
“ፋሽሽቶች የሀገራችንን አርበኛ ሽፍቶች ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሽሽት ነው”
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እውነትን የያዘ ሞት አያስፈራውም፣ ጨለማ አያስቆመውም፣ የጠላት ድንፋታ አያስደነግጠውም፣ ጎዳናዎች አይችሉትም፣ የጠላት በትሮች አይመልሱትም፡፡ እውነት መንገዷ ጠባብ ናት፣ እውነት አድካሚ ናት፣ እውነት በመከራ የተመላች ናት፡፡
ሀገር ማፍቀር እንዴት ነው? ሀገርን መውደድ እስከ ምን ድረስ ነው? ሀገርን ማክበር እስከ የት ነው? ሞትን አብዝተው ናቁት፣ ውሸትና ማስመሰልን አብዝተው ተጸየፉት፣ ስለ እናት ሀገራቸው፣ ስለ ተፈጠሩባት፣ አብዝተው ስለሚወዷት ሀገራቸው ሲሉ መከራውን ታገሱት፣ መራራውን የሞት ጽዋ ተጎነጩት፡፡
ማን ሀገሩን ወድዷል፣ ማን ለቃሉ አድሯል፣ ማን ቃሉን በተግባር ኖሯል፣ ማን ስጋውን ገድሎ ነብሱን አስከብሯል፡፡ የታደሉት ስለ እውነት ሞተው ስማቸውን ከመቃብር በላይ ያስቀምጣሉ፣ ታሪካቸውን በማይጠፋ ቀለም ያስቀርጻሉ፣ ዓርዓያ ኾነው በትውልድ ቅብብሎሽ ይጠራሉ፣ ይመሰገናሉ፡፡
ብዙዎችን ሞት ያስፈራቸዋል፣ ጥቂቶችን ደግሞ ሞት ራሱ ይፈራቸዋል፣ ለምን ካሉ ከሞታቸው ይልቅ ሥራቸው፣ ከሞታቸው ይልቅ ቃላቸው፣ ከሞታቸው ይልቅ እውነታቸው፣ ከሞታቸው ይልቅ ጽናታቸው፣ ከሞታቸው ይልቅ መልካም ተግባራቸው፣ ከሞታቸው ይልቅ ቃል ኪዳናቸው ሲነገር ይኖራልና፡፡
ፈጣሪ ለመልካም ነገር አዘጋጃቸው፣ በመልካሙ መንገድም መራቸው፣ ወደዳቸው፣ ስለ እውነት ይኖሩ ዘንድ ጠበቃቸው፡፡ ሀገራቸውን አብዝተው ወደዷት፣ ስለ ፍቅሯ ሞቱላት፣ ሃይማኖታቸውን በጽናት ጠበቋት፣ የአንደበታቸውን ቃል እንዳይናገሩ ሲገደሉ በደማቸው ሰበኩላት፣ በአጥንታቸው መሰከሩላት፡፡ በሞታቸው ውስጥ እውነት፣ በሞታቸው ውስጥ ጽናት፣ በሞታቸው ውስጥ ታማኝነት፣ በሞታቸው ውስጥ ታላቅ አባትነት አለና፡፡
የግብጽ ቤተክርስቲያን ረዘም ላለ ዘመን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን ስትልክ ነበር፡፡ ከእስክንድሪያ የሚመጡት ጳጳሳትም በሀገረ ኢትዮጵያ አባት ኾነው ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቅዱሳን የሚወለዱባት፣ ፈጣሪ አብዝቶ የሚወዳት፣ ስሙ ሳይቋረጥ የሚመሰገንባት፣ ምስጋናና ውዳሴ የሚቀርብባት ኾና ሳለች ለምን ከምድሯ የተፈጠረ ጳጳስ አጣች የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ነበረ፡፡
የጥያቄው መመለሻ ዘመንም ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያውያን አበውም ለጵጵስና ታጩ፡፡ ለጵጵስና ከታጩት አበው መነኮሳት ውስጥ ታላቁ አባት አቡነ ጴጥሮስ አንደኛው ነበሩ፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ገና ከልጅንታቸው ጀምሮ እውቀት ወደሚፈስስባቸው፣ ሃይማኖት ወደ ሚሰበክባቸው ገዳማትና አድባራት እየተዘዋወሩ ከሚፈስሰው እውቀት ጠጥተዋል፣ ከሚቆረሰው የእውቀት ኅብስት በልተዋል፡፡ በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ እና በሌሎች ገዳማትና አድባራት እየተመላለሱ ተምረዋል፡፡

