
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) የ2019 ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን አስመልክቶ ቅዳሜ ጥቅምት 08 ቀን 2012ዓ.ም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የተሰናዳ የደስታ መግለጫ መርሀ ግብር ላይ ድንገት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዳሚ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ንግግር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ‹‹ይሄ ግጥምጥሞሽ ነው… ‹ዲያስፖራው ዝግጅት አለው› ስባል ሠላምታ ለማቅረብ ነው የመጣሁት›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚለዩበት አንድ መለያ በሠላም መኖር፣ የአገሪቱን ሕግ ማክበር፣ ሥራ መውደድ፣ እርስ በእርስ መግባባት፣ የተቸገረን መርዳት ሲሆን ሁል ጊዜም የምትመሠገኑበትን ይሄንን መልካም ስማችሁን እንድታቆዩ አደራ እላችኋለሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹ጅቡቲ ሁለተኛ ቤታችን ነው›› ያሉት ዶክተር ዐብይ ‹‹ጅቡቲያውያኑ እኛን ይወዳሉ፤ እኛም ደግሞ አብዝተን እነሱን እንወዳቸዋለን›› ብለዋል፡፡ መደመር በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ በግልጽ መታዬቱን ጠቅሰው ‹‹ይሄንን በሁለቱ አገራት መካከል ያለ ጥብቅ ወዳጅነት የምታጠናክሩ ድልድዮች ጀግና ኢትዮጵያውያን ስለሆናችሁ በታማኝነት፣ በጨዋነትና በፍቅር እዚህ ካለው ሕዝብ ጋር በመኖር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አምባሳደር እንዲሠራ አደራ›› ብለዋል፡፡
ስለ ኖቤል ሽልማቱ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የኖቤል ሽልማቱ በአንድ ሰው ስም መነገር ስላለበት እንጂ ሽልማቱ የሁላችሁም ነው›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰፋፊ ሥራዎች መጀመሩንና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላላቅ ምጣኔ ሀብት ከገነቡ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የኤርትራ ብልጽግና መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹በውስጣችንም በአጎራባች አገራትም ሠላም እንዲኖር እንሠራለን›› ብለዋል ዶክተር ዐብይ፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ‹‹ከተመረጥን እንሠራለን፤ ካልተመረጥን አቅፈን በማስረከብ አርዓያ የሆነ ሥራ እንሠራለን›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ተሸንፎ ስልጣንን በሥርዓት ማስረከብ ከኖቤል የሚበልጥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
‹‹ስደት እንዲያበቃ ለልጆቻችን የምትበጅ ኢትዮጵያን ሠርተን ማቆየት አለብን›› ብለዋል ዶክተር ዐብይ በንግግራቸው፡፡
በጅቡቲ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉስልጣን አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ መገኘት የተሰማቸውን ደስታና ክብር ገልጸው በጅቡቲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አምባሳደሩ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለዚህ ታላቅ ዓለም-አቀፋዊ ሽልማት በመብቃታቸው በጅቡቲ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል›› ብለዋል፡፡ ሽልማቱ መላው ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም-አቀፍ መድረኮች ላይ እየተጫወተች ያለውን ሚና የሚያጎላና ዕውቅናንም የሚሰጥ እንደሆነም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
በዝግጀቱ የተገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰማቸውን ደስታና ክብር ከፍ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