
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከሀገር ውጭም ከሀገር ውስጥም የተሰባሰቡት የጨለማው ልዑላን በብሔር ስም የተደራጁ እና የታጠቁ የሽብር ቡድኖችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ለዘመናት መረጋጋት የተሳናት እና ደካማ ሀገር ሆና የማየት ከንቱ ምኞታቸውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉ አሜሪካዊው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን ገልጸዋል፡፡
ሎውረንስ ፍሪማን በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው እልቂት ኢትዮጵያ ውስጥ በዘር የተደራጁ ተልዕኮ ተቀባዮች፣ የውጭ ሀገር መንግሥታት እና ለመሰል ጥፋት ሆን ተብለው የተደራጁ ጽንፈኛ ኃይሎች የፈጸሙት ድርጊት ነው በማለት አጥብቆ ይከራከራሉ።
“ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በንጹሃን የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የጨለማው ልዑላን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ዘርን መሰረት አድርገው የታጠቁ የሽብር ቡድኖችን በመጠቀም የፈጸሙት ጭፍጨፋ ነው” ብለዋል የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ፡፡
እንደ ሎውረንስ ፍሪማን ገለጻ ከውስጥ እና ከውጭ ተናበው የሚሠሩት የጨለማው ልዑላን የተረጋጋች፣ ምጣኔ ሃብታዊ አቅም የፈጠረች እና ሉዓላዊነቷ የጸና ኢትዮጵያን ማየት አይፈልጉም፡፡
ኢትዮጵያን ለመበታተን እና ለማዳከም በተዘጋጀው ፕሮጀክት ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያ አውድ ውጭ እንዲተረጎም ተደርጓል ያሉት ተንታኙ በተሳሳተ ትርክት የተመሰረቱ እና የኢትዮጵያን መጽናት የማይሹ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲቋቋሙ አድርጓል ብለዋል፡፡
ሎውረንስ ፍሪማን ከሰሞኑ በወለጋ ከተፈጸመው የአማራ ብሔር ተወላጆች ጭፍጨፋ ጀርባም “የጨለማው ልዑላን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ዘርን መሰረት አድርገው የታጠቁ የሽብር ቡድኖችን እየተጠቀሙ ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በውጭ የፋይናንስ ምንጮች የሚደገፉት ታጣቂ ሚሊሻዎች ከሰሞኑ የፈጸሙት ክስተት ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ጋር እንደሚያያዝም ፍሪማን ጠቁመዋል፡፡ የውኃ ሙሌቱን ተቃዋሚዎች የተፋሰሱ የታችኞቹ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን ብቻ አይደሉም ያሉት ሎውረንስ ፍሪማን ምዕራባዊያን የሴራ እጆቻቸው እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት፣ በአፍሪካ ቀንድ ጨዋታ ቀያሪ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ ይህ እዲሆን የማይሹ ቡድኖች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ተከታታይ የእርስ በእርስ ግጭት ካለ ለውጭ ሀገር ተጽዕኖ እጅ የሚሰጥ ደካማ መንግሥት መፈጠሩ አይቀሬ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት እና አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያደነቁት ፍሪማን ከሽብርተኛው ትህንግ ባህሪ እና ስሪት አንጻር የድርድሩ ስኬታማነት እንደሚያጠራጥራቸው ገልጸዋል፡፡ ምዕራባዊያን መንግሥታት እና የብዙኃን መገናኛ ተቋሞቻቸው ኢትዮጵያን ለማዳከም ያደረጉት ዘመቻ አልሳካ ሲል የሽብር ቡድኖችን መደገፋቸውንም ተችተዋል፡፡
ችግሩን ለመቋቋም እና ለመፍታት መፍትሄው ራሳቸው ኢትዮጵያዊያን ናቸው ያሉት ተንታኙ መጀመሪያ አሉ በሚባሉ ልዩነቶች ላይ ሕዝባዊ ውይይት እና ምክክር ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ፍትሐዊ እና ተደራሽ ውይይት ለአሁናዊቷ ኢትዮጵያ ችግሮች ፍቱን መድሃኒት ነው፤ አንድነትን ማጽናት ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀው የኢትዮጵያዊነት ተልዕኮ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/