
ሐምሌ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍ ባለ የታሪክ ማማ ላይ ተቀምጣለች፣ በማይጠፋ ብዕር ተቀልማ፣ በማያረጅ ብራና ላይ ተከትባለች፣ እንዳይደረስባት ኾና ቀድማለች፣ እንዳትናወጽ ኾና ፀንታለች፣ ለድንቅ ነገር፣ በድንቅ ጥበብ ተፈጥራለች፣ ለምስክር ተቀምጣለች።
ደም አፅንቷት፣ አጥንት አጠንክሯት፣ ጀግንነት ጠብቋት፣ አንድነት አስከብሯት ኖራለች። ለክብር ተፈጥራለች፣ በክብር ኖራለች፣ በክብር ትኖራለች፣ ለአሸናፊነት ተፈጥራለች፣ በአሸናፊነት ኖራለች፣ በአሸናፊነት ትኖራለች። የገፏት ወድቀዋል፣ የጠሏት አልቀዋል፣ የነኳት ተቃጥለዋል።
እርሷን ነክቶ ያልተሸነፈ፣ ከእርሷ ጋር ገጥሞ ያልተሰየፈ የለም። ጀንበሯ ጠለቅችባት ሲባል ፈክታ ትወጣለች፣ ጨለማ ጋርዷት ለዘላለም ተደበቀች ሲባል ብርሃኗን ፈንጥቃ ከእርሷ አልፋ በአሻገር ታበራለች፣ ተሸነፈች፣ ለጠላቶቿ እጅ ሰጠች፣ እንዳትነሳ ኾና ተንኮታኮተች ስትባል ከድል ላይ ድል ደራርባ ትወጣለች፣ ጠላቶቿን እጅ ታስነሳለች፣ ከእግሯ ሥር ጥላ ታሰግዳለች።
በእርሷ ሰማይ የወጣችው ጀንበር አልጠለቀችም፣ በደመና አልተጋረደችም፣ በጨለማ አልተከበበችም፣ ብርሃኗን አልከለከለችም። የእርሷ ጀንበር አትጠልቅም፣ በጨለማም አትወጣም። ለእርሷ የተሰጠችው ቃል ኪዳን ዘላለማዊት ናት፣ በመከራ ዘመን የማትለወጥ፣ ፈተናዎች በበዙ ጊዜ የማትናወጥ።
የእርሷ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በምድር ይውለበለባል፣ በየኮረብታዎቹ ኹሉ ያስጌጣል ያጌጣል፣ በልብ ውስጥ ይውለበለባል። ሠንደቋ ከልጆቿ ደምና አጥንት ጋር አብሮ ተሸምኗል፣ በየጎዳናው በተውለበለበ ቁጥር ልጆቿ ስጋና ደማቸው ነውና አብረው ይከንፋሉ፣ የደስታ እንባ ያነባሉ።
አበው ያለ ድካምና ያለ እረፍት ስለ እርሷ ሰላም ይማፀናሉ፣ ከሰማይ ወደ ምድር በረከትና ረድዔት ይወርድ ዘንድ ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ፣ ሳያስታጉሉ ለፈጣሪያቸው ምሥጋና ያደርሳሉ፣ አቤቱ ጠብቃት፣ ጠላቶቿን ፈጥነህ አስገዛላት፣ ለልጆቿ ፍቅርና ሰላምን አድልላት፣ አንድነት ስጥላት፣ ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት አድርግላት፣ ለዘላለም ጠብቃት እያሉ ይማፀናሉ።
ፈጣሪም የቃል ኪዳኗን ሀገር ያፀናታል፣ ይጠብቃታል፣ በረከትና ፍቅር ይሰጣታል፣ ጠላቶቿን ይቀጣላታል፣ በጨለማ ውስጥ በብርሃን እየመራ ያሻግራታል፣ ከጠላቶቿ አልቆ ያስቀምጣታል። ቅዱሳን ሞልተውባታል፣ ጠቢባን ፈልቀውባታል፣ ጀግኖች ተወልደውባታል፣ ጠላት ይፈራታል፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ስሟን ይጠሯታል፣ ወዳጅ ያከብራታል፣ ፈጣሪ አብዝቶ ይወዳታል፣ በኃይሉም ይጠብቃታል – ድንቋ ምድር ኢትዮጵያ።
