
ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ከክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እና ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይም ነዋሪዎቹ በርከት ያሉ ሀሳቦችን አንስተዋል።
ነዋሪዎቹ የሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ቀዳሚው ሲሆን “የተደቀነብንን የደኅንነት ስጋት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ሊፈታልን ይገባል” ብለዋል። የአማራ ሕዝብ በየቦታው ለምን ይሳደዳል? ይሄ መቆም ያለበት ጉዳይ ነው ሲሉም ጠይቀዋል።
የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መጓተትና የፕሮጀክቶች መዘግየት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል።
በዞኑና በከተማ አሥተዳደሩ የሚታየው የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ሊፈታ እንደሚገባው እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ዞን ከ100 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ጥያቄ አንስተዋል።
እንደ ሀገር እየተስተዋለ የሚገኘው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ችግር እልባት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን ለማስቆም ከክልሎች ጋር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
“ጠላቶቻችን ፍላጎታቸው በሚቀዱልን ቦይ ብቻ እንድንሄድ ነው፤ እኛ ግን ከዚህ አዙሪት ወጥተን የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንሠራለን፤ እየሠራንም ነው” ብለዋል።
ተፈናቃይ ወገኖችን ከጊዜያዊ መጠለያ በዘለለ በዘላቂነት መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩበትን ምህዳር ለመፍጠር ጠንካራ ሥራ ይጠበቅብናል ሲሉም ገልጸዋል።
ዶክተር ይልቃል ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ምክንያት የሽብር ቡድኖቹ የኦነግ ሸኔና የትህነግ ሴራ መሆኑን የጋራ አቋም ልንይዝ ይገባናል ነው ያሉት።
በዞኑ እየተገነቡ ያሉና በቀጣይም የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በክልሉና በፌዴራል መንግሥቱ አቅም ልክ እንዲሠሩ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጠው ከዳር ተመልካችነት በመውጣት ሁሉም ያገባኛል በሚል መንፈስ መሥራት ሲቻል በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡-ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/