ገና በልጅነት እውቀት የዘለቃቸው፣ ፈጣሪ አብዝቶ የባረካቸውና የወደዳቸው አባት ለታላቁ ክብር ተመረጡ፡፡ በግንቦት 18/1921ዓ.ም በእስክንድሪያው መንበረ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስና ተቀበሉ፡፡ ወደ ሀገራቸውም ተመለሱ፡፡ ወደ ሀገራቸው በተመለሱም ጊዜ ʺ አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው ተሾሙ፡፡
ዘመን ዘመንን እያስከተለ መጣ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በታላቅ አባታዊ ፍቅር ሃይማኖታቸውን እያስተማሩ፣ ምዕምናንን እየባረኩ ነበር፤ በዓድዋ የመረረ የሽንፈት ጽዋ የተጎነጨችው ኢጣሊያ ለዳግም ወረራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች፡፡ ኢጣሊያም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተች፡፡ ኢትዮጵያውያን ላይ በደል አደረሰች፣ የማይደፈረውን ደፈረች፡፡ ይህን ያዩት ታላቅ አባትም መስቀላቸውን ይዘው ተነሱ፡፡ ለሀገራቸው ፍቅርና ክብር የሚዋደቁትን ኢትዮጵያውያንን እየባረኩ አይዟችሁ አሏቸው፡፡ በጸሎት ረዷቸው፡፡ ታላቁን አባት ያዩ ኢትዮጵያውያንም በጠላቶቻቸው ላይ አብዝተው ተቆጡ፡፡
ጦርነት በኢትዮጵያ ምድር ተቀጣጠለ፡፡ ለእናታቸው ክብርና ፍቅር የተነሱ ኢትዮጵያውያን ከጠላት ጋር ተናነቁ፡፡ መከራውን እና ስቃዩን ፈጽመው ናቁ፡፡ ዱርና ገደሉ፣ ዋሻና ሸለቆው፣ ሜዳና ሸንተረሩ ጥይት ሳይሰማበት፣ ጀግና ጠላቱን ሳይጥልበት አልውል አለ፡፡
ብጽዕ አቡነ ጴጥሮስ በጸሎትና በትምህርት ሀገሬውን ያበረታቱታል፣ እንኳን ታላቅ አባት አስተምረውት ለወትሮው ለእናት ሀገሩ እንቅልፍ የማያውቀው የሀገሬው ሰው እሳት ኾነ፡፡
1928 ዓ.ም ጦርነቱ በየቦታው እየተካሄደ የክረምቱ ወቅት ገባ፡፡ የሐምሌ ሰማይ ጥቁር ደመና እያዘለ ዝናቡን እየደፋው ነው፡፡ ብርድና ዝናብ በበዛበት፣ ጭቃና ጭጋግ በበረታበት፣ ወንዞች በሞሉበት፣ መንገዶች ሁሉ በጥሻ በሚሸፈኑበት በወረሃ ሐምሌ የኢትዮጵያ አርበኞች ከጠላት ጋር ይፋለማሉ፡፡ አርበኞቹም በከፍተኛ ጀግንነት አዲስ አበባን ከጠላት እጅ ለማስለቀቅ ይፋለሙ ነበር፡፡ ጠላትንም ያስጨንቁት ነበር፡፡
ኢጣሊያ ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ሸብረክ አልልም ያሉትን ጳጳስ ጠልታቸዋለች፡፡ በዚህ ትንቅንቅ መካከልም አቡነ ጴጥሮስ ከጠላት እጅ ወደቁ፡፡ ጳጳሱም ለግራዚያኒ ተላልፈው ተሰጡ፡፡ ሀገሬን አትንኩብኝ ከማለት ውጭ ሌላ በደል ያልተገኘባቸው ብፁዕ አባት በጠላት ተያዙ። ኢትዮጵያዊያንም ተስፋችን፣ መካሪያችን፣ አባታችን፣ መሪያችን፣ አስተማሪያችን፣ ባራኪያችን የሚሏቸው በጠላት በመያዛቸው አብዝተው ተጨነቁ፤ ተጠበቡ፡፡
ዲያቆን መርሻ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍቸው ፓጃሊ የተሰኘውን የኮርየሪ ዴላሴራ ጋዜጠኛ ዋቢ አድርገው ሲገልጹ ʺ ሐምሌ 22 ቀን 1928 አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ ያለ መልካቸው ጠየም ያለ አዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብስ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚሕ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምጽዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም