
ሐምሌ 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጨለማ ዘመን ተመኙላት የብርሃን ዘመን ገለጠች፣ ጦር አዘመቱባት ጠላቶቿን አደቀቀች፣ ገብሪልን አሏት እርሷ አስገበረች፣ እናንበርክክሽ አሏት በክንዷ አንበረከከቻቸው፣ ምድሯን ለመርገጥ የመጡትን ቀጣቻቸው፣ በሸለቆዎቿ፣ በሸንተረሮቿ ጣለቻቸው፡፡
ሕዝብ ኹሉ እርሷን ተስፋ አድርጎ ኖሯል፣ በጨለማ ዘመን እየኖረ የብርሃን ዘመን ይመጣ ዘንድ በተስፋ ጠብቋል፤ የተስፋዋ ብርሃን ከእርሷ ዘንድ ይወጣልና፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ጠበቋት፣ ተስፋችን፣ መመኪያችን፣ አለኝታችን አሏት፡፡ ከእርሷ ዘንድ ነጻነት፣ ከእርሷ ዘንድ አንድነት፣ ከእርሷ ዘንድ አሸናፊነት አለና፡፡
በጨለማ የሚኖሩት ተስፋ ሳይቆርጡ ጠበቋት፣ አንቺ የተስፋ ምድር ኾይ በፈጣሪሽ ትተማመኛለሽ፣ በአንድነትሽ ትታወቂያለሽ፣ ለምስክር ተቀምጠሻል፣ ለአሸናፊነት ተፈጥረሻል፣ ለድል አድራጊነት ተመርጠሻልና ድረሽልን ሲሏት ኖሩ፡፡
የጠፋባቸውን መንገድ እንድታሳያቸው፣ መቅረዙን እንድታበራላቸው፣ የተጠፈሩበትን እንድትበጣጥስላቸው አብዝተው ጠየቋት፡፡

በችግር ውስጥ የነበሩት በሚለምኑበት፣ የእርሷን መምጣትና ብርሃን መስጠት በሚጠባበቁባት ዘመን ታዲያ ጠላቶች ለምልክት የተቀመጠችውን ሀገር ብርሃኗን አጥፍተው በጨለማ ያኖሯት ዘንድ ይታትሩ ነበር፡፡ እርሷ ብርሃኗን ከተነጠቀች ተስፋ ያደረጉት ተስፋቸውን ያጣሉ፣ ብርሃን የጠበቁት በጨለማ ዘመን ይኖራሉ፣ ድረሽልን ሲሏት የነበሩት ደራሽ ያጣሉ፡፡
እርሷም አንድም የራሷን ብርሃን ከፍ አድርጋ ለማብራት፣ ኹለትም ተስፋ ላደረጉባት ተስፋ ለመኾን ልጆቿን በአንድነት ሰባስባ ተነሳች፡፡ ተስፋ ሲያደርጉበት የቀረ፣ እምነት ሲጥሉበት እምነቱን ያጎደለ፣ ቃሉን የበላ፣ ቃል ኪዳኑን ያላላ ነውር መኾኑን ታውቃለችና ተስፋ ለጣሉባት ልትደርስላቸው፣ የጨለማውን ካባ አውልቃ ብርሃን ልታለብሳቸው ቆርጣ ተነሳች፡፡
