አሸባሪው ትህነግ በአማራና በአፋር ክልሎች ትንኮሳውን እንደማያቆም የአውሮፓ ኅብረት ሊያውቀው እንደሚገባ የአማራ ክልል መንግሥት አስገነዘበ።

258

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ከአውሮፓ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዶ.ር አኒቲ ዌበር ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ርእሰ መስተዳድሩ የትኅነግ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል ባደረሰው ወረራ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ገልፀውላቸዋል ። ዜጎች በጅምላ ተጭፍጭፈዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሃብትና ንብረት ወድሟል ነው ያሉት። በወራሪው ቡድን ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች ተቋማት መውደማቸውንም ገልጸዋል ። ሕዝብን በማስተባበር ተቋማትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል ።

ትህነግ አሁንም መልሶ ለመውረር ጥረት እያደረገ መኾኑንም ገልፀዋል። የሽብር ቡድኑ ለሰላምና ለውይይት ዝግጁ አለመኾኑን አንስተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ የክልሉ መንግስት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም ገልፀዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ለሰላም አማራጭ ዝግጁ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ትህነግ ግን ለሰላም አማራጭ ዝግጁ አይደለም ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳለውም ተናግረዋል ።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን አሁንም በአማራና አፋር ሕዝብ ላይ ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጀ እንደኾነና ትንኮሳ ከማድረግ እንደማይቦዝንም የአውሮፓ ኅብረት ሊገነዘበው ይገባል ነው ያሏቸው።

የሽብር ቡድኑ የአማራ የፀጥታ ኃይሎች እና የኢፌዴሪ የፀጥታ ኃይሎች በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃት እንዳደረሱ የውሽት መረጃ እንደሚያሰራጭም የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ፤ የአማራ ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ የማጥቃት አላማም ፍላጎትም የለውም፣ የትግራይ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው፣ በችግር ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ነው ብለዋል። ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳት እንዲገባ በአማራ ክልል ያሉ መግቢያዎች ክፍት መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በአማራ ክልል የራያ ፣ የዋግ፣ የጠለምትና ሌሎች አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ በመያዛቸው ዜጎች በከፍተኛ በችግር ውስጥ መኾናቸውንም ተናግረዋል ። በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችል የመግብ እና ሌሎች አቅርቦቶች እጥረት እንዳለም ገልፀውላቸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ችግር ውስጥ የወደቀው በሕወሃት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበትም ራሱ ሕወሃት ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ከሌሎች ክልሎች ጋር ለሰላም እና ለአብሮነት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ገልፀውላቸዋል። በተሠራው ሥራ በተለይም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመመለሳቸውን ተናግረዋል ።

ከአፋር ክልል ጋርም የጠበቀ ወዳጅነት መኖሩን ነው የገለፁላቸው። የአማራ ክልል ከክልሎች ጋር ምንም ችግር የለበትም፣ ቸግሩን የሚፈጥሩት የሽብር ቡድኖች ናቸው፣ የአውሮፓ ሕብረትም ክልል ከክልል ወይም በሕዝብ እና በሕዝብ መካከል ግጭት እንደሌለ ሊረዳው ይገባል፣ ችግሩ በሽብር ቡድኖች የሚፈጠር ነው ብለዋል። የፌደራል መንግሥት ማንነት ተኮር ጥቃት በፈፀሙ የሽብር ቡድኖች ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መኾኑንም አንስተዋል።

በሱዳን የተፈጠረውን ጉዳይም በሰላም ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለ ነው የተናገሩት ። የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ እየሠራች መኾኑን ያነሱት ዶክተር ይልቃል ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያ ችግሮችን ለመፍታት ሚናው ላቅ ያለ እንደኾነም ገልፀውላቸዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር በአማራ ክልል ያለውን አሁናዊ ሁኔታ መረዳታቸውን ገልጸዋል ።

የአውሮፓ ኅብረት ጦርነቱ በሰላም እንዲፈታ ፅኑ ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካላት ተሰሚነት አንፃር ሰላም መኾን እንደሚገባት ነው የተናገሩት። የአውሮፓ ኅብረት ከአማራ ክልል ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኑንም አንስተዋል። የኢትዮጵያን አንድነት እንደሚፈልጉና እንደሚያደንቁም ገልፀዋል። የአልሸባብ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ትንኮሳም አንስተዋል። ዜጎች በተረጋጋ ሕይወት እንዲኖሩ ሰላም ግዴታ እንደኾነም ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት የጀመሩትን ሂደት ያነሱት ልዩ መልዕክተኛዋ በሂደቱም ደስተኞች መኾናቸውን ገልጸዋል ።

ዜጎች በሀገራቸው ሲኖሩ ሰላምና ደኅንነት ሊሰማቸው እንደሚገባ ነው የተናገሩት ። ያደረጉት ውይይት ጠቃሚ መኾኑንም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

Previous article“ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next article“መከራው ቢበዛ ችግሩ ቢረቅቅም ፣ ከፍ ማለት እንጂ ዝቅታን አታውቅም”