
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በ41ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሉሳካ ገብተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የአስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የአባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ነው።
የዘንድሮ 41ኛ መደበኛ ስብሰባ የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ራሱን ችሎ በሚሰራበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ስልጣን ስለመስጠት ይመክራል።
በመደበኛ ስብሰባው የቀጣዩ ዓመት የህብረቱ በጀት የሚፀድቅ ሲሆን በቅርቡ ለተመሰረተው የአፍሪካ መድሃኒት ኤጀንሲ ዋና መቀመጫ አስተናጋጅ ሃገር የሚመረጥም ይሆናል።
በተጨማሪም የህብረቱ ተቋማዊ የማሻሻያ ስራዎች የደረሱበት ደረጃ በመገምገም አቅጣጫ ያሰቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ41ኛው የአስፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በተጨማሪ በሉሳካ የህብረቱ ቢሮ አባላት እና የክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ሊቃነ መናብርት የሚሳተፉበት ቅንጅታዊ ጉባኤም እንደሚካሄድም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።