ጠላቶቿም የጥቁሮችን ምድር በጨለማ ሊያስውጡት፣ እንደ አሻቸው አድርገው ሊገዙት አሰፈሰፉ፡፡ በጥቁሮች ምድር ኹሉ የሚገታቸው፣ ሞትን ንቆ የሚመታቸው፣ ከእርምጃቸው የሚያስቆማቸው፣ ከድንበር የሚመልሳቸው ኃይል አላገኙም እና እርሷንም እንደ አሻቸው ያደርጓት ዘንድ ቋመጡ፡፡
ጠላቶች በጥቁሮች ምድር የመጨረሻዋ ጀንበር ስታዘቀዝቅ፣ ቆይታም ላትመለስ ስትጠልቅ ለማየት ቸኩለዋል፡፡ እርሷን ተስፋ ያደረጉት ደግሞ የመጨረሻውን ነገር ለማየት ጓጉተዋል፣ ተስፋችን ያሏት ብርሃን ትጠልቅ ይኾን ወይንስ በእኛም ላይ ትዘልቅ ይኾን በሚል ከባድ ሐሳብ ተጨንቀዋል፡፡ አቤቱ ተስፋችን ናት እና እርዳት፣ ጠላቶቿን አስገዛላት፣ ድልን ስጣት እያሉ ነበር፡፡
ለምን ካሉ በእርሷ ሰማይ ስር ያለችው ጀንበር ከጠለቀች፣ ብርሃኗንም ከከለከለች፣ እነርሱ የብርሃን ዘመን ሳያዩ በጨለማ ውስጥ ይኖራሉና፡፡ ሀገር እያላቸው ሀገር አልባዎች፣ ማንነት እያላቸው ማንነት የለሾች፣ ሃብት እያላቸው ድሃዎች ኾነው ይኖራሉና፡፡ ተስፋ ለሚያደርጉባት ተስፋቸው፣ መድረሻ ላጡት መጠለያቸው፣ ለተራቡት መጉረሻቸው፣ ለተጠሙት መጠጫቸው፣ መንገድ ለጠፋባቸው መሪያቸው የኾነች እመቤት ኢትዮጵያ ተስፋ የሚያደርጉባትን አታሳፍርም፣ አሰፍስፈው ለመጡትም አትደፈርም፡፡

የጥቁሮችን ጀንበር ለማጥለቅ የመጣውን ወራሪ በልጆቿ የተባበረ ክንድ መታችው፣ የወራሪዎችን የድል ዜና ለመስማት ሲጓጓ የኖረውን አሳፈረችው፣ አስደነገጠችው፡፡ ተስፋ ላደረጉባት ተስፋ ኾነቻቸው፣ ሰንሰለቱን ፈታችላቸው፣ ማሰሪያውን በጣጠሰችላቸው፣ መንገዱን አሳየቻቸው፣ ብርሃኗን አበራችላቸው፡፡ ምኞታቸው ደረሰ፣ ጸሎታቸውም ሠመረ፡፡
ጥቁሮች ኹሉ ኢትዮጵያን ነጻ ሀገር የኾነች፣ ነጻነትን ለሌሎችም ያጎናፀፈች፣ የነጻነት እናት፣ የኩራት ምልክት ይሏታል፡፡ ለምን? ነጻነትን ሰጥታቸዋለች፣ ኩራትና መመኪያ ኾናቸዋለችና፡፡ ክፉዋን የሚመኙ ፍስሐዋን ያያሉ፣ መለያየቷን የሚናፍቁ፣ አንድነቷን ይመለከታሉ፡፡ ለምስክር የተቀመጠን ማን ያሸንፈዋል፣ በአንድነት የተነሳን ማን ይረታዋል?