ካህናቱም ኾኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያን መንግሥት ገዢነት አምነው ሲቀበሉ እርሰዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎትን አፈንጋጭ ኾኑ? ሲል ጠየቃቸውʺ አቡነ ጴጥሮስም ተናገሩ፡፡ እንዲሕም አሉ፡፡ʺአቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚሕ ስለ ሀገሬና እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚሕ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪየ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡

ጳውሎስ ኞኞም የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው የኮርየሪ ዴላሴራ ጋዜጠኛ ፓጃሊን ዋቢ አድርገው ሲገልፁ ʺጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ፡፡ ይሕ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ፈጠረ፡፡ ጉዳዩም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ” ብለዋል፡፡ መስቀል የያዙት ጳጳስ የሞቱን ፍርድ በዝምታ አዳመጡ፡፡ ወደ መገደያ ቦታውም ወሰዷቸው፡፡ ጳጳሱም መገደያቸው ቦታ ሲደርሱ ፊታቸውን አሟሟታቸውን ሊያይ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ አዙረው ቆሙ፡፡ እርሳቸው ሞት ይፈሩ ይመስል ሊገድሏቸው እያዘጋጇቸው ዓይንዎን እንዲሸፈኑ ይፈልጋሉን? ብለው ጠየቋቸው፡፡ እሳቸው ግን እንደፈለጋችሁ አድርጉ ለእኔ ማንኛውም ስሜት አይሰጠኝም አሉ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ ዜና ቤተክርስቲያንን ዋቢ አድርገው ሲገልጹ ʺ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱንም አቅጣጫ በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ ፋሽሽቶች የሀገራችንን አርበኛ ሽፍቶች ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሽሽት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን” አሉ፡፡
የመከራዋ ሰዓት ደረሰች፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ስለ እውነት ኖረው ወደ እውነተኛው ፈጣሪያቸው ሊሄዱ ነው፡፡ ለግዳይ ተመቻችተው ቆሙ፡፡ ገዳይ ወታደሮች ታዘዙ፡፡ የሕዝቡ የልብ ምት ጨምሯል፡፡ ምላጫቸውን ረገጡ፡፡ እልል እየተባለ የሚታጀቡት፣ የወርቅ ጥላ የሚለብሱት፣ ታላቅ አባት በግፍ አሸለቡ፡፡ ምድር ተጨነቀች፡፡ የምትለውን አጣች፡፡ የገዳይ ነብስ ተቅበዘበዘች፣ የእርሳቸው ነብስ ግን ስለ እውነት ደስ ተሰኘች፡፡ ያቺ ቀንም ሐምሌ 22 ነበረች፡፡
ስለ እውነት ሞትን ንቀዋል፤ ሀገርን በቃል ኪዳን አሥረዋል፣ በደም አጽንተዋል፣ ምድሯ ጠላት እንዳትቀበል ገዝተዋልና ክብር ለእርሰዎ ይሁን፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