ኢትዮጵያ እልፍ ጀግኖች ሲወለዱላት፣ እልፍ ጠላቶች ይወለዱባታል፣ እልፍ ደጎች ሲተከሉላት፣ እልፍ ጠላቶች ይነሱባታል፣ አንደኛውን መከራ ስታልፈው ሌላ መከራ ይጠብቃታል፣ አንደኛውን ተራራ ስትወጣው ሌላ ተራራ ይመጣባታል፣ የከፋውን ማዕበል ስትሻገር ሌላ ማዕበል ያማታታል። ዳሩ በዘመናት ቅብብሎች ጠላቶቿ በልጆቿ ላይ ድል አልተቀዳጁም፣ ኢትዮጵያን ገፍተው አልጣሉም፣ አይጥሉምም።
በሚጠሏት ፊት ትነግሣለች፣ በሚንቋት ፊት ትከበራለች፣ ጨለማዋን በሚመኙላት ፊት ብርሃን ትፈነጥቃለች፣ በልጆቿ ጀግንነት ጠላቶቿን እያስለቀሰች፣ ወዳጆቿን እያስፈነደቀች፣ ግርማ ባለው ኩራት ሠንደቋን ከፍ አድርጋ ትጓዛለች።
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በቀደመበት ኹሉ ድል አለ። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በዋለበት ኹሉ ግርማና ክብር አለ። ሠንደቋ ለጠላት ያስጨንቃል፣ ለወዳጅ ያስከብራል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የዓለም ሀገራት በተሰበሰቡበት፣ ዓይኖች ኹሉ ባነጣጠሩበት፣ ክብር እና የሀገር ፍቅር ታላቅ ሥፍራ በሚሰጥበት፣ ጀሮዎች ኹሉ ለመስማት በሚጓጉበት፣ አንደበቶች ኹሉ ለመናገር በሚቻኮሉበት በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ተውለብልቧል። በሚጠሏትም በሚወዷትም ፊት ከፍ ብሏል።
የኢትዮጵያ ማሕጸን ያፈራቸው፣ የኢትዮጵያ ክብር እና ፍቅር የገባቸው፣ ጀግንነት እና አሸናፊነት ከአባቶቻቸው እና እናቶቻቸው የወረሱት፣ በኩራት ገስግሰው በድል የተመለሱት አትሌቶች ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋታል። ስሟን በከበረ መዘገብ ላይ አስመዝግበዋታል።
ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ከፍ ብሎ እንዲወለበለብ በማይፈለግበት ሠማይ ሥር በኩራት አውለብልበውታል፣ በአሸናፊነት ለዓለም ኹሉ አሳይተውታል። በድላቸው የደበዘዘ የመሰለው ኢትዮጵያዊነት ፈክቷል፣ የላላ የመሠለው አንድነት ፀንቷል፣ የቀነሰ የመሰለው ፍቅር በዝቷል፣ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ካዳር ዳር በእንባ በታጀበ ድምፅ ተጠርቷል።
ኢትዮጵያዊነት አያረጅም፣ ኢትዮጵያዊነት አይደበዝዝም፣ ኢትዮጵያዊነት በጨለማ አይከበብም፣ ኢትዮጵያዊነት በጠላት እጅ አይነካም፣ ኢትዮጵያዊነት አይጎድፍም፣ ኢትዮጵያዊነት አይሸራረፍም፣ ኢትዮጵያዊነት ከክብሩ አይዛነፍም። ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው፣ ኢትዮጵያዊነት ምስጢር ነው፣ ኢትዮጵያዊነት የማይመረመር እፁብ ነው።
