“ከኅሊና ጓዳ ተስጦ የሚኖር፣ ሀገርም ጥላ ነው ቅር ቢሉት የማይቀር”

247

ሐምሌ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከጥላህ ተለይተህ መሄድ ከቻልክ፣ ሀገር አልባ ኾነህ መኖር ትችላለህ፣ ጥላህን ቅር ብለህ ከጉዞ ካስቀረህ ሀገርን ጥለህ ብቻህን መኖር ትችላለህ፣ ነገር ግን ጥላህ ወይ በቀኝ፣ ወይ በግራህ፣ ወይ በፊት ወይ በኋላህ ከአንተ ጋር አይለይም፡፡ በጨለማ ሰዓት ከአንተ የተለየህ ቢመስልህም በምታርፈበት ኹሉ አብሮህ ያርፋል፣ በተነሳህም ጊዜ አብሮ ይነሳል፤ በተጓዝክም ጊዜ አብሮ ይጓዛል፡፡ በጨለመ ሰዓት ተለየሁት ያልከው በብርሃን እንዳልተለየህ ያሳይሃል፡፡ በብርሃንም በጨለማም አብሮህ ይኖራል እንጂ፡፡

ስታርፍ ያርፋል፣ ስትጓዝ ይጓዛል፡፡ ጥላህን አታስፈልገኝም ብለህ እንደማታስቀረው፣ እንደማትለየው ኹሉ ሀገርህን አታስፈልጊኝም ማለት አይቻልም፣ ሀገር የማታስፈልግ ቢኾን ሺዎች አንገታቸውን ለሰይፍ አሳልፈው ባልሰጡ ነበር፣ ሀገር ባታስፈልግ ኖሮ ሺዎች በጦር ባልተወጉ ነበር፣ ሀገር ባታስፈልግ ኖሮ ደም ባልፈሰሰላት፣ አጥንት ባልተከሰከሰላት፣ ሕይዎት ባልተገበረላት፣ ረሃብና ጥሙ ባልተቻለላት፣ ሞት ባልተናቀላት ነበር፡፡
የሀገር ውሉ የገባቸው ደም እንደ ውኃ ቀድተዋል፣ የሀገር ፍቅሩ የዘለቃቸው አጥንት እንደ ሸክላ ከስክሰዋል፣ የሀገር ክብር የሚገባቸው በሞት ላይ ተረማምደዋል፡፡ እነርሱ ሞተው ጽኑ ሀገር አቆይተዋል፡፡ ሀገር ሲደሰቱ የሚጫወቱባት፣ ሲጣሉ ጨዋታ ፈረሰ የሚባባሉባት አይደለችም፡፡ ሀገር ከጠብም ከፍቅርም በላይ ናት፡፡ በተደሰቱ ጊዜ የሚያፈቅሯት፣ የሚስሟት፣ ደግነቷን የሚናገሩላት፣ በተከፉ ጊዜ የሚነክሷት፣ ብትፈርስ፣ ብትገረሰስ እንጃልሽ የሚሏት አይደለችም፡፡ ሀገር በክፉውም በደጉም ዘመን አክብረው የሚይዟት ከፍ አድርገው የሚያኖሯት ናት፡፡

የአበው ደም ያስፈራኛል፣ የጀግኖች አጥንት ያስደነግጠኛል፣ ያስረከብናችሁን ሀገር ጠበቃችኋት? ወይስ አደራዋን በልታችሁ መከራዋን አበዛችሁባት? ቢሉ መልስ ይቸግረናል፡፡
ዛሬ ላይ የእነርሱን ክብርና ዝና ትተው የቀደሙት ቀድመው ሞተው አፀኗት፣ ያለፉት ከጠላት ጋር ተዋግተው አቆሟት፣ ፍቅርና ክብር የሚያውቁት በደም ማኅተም አተሟት፣ የአኹኖቹ እርስ በርስ እየተገዳደሉ አስጨነቋት፤ ስቃይዋን አበዙባት፣ መከራዋን አጸኑባት፡፡ በአንደኛው ልጇ የሚገደለውን ሌላኛውን ልጇን በመቅበር አሰለቿት፡፡ ድንኳኑ ለቀናት ሳይኾን ለዓመታት ከማይነሳ ለቅሶ ላይ አስቀመጧት፡፡

ትምህርት አልነበረበትም፣ ዘመናዊነት አልተስፋፋበትም በተባለበት፣ የጨለማ ዘመን ነበር በሚባልበት የነበሩት ብልኾቹ ኢትዮጵያውያን እምዬ ሀገራቸውን ወደ ብርሃን መሯት፣ ወደ ድል ማማ ከፍ አደረጓት፡፡ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው አስከበሯት፤ የአሸናፊነት ምልክት፣ የድል አድራጊነት ተምሳሌት አደረጓት፡፡ እነርሱ የጨለማ ዘመን ፋኑስ፣ የማዕበል መሻገሪያ ባሕር ከፋይ ዘንግ ነበሩና ተከብረው አስከበሯት፡፡ ተሻግረው አሻገሯት፣ ከፍ ብለው ከፍ አደረጓት፡፡
የቀደመው ዘመን ጨለማ ነው ሲሉ ኢትዮጵያውያን ግን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ብቻ ሳይኾን በጥቁር ምድር በሙሉ ብርሃን ያበሩ ነበር፤ የተቸገረውን ያሻገሩ፣ መድረሻ የጠፋበትን ያሳደሩ፣ መንገድ ለጠፋበት ከጥበባቸው ብርሃን ያበሩ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በጨለማ ዘመን ብርሃን አብርተው ካሻገሯት የተቀበሉት፣ በብርሃን ዘመን ጨለማ ጠርተው መንገዷን አጠፉባት፣ ልጆቿን አፋጁባት፣ በማሳዋ ላይ ፍቅርን አጭደው ክፋትን ዘሩባት፡፡

