
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በክልሉ በ2014 የበጀት ዘመን በ11 ወራት የተፈጸሙትን የመልካም አሥተዳደር፣ የልማትና የማኅበራዊ ክንውኖችን ሪፖርት አድርገዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በአማራ ክልል በሚቀጥሉት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን በእጥፍ ለመጨመር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል ። በ2014/15 የምርት ዘመን 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 143 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱንም አስታውሰዋል። በዚኽም እስካሁን 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ መታረሱንም ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርተር 8 ነጥብ 25 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 4 ነጥብ 29 ሚሊዮን ኩንታል መቅረቡን ጠቁመዋል። በበጀት ዓመቱ በነባርና በአዳዲስ መስኖዎች 239 ሺህ 383 ሄክታር መሬት በማልማት 38 ሚሊዮን 508 ሺህ 700 ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እስካሁን 21ሚሊዮን 375 ሺህ 423 ኩንታል ምርት መገኘቱን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ በ8 ሺህ 38 ተፋሰሶች የሥነ አካላዊ ሥራዎች መከናወናቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል።
ለተከታታይ አራት ዓመታት የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ተግባራዊ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን በማፍላት እየተተከሉ መኾኑን ተናግረዋል። በአንድ ጀንበር ተከላ 250 ሚሊየን ችግኞችን የመትከልና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት፣ የሥጋ፣ የወተት፣ የእንቁላል፣ የማር ምርት እና ሌሎችንም ተያያዥ ምርቶች ወደ ገበያ በማቅረብ በኩል የተሻሉ አፈጻጸም መመዝገቡን አመላክተዋል።
ለገጠር ኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚውል መሬት ልየታና አቅርቦት ሥራዎችን በማከናወን በበጀት ዓመቱ 11 ሺህ 881 በላይ ሄክታር መሬት የመለየት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። የ801 ባለሃብቶች የልማት አፈፃፀም በመገምገም 62 ነጥብ 8 በመቶ ለሚኾኑት ባለሃብቶች የልማት አፈጻጸም ፕሮፋይል መሞላቱንም ተናግረዋል።
ዶክተር ይልቃል ዘመናዊ፣ ፍትሐዊና በውድድር ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥርዓትን በማጠናከር በንግድና ገበያ ሥርዓት ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ የንግድ ማኅበረሰብ እና ሸማችን የመፍጠር ሥራ በእቅድ ተይዞ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
የንግዱ ማኅበረሰብ ወደ ንግድ መረቡ በስፋት እንዲቀላቀል በተደረገው ጥረት በቢሮዉ በኩል አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ለ432 ሺህ135 ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ እድሳት ለመስጠት ታቅዶ ለ342 ሺህ 461 ነጋዴዎች የንግድ ፍቃድ ማደስ እንደተቻለ ርእሰ መሥተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርት አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/