“መከራው ቢበዛ ችግሩ ቢረቅቅም
ከፍ ማለት እንጂ ዝቅታን አታውቅም” ኢትዮጵያ መከራው ቢበዘባት፣ ችግሩ ቢደራረብባት፣ ክፉዎች ቢነሱባት፣ ጠላቶች ቢበረክቱባት፣ ስቃይና በደል ቢያደርሱባት፣ ከፍ ትላለች እንጂ ዝቅ አትልም። ለምን ካሉ እርሷ ከፍታ እንጂ ዝቅታ አታውቅምና።
ዓለም በኢትዮጵያን የሀገር ፍቅር ተደምማለች፣ በልጇቿ ጀግንነት ተገርማለች፣ በድል አድራጊነቷ አጀብ ብላለች። ኢትዮጵያም በድል አድራጊነት እፁብ ድንቅ ተሰኝታለች። ጀግኖቹ የተበተነ የመሰለውን ሰብስበውታል፣ የራቀ የመሰለውን አቅርበውታል፣ የጨለማ የመሰለውን በብርሃን መልተውታል፣ የተከዘውን በደስታ ማዕበል ውስጥ ከትተውታል፣ ተስፋ ያጣውን ተስፋ ኾነውታል። የሀገር ፍቅር ውሉ የጠፋበትን በላባቸው አረጋግጠው አሳይተውታል። የሀገር ክብር የተዛነቀበትን አጥርተው አመላክተውታል።
እነርሱ ኢትዮጵያን ብለው ሮጠው ቀድመዋል፣ ኢትዮጵያን ብለው አሸንፈዋል፣ ኢትዮጵያን ጠርተው በድል አድራጊነት ተረማምደዋል። ሠንደቋን ከኹሉም ላቅ አድርገው አውለብልበዋል። ስሟን እየጠራህ ተነስ በስሟ ድል ሞልቷል፣ ስሟን እየጠራህ ሩጥ ድል ለእርሷ ተሰጥቷል።
ቢቻልህ በተሰማራህበት ሩጥና ሀገርህን ቀዳሚ አድርጋት፣ ስሟን አስጠራት፣ ሠንደቋን ከፍ አድርገህ አውለብልብላት፣ ባይቻልህ ከሩጫዋ አታስቁማት፣ መንገዷን አትዝጋባት፣ እንዳሻት ሩጣ ታሸንፍ ዘንድ አታሰናክላት። ልጆቿን ወደ ኋላ አትጎትትባት። ከክብር አታውርዳት።
ኢትዮጵያ ኾይ ድል በስምሽ አለና ለድልሽ እንተባበራለን፣ ኢትዮጵያ ኾይ ክብር ተሰጥቶሻልና ለክብርሽ እንቆማለን፣ ኢትዮጵያ ኾይ ከኹሉም ትበልጫለሽና ምንም ሳንሳሳ ያለንን ኹሉ አንሰጥሻለን፣ ኢትዮጵያ ኾይ ጠላቶችሽ ቢበዙም ከአበው በወረስነው ቃል ኪዳን ተሳሳስረን ጠላቶችሽን እናሸንፍልሻለን፣ ኢትዮጵያ ኾይ ስምሽ ኃያል ነው ለኃያልነትሽ ሳንሰስት እንሠራለን፣ የድልሽን ነገር እንናገራለን፣ የአሸናፊነትሽንም ምስጢር እንመሰክራለን፣ ክብርና ዝናሽን እናከብራለን፣ አክብረን እንጠብቅሻለን።
እነኾ ጀግኖች ያውለበለቡት፣ ከፍ አድርገው የሰቀሉት ሠንደቅ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ይውለበለባል፣ ከፍ ብሎ ይኖራል። ጀግኖቹም ይከበራሉ። ስማቸውንም በታሪክ መዝገብ ላይ ያሰፍራሉ። ክብርና ድል የተሰጣችሁ ኢትዮጵያዊውን ኾይ እማማን ጠብቋት። በጠላቶቿ ፊት በክብር አራምዷት። ድል ኹሉ ለእርሷ ይኹን።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/