“የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦችን አብሮነት ማንም አይበጥሰውም” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

206

ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሪዎች በጋራ ችግኝ ተክለዋል።
በመርኃግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ‟ግድያና ትርምስ የነበረበት አካባቢ ወደ ሰላም ተመልሶ በጋራ የአብሮነት እና የፍቅር ችግኝ በመትከላችን ተደስቻለሁ” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከነበሩባት ችግሮች አንዱ የመተከል አካባቢ እንደነበርም አስታውሰዋል። በአካባቢው የነበረው ችግር ጽንፈኝነትና ጥላቻ የወለደው እንደነበር ተናግረዋል። በጥላቻ የተነሳው ግጭት ዜጎችን ለሞትና ለመፈናቀል ዳርጎ እንደነበርም ገልጸዋል። የፀጥታ ኃይሉም ከሕዝቡ ጋር ባደረገው ትግል አካባቢው ወደ ሰላም ተመልሷል ብለዋል።

የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እጣፋንታ መለያየት አይደለም፤ አብሮነቱን ማንም ሊበጥሰው አይችልም፤ ችግር ሲፈጠር በጋራ እየፈታን አብሮነትን ማስቀጠል አለብንም ነው ያሉት። ክልሎች በጋራ በሠሩት ሥራ ሰላም መምጣቱንም ገልጸዋል።
ጥላቻን እየነቀልን ፍቅርን እየተከልን እንቀጥላለን ፤ በጋራም እንሠራለን ነው ያሉት። አካባቢው የልማትና የቱሪዝም አካባቢ ኾኖ ይቀጥላል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህ የሚኾነው ጥላቻን እየነቀልን ፍቅርን ስንተክል ነው ብለዋል።
የተተከለው ችግኝ የፍቅርና የአብሮነት ማስታወሻ ኾኖ እንዲኖር እንክብካቤ ያስፈልገዋል ነው ያሉት። ወደፊት ችግር ቢፈጠር እንኳን በሀገር ባሕልና በሕግ አግባብ መፍታት ይገባል ነው ያሉት። ኹለቱ ክልሎች ለሰላም ሠርተው በጋራ ወደ ልማት መግባታቸው ለሌሎች አርዓያ እንደሚኾንም ተናግረዋል።
ክልሎች በጋራ መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። የያዝነውን ሰላም በአግባቡ መያዝ ይገባናልም ነው ያሉት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሐሰን ‟ለሰላም ያበቁን ኹሉ ምሥጋና ይገባቸዋል” ብለዋል።
የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብ በታሪክም ኾነ በአኹናዊ ሁኔታ አንድ የኾነ ሕዝብ እንደኾነ አስረድተዋል። የሕዝቦች ትስስር ታሪካዊና ነገም የሚቀጥል ነው ብለዋል።
ጠላቶች ሀገርን ለማፍረስና የሕዳሴ ግድቡን ሥራ ለማስተጓጐል በፈጸሙት ጥፋት በዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል። ዛሬ ጥላቻን ነቅለን የሰላም የአብሮነት ችግኝ ተክለናል ብለዋል። ❝በአብሮነት ከሠራን ችግር ቢከሰት እንኳን መፍታት እንችላለን❞ ነው ያሉት።
ጽንፈኞች በሀገር ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት መመከት የሚቻለው በአንድነት ነውም ብለዋል። ❝ከዚህ በኋላ ስንገናኝ ማውራት ያለብን ስለ ልማት መኾን አለበት❞ ነው ያሉት። አካባቢው ወደ ሰላም እንዲመለስ ከፍተኛ መስዋእትነት ለከፈሉ የፀጥታ ኀይሎች ምሥጋና ይገባቸዋልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ለሰላም እያደረገው ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑንም አንስተዋል።
ችግኞቹን በጋራ ለመንከባከብም የአካባቢው መሪዎች ተስማምተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኩር ጋዜጣ – ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleʺድል ለእርሷ ተሰጥቷል፣አሸናፊነት ከእርሷ ጋር ተሰርቷል”