“ለበይክ፡ የባሪያህን የኢብራሒምን ጥሪ ሰምተን መጥተናልና”

171

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሒጅራ ዘመን አቆጣጠር ለ1443ኛ ጊዜ የሚከበረው ዒድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል የተለያዩና የተራራቁ የሚገናኙበት፣ አንዱ ለአንዱ የሚተሳሰብበትና የሚተዛዘኑበት፣ ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ሥልጣን፣ ሃብት ሳይለያቸው በአንድነት እና በእኩልነት የሚቆሙበት እንዲሁም የመስዋዕትነት በዓል በመባል ይታወቃል።
ይህ ታላቅ በዓል ሲነሳ ከአምስቱ የኢስላም መሰረቶች አንዱ የኾነውና የአረፋን በዓል ተከትሎ የሚከናወነው የሐጅ ሥርዓት ነው።
አንድ ሙስሊም በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ መካን ማየት (ሐጂ ማድረግ) ሐይማኖታዊ ግዴታው ነው። ነገር ግን ከአንድ ጊዜ በላይ የሚያደርጉት የሐጅ ጉዞ የሚወደድ (እንደ መልካም ሥራ) የሚቆጠር ይኾናል።
እናም በሐጅ ወቅት ሙስሊሞች ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት ወደ መካ ይጎርፋሉ። የቦታ ርቀት ሳይገድባቸው፣ ቋንቋና የዘር ሐረግ ሳይጋርዳቸው፣ ለአንድ ዓላማ፣ በአንድ ልብ፣ ከምዕራብ፣ ከምሥራቅ፣ ከሰሜን፣ ከደቡብ ይጠራራሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የተለያየ ፆታ፣ የተለያየ ቀለም፣ የተለያየ ዕድሜ፣ የኑሮ ደረጃ ሳይገድባቸው፣ የሀገር መሪውም ተመሪውም፣… ግን በአንድ ቦታ ይቆማሉ፤ አንድ ዓይነት ልብስ፣ አንድ ዓይነት ቃል (ለበይክ)፣ በአንድ ዓይነት ቋንቋ ሁሉም ፊታቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ አዙረው፣ አንድ ጌታን እያወሱ፣ ለሱ እያለቀሱ ሊዋደዱ፣ ችግሮቻቸውን በጋራ ሊያስወግዱ፣ ሊማማሩ፣ ሊመካከሩ፣ … በአንድ መስክ ይሰባሰባሉ።
ከሺህ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢብራሒም ላደረጉት ጥሪ ምላሽ ይሰጣሉ። እርሳቸው የገነቡትን ቤት ለመጎብኘት ይሄዳሉ። ” ለበይክ (አቤቱ ብለናል ጌታችን)” ይላሉ ሁሉም በአንድ ድምፅ። “የባሪያህን የኢብራሒምን ጥሪ ሰምተን መጥተናል” እንደ ማለት ነው።
ምዕመኑ ይህን አምልኮ ሲፈጽም በንጹህ ማሰብ፣ መፈለግ፣ የተለመደ አለባበስንና አኗኗርን ትቶ ሐጂ የማድረጊያ ልብስ (የኢህራም ልብስ) ለቀናት ለብሶ ይቆያል::
በሂጅራ አቆጣጠር ዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን ሁሉም ሐጃጆች አረፋ ላይ ይገናኛሉ። ይህ ክንውን የሐጅ ሥራዎች አስኳል በመኾኑ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ.) “ሐጅ ማለት አረፋ ነው።” እስከ ማለት ደርሰዋል።
ሐጃጆች ከሐጅ የሚያገኟቸው መንፈሳዊም ዓለማዊም ጥቅሞች በርካታ ናቸው። አላህን የማምለክ ስልጠና፣ እርስ በእርስ የመፋቀር፣ ትዕግስትንና ትጋትን፣ ሩህሩህና አዛኝ መኾንን፣ ከራስ ይልቅ ለወንድም ማሰብ፣ በምላሹ ምንም ነገር ሳይጠብቅ ገንዘቡን በአላህ መንገድ ማውጣትን፣ አላህ የወደደውን ሁሉ መውደድን፣ እርሱ የጠላውን መጥላትን በአጠቃላይ መልካም ሥነ ምግባራትን ይማራሉ::
የሐጅ ሌላኛው ጥቅም ደግሞ የንግድ ሰዎች በገፍ ገበያ ያገኙበታል። በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛር ይዘጋጃል። ይህን ትርዒት ሚሊዮኖች ይጎበኙታል፤ ይታደሙታልም።
ኢትዮጵያ ለኢስላም ብዙ አበርክቶ ያላት ሀገር ናት፡፡ በመኾኑም ለሐጂ ሥርዓት የምትጓዙ ኢትዮጵያዊያን ሐጃጆች ከሌላው ዓለም ለሚመጡ ሐጃጆች የነጃሺ መስጂድን፣ የቢላልን ትውልድ ቦታ፣ የእሙ አይመንን ሀገር ኢትዮጵያን መጥተው እንዲጐበኟት ጥሪ ለማድረግ እና ለማስተዋወቅ አጋጣሚም ነው፡፡
በእመቤት አሕመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleጀማራት ተብሎ የሚጠራው የመጀመርያው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ወይም የመስዋዕትነት በዓል በመላው ዓለም እየተከበረ ነው፡፡
Next article“ኢትዮጵያ የገጠሟት ፈተናዎችን ለመሻገር የጠነከረ የሕዝብ አንድነት እና መተባባር ያስፈልጋል” በሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት