቅምት 10/2012 ይቀጥላል፡፡ በጉዞው ከ16 የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች እና ደራሲያን እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የጉብኝቱ ዓላማ ታሪካዊ እና የመስህብ ስፍራዎችን በማዎቅ ሁሉም በየተሰማራበት የሙያ ዘርፍ ለትውልድ የማሳወቅ ኃላፊነትን እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡
ቡድኑ የጉብኝቱን መነሻ ያደረገው በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ከሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎች ነው፡፡ መንዝ ማማ ምድር ላይ ንዋዬ ቅድሳትን ከወራሪ እና ከጥቃት ለመከላከል ያገለግል የነበረውን ‹አፍሮ አይገባ› የተባለውን ታሪካዊ ዋሻ፣ ጥንታዊ የቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና በውስጡ የሚገኘውን ጥንታዊ ሀገር በቀል ደን ጎብኝተዋል፡፡ ሐገረ ማርያም ከሠም ወረዳ ላይም ኮረማሽ ቀበሌ የሚገኘውን የዳግማዊ ምኒሊክ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ጎብኝተዋል፡፡ ቀጣዩ መዳረሻቸው ደግሞ መንዝ ላሎ ላይ የሚገኙት ዘብር ገብርኤል ገዳም እና የአብነት ትምህርት ቤት ነበሩ፡፡
ጋዜጠኞች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ሞጃና ወደራ፣ አንኮበር እና መንዝ ጌራ ምድር ላይም ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝተዋል፡፡
አስተያዬታቸውን ለአብመድ የሰጡ የቡድኑ አባላት ሰሜን ሸዋ ዞን የበርካታ ታሪካዊ ቦታዎች መገኛ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አካባቢው በውስጡ የያዛቸው ታሪኮች እና የመስህብ ስፍራዎች ለሕዝብ አለመተዋዎቃቸውንም ታዝበዋል፡፡
አካባቢው በታሪካዊነቱ ልክ የመንገድ፣ የመብራት እና የውኃ መሠረተ ልማት እንዲሟላለት ባለመደረጉ ታሪካዊ እና የመስህብ ቦታዎች በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተዋወቁ፣ ኅብረተሰቡም ተጠቃሚ አለመሆኑን የጉብኝቱ አባላት ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ለችግሮቹ አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት ታሪክ ተዳፍኖ አንዳይቀር፣ የኅብረተሰቡ ሕይወትም እንዲሻሻል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ “የሸዋ ታሪክ የእኛ ታሪክ ነው፤ ሸዋን ሳናለማ ኢትዮጵያን አለማን ማለት አንችልም’’ ብለዋል የህያው የጥበብ ጉዞ ተጓዦች፡፡ ሸዋ ትክክለኛው ኢትዮጵዊነት የሚንጸባረቅበት ቦታ ስለመሆኑም መስክረዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት ሁሉ አንድ አደራ ተቀብለዋል፤ በየሙያ መስካቸው ትክክለኛ ታሪኩን ለትውልድ የማስተማር አደራ፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