
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ነገ አዲስ አበባ ይገባል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ በመድረኩ ታሪክ ትልቁን ውጤት ማስመዝገብ ችላለች።
ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ አራት ብር እና ሁለት ነሃስ በማስመዝገብ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆና ውድድሩን ጨርሳለች።
ቡድኑ ነገ ምሽት 3:00 አዲስ አበባ ሲገባ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት ተገልጿል ።
በማግስቱም በተመረጡ ዋና ዋና ጎዳናዎችና በመስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል።
የአቀባበሉ መርሐግብር ማጠቃለያ በብሔራዊ ቤተመንግስት እንደሚኾን ተገልጿል።
የሽልማት ፕሮግራሙም በዛው ይከወናል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ለአትሌቶች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ የተለያዩ ኮሚቴወች ተቋቁመው እየተሠራ ነው ብለዋል።
የቡድን ሥራ የጎላበት ኢትዮጵያዊነት ያሸነፈበት ነበር ብለዋል። ለዚህም አትሌቶችንና ልዑካኑን አመስግነዋል ።
ዳጎስ ያለ ሽልማት እንደተዘጋጀም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን