
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አቤቱ ጠላቶቿን ፈጥነህ አስገዛላት፣ በምድሯ ሰላምን ሙላላት፣ ረሃብና ጥም፣ መከራና ብስቁልና እንዳይኖር እርዳት እያሉ ሳያቋርጡ ይማጸናሉ፡፡ ነብሳቸውን አጥግበው፣ ስጋቸውን አስርበው ጸሎትና ምሕላ ያቀርባሉ፡፡ እንቦሶች ጠብተው ይጥገቡ፣ ላሞች አይራቡ፣ በሬዎች አርሰው እሸት ይመግቡ እያሉ በጸሎት ይተጋሉ፡፡ ሰዎችን ሁሉ ፍቅርህና ምሕረትህ ይጎብኛቸው፣ መአትና መከራ አይምታቸው፣ ጥልና ክፉ መንፈስ አይቅረባቸው፣ ኃይልህ ይጠብቃቸው እያሉ ይማጸናሉ፡፡
ሀገርን ከእነ ውበቱ፣ ሃይማኖትን ከእነ ስርዓቱ ለዘመናት ጠብቃለች፣ ተከብራ አስከብራለች፣ ጥበባትን ሳታቋርጥ አመንጭታለች፣ ብራና ፍቃ፣ ቀለም በጥብጣ ታሪክን መዝግባላች፣ እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፋለች፡፡ ምስጢራትን አመስጢራለች፣ አያሌ ምስጢራትን ጠብቃና አክብራ ይዛለች፡፡
ተመራማሪዎች የሚያስሱት፣ አስሰው ያልደረሱበት፣ በፈቃድ ካልሆነ በስተቀር በብልጠት ብቻ የማይደርሱበት፣ የማያገኙት፣ ስሆነው ፣ እየሆነ ስላለውና ስለሚሆነው የሚገልጡ አያሌ ጥበባትን አስቀምጣለች፡፡ ስለ ሀገር ፍቅር ታስተምራለች፣ መከበባርና አንድነት እንዲኖር ታዝዛለች፣ ክፉ ነገር ሁሉ ከምድር ርቆ መልካም ነገር በምድሯ እንዲሰፋ ሳታቋርጥ ትሰብካለች፡፡ ሰዎች ሁሉ ፈጣሪያቸውን እንዲፈሩ፣ ሕግጋትን እንዲያከብሩ፣ በአንድነት እንዲኖሩ በትጋት ታስተምራለች፡፡
ጥበብ በጠፋበት ዘመን የጥበብ ምንጭ ነበረች፣ እነሆ ዛሬም በጥበብ ምንጭነቷ ቀጥላለች፣ ነገር ትቀጥላላች፣ ከእርሷ የሚመነጨው ጥበብ አይቋጥምና፤ ዘመናዊ ትምህርት ከመታሰቡና ከመታለሙ አስቀድሞ እርሷ ትውልዱን አስተምራለች፣ ብርሃኗን እየገለጠች ለጨለማው ዓለም ብርሃን አሳይታለች፣ ከፊት ቀድማ መንገድ መርታለች የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፡፡
አውደ ምህረቶቿ ያለ ትመህርት ውለው ያደሩበት ቀን የለም፡፡ ሊቃውንቱ ያስተምራሉ፣ ጥበብን በተማሪዎቻቸው ላይ ያዘንባሉ፡፡
ኢትዮጵያ እንድትከበር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በረከትና ረድዔት እንዲኖር፣ ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ እንድትል አያሌ ተግባራትን ፈጽማለች፡፡ አሁንም እየፈጸመች ነው፣ ወደፊትም ትፈጽማለች፡፡ ለምድር የተሰጡ በረከቶችን ታቅፋ ይዛለች፡፡ በያዘቻቸው ድንቅ የሆኑ ሃብቶች የዓለምን ዓይኖች ስባለች፣ ከእርሷ ውጭ በሌላ በየትኛውም ሀገር የማይገኙ ሃብቶችን ይዛለችና ዓለማት ይፈልጓታል፣ በመብራት ያስሷታል፡፡
ለኢትዮጵያ ድንቅ ውበት፣ ጽኑ መሠረት ከመሆነም አልፋ የሃብት ምንጭም ናት፡፡ ጎብኚዎች በእርሷ ዙሪያ የሚገኙትን ለማየት ይመጣሉ፣ ሃብት ፈሰስ አድርገው ይመለሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጻሕፍትን ከመጻፍ፣ ጥበባትን ከማፍለቅ፣ ሊቃውንትን ከማፍራት ያለፈ ታላቅ ነገርም ስለ ሀገር ስታደርግ ኖራለች፡፡ የተራቆተ ምድር እንዳይኖር በትጋት ስትሠራ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ ገዳማቷና አድባራቷ በአረንጓዴ ካባ እንዲዋቡ፣ የደከመው እንዲያርፍባቸው፣ ተስፋ ያጣው ተስፋ እንዲሰንቅባቸው፣ እንኳን የሰው ልጅ አራዊትና አዕዋፋት እንዲጠለሉባቸው የሚያደርጉ እጽዋትን እየተከለች ታሳድጋለች፡፡
ቤተክርስቲያኗ ለደን ልማት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች፡፡ ቁጥራቸው የበዙ የእጽዋት ዓይነቶችን ተንከበባክባ አኑራለች፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የምትኮራባቸው፣ ተማራማሪዎች የሚያስሷቸው የእጽዋት ዝርያዎች አብዛኛዎቹ የኖሩትና እዚህ ዘመን የደረሱት በእርሷ ብርታት ነው፡፡
ገዳማቱንና አድባራቱን በአረንጓዴ እጽዋት ታስውባቸዋለች፣ ሊቃውንቱ በዛፎቹ ግርጌ ቆመው ጸሎትና ምሕላ ያለማቋረጥ ያደርሳሉ፣ መናንያን መነኮሳት ጥቅጥቅ ባለው ጫካ ውስጥ ጎጆ ቀልሰው ያለሟቋረጥ ይማጸናሉ፣ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ፍቅርና ተድላ ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ፡፡ ምዕምናኑ በአማረው ቅጽር ግቢ ውስጥ ተሰባስበው መልካም ነገር ይሆን ዘንድ ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ አዕዋፋት በዛፎቹ ላይ ሰፍረው ሕብረ ዝማሬያቸውን ያሰማሉ፤ ልዩ ዝማሬ እየሰጡ ቀልብን ይስባሉ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንደ ዛሬው አዋጅ ባልተነገረበት፣ ሹማምንቱ ለችግኝ ተከላ ወደ ማሳ ባልወረዱበት፣ ችግኝ መትከል ዘመቻ ተብሎ ባልታወጀበት በቀደመው ዘመን ጀምሮ ሳታቋርጥ ችግኝ ተክላለች፣ የገዳማቱንና አድባራቱን ዙሪያ ገባ አስውባለች፣ ግርማ ሞገስ አልብሳለች፣ ጠብቃ አኑራለች፣ እድሜ ጠገብ እጽዋትን እንካችሁ ብላለች፡፡
ከተከለቻቸው ችግኞች ቀለም እየበጠበጠች፣ ብዕር እየቀረጸች ጥበባትን መዝግባለች፣ ታሪክ አስፍራለች፣ የእውቀት ምንጭ ኾና ኖራለች፡፡ በተከለቻቸው ችግኞች ለሀገር ውበት ኾናለች፣ የደከመውን አሳርፋለች፣ ምድረ በዳ የነበረውን ምድረ ገነት አድርጋለች፣ ሊጠፋ የነበረውን እጽዋት ዘር አቆይታለች፣ የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ሚናዋን ተወጥታለች፡፡ አስከብራ ተከብራለች፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባታል፡፡
አካባቢን ማስዋብ፣ ችግኝ በትከል ለእርሷ መገለጫዋ ነው፡፡ የገዳማቱና የአድባራቱ ዙሪያ ገብ እንዲራቆት፣ ራቁት ኾኖ እንዲቀመጥ አይፈቀድም፡፡ ይልቁንስ በአረንጓዴ ካባ እንዲዋቡ ይፈለጋል እንጂ፡፡ ደብር ሲደበር ችግኝም አብሮ ይተከላልና፡፡ ችግኝ መትከል የክብር መገለጫ ነው፡፡ ችግኝ መትከል ውበት ነው፡፡ ችግኝ መትከል ጥበብን መትከል ነው፡፡ ችግኝ መትከል መልካ ምዕድርን ማሳመር ነው፡፡ ችግኝ መትከል ምድርን ማስዋብ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ገዳማቶቿንና አብያተ ክርስቲያኖቿን ልብ ብላችሁ ተመልከቷቸው በእድሜ ጠገብ እጽፈዋት የተዋቡ ናቸው፡፡ ጎብኚዎችን ከሚስቡት አንደኛው በአብያተ ክርስቲያናቱና ገዳመቱ ዙሪያ ያለው ያማረ ውበት ነው፡፡ ለዘመናት በዘለቀው የችግኝ መትከል ጥበቧ አፈርን ጠብቃ አኖራለች፣ መሬት እንዳትሸረሸር አድርጋለች፡፡
በችግኝ መትከሏ ምክንያት ውበት ሰጥታለች፣ ሊጠፉ የነበሩ የእጽዋት ዝርያዎችን አቆይታለች፣ የመሬት መሸርሸርን ተከላክላለች፣ ምድረ በዳ የነበረውን ምድር አስውባለች፣ ንጹሕ አየር እንዲመጣ አድርጋለች፡፡ ችግኝ በመትከል ብዙ ነገርንም ፈጽማለች፡፡
ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን ማስዋብ፣ ራስን ማስዋብ ነው፣ ችግኝ መትከል የገበሬው ማሳ እንዳይሸረሸር መጠበቅ ነው፡፡ አንድ ችግኝ መትከል ውበትን፣ ጥበብን፣ ተስፋን እና እውቀትን መትከል ነው፡፡ ዙሪያ ገባዎችን በአረንጓዴ ካባ እናስውባቸው፡፡ ችግኝ ስንተልክ እንደ ቤተክርስቲያን ሁሉ ኢትዮጵያን እናስጌጣታለን፣ ውበቷን እንጠብቅላታለን፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/