ኢትዮጵያ ጠላቶቿ አታደርጊም ያሏትን እያደረገች፣ አትችለውም የተባለችውን እየቻለች፣ አታልፈውም የተባለውን እያለፈች፣ አታሸንፈውም የተባለውን እያሸነፈች፣ ወዳጆቿን በፍቅር፣ ጠላቶቿን በጦር እያንበረከከች ዘመናትን የተሻገረች ድንቅ ሀገር ናት፡፡
ግርማዊ ቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ “በጠነከረ መሠረት ላይ የታነጸን ቤት ዝናብ ቢዘንብ፣ ጎርፍ ቢጎርፍ፣ ነፋስ ቢነፍስ፣ ገፍተው ሊጥሉት አይችሉም” ብለው ነበር፡፡
በጠነከረ አንድነት የተመሠረተን ጠላት አይረታውም፣ ኾኖለት አይደፍረውም፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድ ስለኾኑ ነጻ ሀገር አቆይተዋል፣ አንድ ስለኾኑ ጠላቶቻቸውን ቀጥተው መልሰዋል፣ አንድ ስለኾኑ ተስፋ ለጣሉባቸው ደካሞች ተስፋ ኾነዋል፡፡ አንድ ስለኾኑ ታሪካቸውን ከፍ አድርገው ጽፈዋል፣ አጽፈዋል፡፡
በተመቸም ባልተመቸም ዘመን ኢትዮጵያውያን እንድ ኾነዋል፣ ጠላት በተነሳባት ዘመን ኹሉ በአንድነት ተነስተው ድል አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያን ሲከፋቸው አልተዋትም፣ ሲደላቸው አልተጠጓትም፡፡ ይልቅስ ሞት በበዛበት፣ መከራ በጸናበት፣ ደም በሚፈስስበት፣ አጥንት በሚከሰከስበት፣ አንድ ነብስ በሚሰጥበት የመከራ ዘመን አብዝተው ይወዷታል፡፡ ለክብሯ ይሞቱላታል፣ ይቆስሉላታል፡፡ ሞትን ይንቁላታል እንጂ፡፡
እነኾ ዛሬም ኢትዮጵያን የሚፈትኗት፣ መከራዋን እና ምጧን የሚያበዙባት ጠላቶች ተበራክተዋል፡፡ የጠነከረውን አንድነታቸውን የሚፈታተኑ ጠላቶች ሞልተዋል፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ፣ ኢትዮጵያዊነትን እንዲረሳ የሚውተረተሩት ብዙዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሲያለቅሱ እነርሱ ይስቃሉ፣ ኢትዮጵውያን ሲከፉ እነርሱ ይደሰታሉ፣ ኢትዮጵያውያን ሲዳከሙ እነርሱ ኀያል ይኾናሉ፣ የእርሷ የኾነውን ለመብላት፣ የእርሷ የኾነውን ለመውሰድ ይቻኮላሉ፡፡

ኢትዮጵያዊነት በመከራ ጊዜ የሚረሱት፣ ሞትና መሰደድ ሲመጣ በቃኝ ብለው የሚያወልቁት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተመቸ ዘመን የሚለብሱት ባልተመቸ ዘመን የሚጥሉት ካባም አይደለም፡፡
ኢትዮጵያዊነት በመከራ ዘመን መጽናት፣ በጨለማ ዘመን ማብራት፣ በድቅድቅ ጨለማ እያበሩ መውጣት፣ ደምና አጥንትን ሰጥቶ ድል ማምጣት፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት በፈተናዎች መጠንከር፣ በአስቸጋሪ ዘመን በትዕግስት መሻገር፣ በክፉ ዘመን በአንድነት ማበር፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት ለዘላለም የሚያጠልቁት፣ እስከ ሞት ድረስ የሚወዱት፣ ከምንም ከማንም በላይ ከፍ አድርገው የሚያስቀምጡት ነው፡፡
የቀደሙትን ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር የሚያስጠራቸው አንድነታቸው፣ ጀግንነታቸው፣ ኢትዮጵያዊነታቸው፣ ጽናታቸው እና የሀገር ፍቅራቸው ነው፡፡ ፍቅር ባይኖራቸው ኖሮ በበጎ አይነሱም፣ ከመቃብር በላይ አይወሱም ነበር፡፡ ዛሬም በአንድነት ጽኑና ጠላቶች ይግረማቸው፣ አንድ ኹኑና ጠላቶች ይጭነቃቸው፡፡ ጨለማዋን ለሚመኙ ብርሃኗን፣ ፍስሐዋን አሳዩዋቸው፡፡
ኢትዮጵያ ኾይ ክፉዎች ወደ እግርሽ ይወድቃሉ፣ በሰይፍሽ እየተመቱ ያልቃሉ፣ ታሪክ ሳይኖራቸው ብኩን ኾነው ይቀራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኾይ አንቺን የሚወዱሽ እና የሚያከብሩሽ ከፍ ብለው ይኖራሉ፣ ይከበራሉ፡፡ መከራሽን የሚመኙ ፍስሐሽን ያያሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