ስለ ኢትዮጵያ አብዝተው የሚጨነቁትና መልካም ነገር ኹሉ በኢትዮጵያ እንዲኾን የሚተጉት ፕሮፌሰር አዱኛ ወርቁ የኢትዮጵያውያንን አኹናዊ ሁኔታ የሚገልጽ አንድ የግጥም ቋጠሮ አላቸው፡፡ በእርግጥ የእሳቸው ሥራዎች ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል ነው፡፡ አንደኛው ግጥማቸው ግን በአንደበታቸው ሲሉት ያስጨንቃል፡፡ ከግጥሞቹ መካከል የተወሰኑ ስንኞች ደግሞ የበለጠ ያስጨንቃሉ፡፡
“ቢሮጥ ቢንደረደር አኩርፎ ተጣልቶ፣
በዓደባባይ ውሎ በጫካ ሸፍቶ፣
እንዴት ይዘልቀዋል ሰው ከጥላው ሸሽቶ፣
የተወሳሰበ ከኅልውና ጋር፣
ከኅሊና ጓዳ ተስጦ የሚኖር፣
ሀገርም ጥላ ነው ቅር ቢሉት የማይቀር፣
ወገንም ጥላ ነው ቅር ቢሉት የማይቀር።” የሚል የስንኝ ቋጠሮ አላቸው፡፡ ሀገርና ወገንን ይቅርብኝ ተብሎ የማይቀር መኾኑን ሲያመላክቱ፡፡ በሰው ሀገር ቢኖሩ የሀገር ትዝታ ይቀሰቅሳል፤ የወገን ናፍቆት ያላውሳል፡፡ አላስቆም አላስቀምጥ ይላል፡፡

ብዙዎች ሀገርና ወገን በዋዛ የሚቀር፣ ቢቀርም የማያጎድል ይመስላቸዋል፡፡ ለዚያም ነው በሀገራቸው ላይ እልፍ በደሎችን የሚያደርሱት፤ ሀገራቸውን ከበዓድ ጋር ተመሳጥረው የሚበጠብጡት፡፡ እነርሱ ከዛሬ ውጭ ነገ አይታያቸውም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የተከፈለው መስዋእትነት ዋጋው አይገባቸውም፡፡ የአበውን አደራ አያስታውሱም፣ የአበውን ቃል ኪዳን አይጠብቁም፡፡
ከፋም በጀም፣ መረረም ጣፈጠም ሀገር ሀገር ናት፡፡ ሀገር እትብት ናት፤ ሀገር እውነት ናት፣ ሀገር ማንነት፣ መሠረት፣ ሕይወት ናት፡፡ ሀገር አልባ ሲኾኑ እንኳን መኖሪያ መቀበሪያ ይጠፋል፤ መድረሻ ይታጣል፡፡ ሠርጉ የሚሞቀው፣ ለቅሶው ሥርዐት የሚኖረው ሀገርና ወገን ሲኖር ነው፡፡ ሀገር ከሌለ ሠርግም ቀብርም አያምርም፡፡

ልብ ይበሉ በየዱር ገደሉ ስንት ጀግኖች ለሀገር ነጻነት ሲሉ መስዋእት እንደኾኑ፡፡ ጀግኖቹ ሞትን ንቀው ሀገር አቆይተዋል፡፡ በመስዋእትነት የቆየች ሀገር በእንዝላልነት አደጋ እንዳይገጥማት መጠንቀቅ ግድ ይላል፡፡
በዓለም አደባባይ በአሸናፊነት የተውለበለበችው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ዛሬም ከፍ እንዳለች እንድትኖር በአንድነት፣ በጽናት፣ በትዕግሥትና በብልሃት መኖርን ያሻል፡፡
የኢትዮጵያውያን አንድነት ጠላቶችን ያስደነግጣቸዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን መከፋፈል ጠላቶችን ያስደስታቸዋል፡፡ ሀገርህን ከምንም በላይ አስበልጣት፣ ከምንም በፊት አስቀድማት፡፡
ኢትዮጵያ የሚያምርባት አንድነትና አሸናፊነት ብቻ ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የተከፈለውን መስዋእትነት አስተውል፤ ልብ በል፣ የአባቶችና የእናቶችን የደምና የአጥንት ቃል ኪዳንን አክብር፡፡ ከከፍታህ የሚያወርዱህን በአንድነት ታገላቸው፣ መከፋፋል የሚሰብኩህን አንድነትን ስበካቸው፡፡ ሀገርህ ከስሜትና ከጊዜያዊነት በላይ እንደኾነች አስብ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየትግራይ እናቶች ባለፈው የግማሽ ምዕተ ዓመት የጦርነት ታሪክ ውስጥ ያተረፉት ድህነት መኾኑን ተረድተው ለልጆቻቸው ሰላምን ሊሰብኩ እንደሚገባ ሃረገወይኒ አሰፋ (ፕ.ር) ተናገሩ፡፡
Next articleበወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ እየተመራ የሀገሩን ክብር የሚጠብቅ ሠራዊት መገንባቱን የማዕከላዊ ዕዝ ገለጸ።