“ሙስሊሙም ኾነ ክርስቲያኑ ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበር፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት ሳይሸረሸር ሊያስቀጥል ይገባል” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

127

ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የኢድ አልአደሃ (አረፋ) በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሰዒድ ሙሐመድ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለኢድ አልአደሃ (አረፋ) በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ የሐጅ ሥነ-ሥርዓት ከሃይማኖቱ ዋና ምሰሶዎች አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የገንዘብ አቅም ያለው ኹሉ በእድሜው አንድ ጊዜ ወደ መካ (ሳዑዲ አረቢያ) በመሄድ ሐጅ በማድረግ ግዴታውን መወጣት አለበት። የሐጅ ሥርዓትም ከዙልሂጃ 8ኛው ቀን ጀምሮ እስከ 10ኛው ቀን ይከናወናል ነው ያሉት።
9ኛው ቀን የአረፋ ቀን ሲኾን ሐጃጆች በአረፋ ተራራ ላይ በመውጣት ቀኑን በዱዓ ያሳልፉታል፤ በ10ኛው ቀን ደግሞ ጀመራት ላይ ጠጠር በመወርወር እና የእርድ ሥርዓት በመፈጸም ለድኾች በማብላት ቀኑን አክብረው እንደሚውሉ ሸህ ሰዒድ አስረድተዋል፡፡
ሐጅ ከሚፈጽሙት ውጭ ያሉ ሙስሊሞች 9ኛውን ቀን ጾም በመጾም፣ ዱዓ በማድረግ እንዲሁም 10ኛውን ቀን የዒድ ሶላት እና የእርድ ሥርዓት በመፈጸም ለተቸገሩት በማብላት ቤተሰባቸውን በማስደሰት እንደሚያከብሩትም ገልጸዋል፡፡
የአረፋ በዓል መነሻ መሠረቱ ከነብዩ አደም (ዐ.ሰ) ጋር የተገናኘ እንደኾነ ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ በዓሉ ከመላው ዓለም የሚሰባሰቡ ሐጃጆች ብሔር፣ ዘር፣ ጾታ፣ ቀለም፣ አህጉር፣ ሀገር ሳይገድባቸው እና ሳይለያቸው አንድ አይነት የኢህራም ልብስ በመልበስ አረፋ በተባለ ልዩ ቦታ በአንድ ቦታ ቁመው ዱዓ በማድረግ ኹሉም የነብዩ አደም ልጆች መኾናችውን የሚያስመሰክሩበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡
“ለበዓሉ የታረደ እርድ አንድ ሦስተኛ ለድኾች አንድ ሦስተኛ ለቤተ ዘመድ እና ለጎረቤት አንድ ሦስተኛ ለቤተሰቡ እንዲመገቡት ይደረጋል፡፡ በዒድ ዕለት የምንፈጽማቸው በጎ ተግባራት ኹሉ ከአላህ ዘንድ አጅር እንድናገኝበት የተቸገሩትንና የተራቡትን በመርዳት በዓሉን ከኛ ጋር እኩል ተደስተው እንዲውሉ በማድረግ በዱዓ ልናሳልፈው ይገባል” ብለዋል፡፡
ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖችን በማስታወስ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ከመደገፍ ባሻገር ወደ ቀድሞው ሕይወታቸውና ቀያቸው እንዲመለሱ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ በመሳተፍ የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ለተከታታይ ዓመታት መፍትሔ ሳያገኝ ዘርን መሠረት ያደረገ የዜጎች ጭፍጨፋ እና መፈናቀል አሁንም የዕለት ተዕለት ችግር ኾኖ በመቀጠሉ ልባችን በሐዘን ተሰብሮ የምናከብረው በዓል ነዉ፡፡
መንግሥት ከኹሉም በፊት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
“ሙስሊሙም ኾነ ክርስቲያኑ በሀገሪቱ የሚታየውን የሰላም እጦት በኹሉም ዜጋ ላይ የተጋረጠ ችግር መኾኑን በመገንዘብ በሚሰጥ አጀንዳ ሳይወዛገብ ለዘመናት በዘለቀው የመከባበር እና የመረዳዳት የአብሮነት እሴታችንን ሳይሸረሸር ልናዘለቅ ይገባል” ነው ያሉት።
ሸህ ሰዒድ በሰጡት መግለጫ የተጋረጠውን ሀገራዊ የኅልውና አደጋ ለመከላከል በአንድነት፣ በጸሎትና በገንቢ አስተሳሰቦች ልንደጋገፍ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleሠራዊቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣና አስተማማኝ ሰላም በማሰፈን ሌት ከቀን ግዳጁን እየፈጸመ እንደሚገኝ በምዕራብ ዕዝ የሜካናይዝድ ሞተራይዝድ ብርጌድ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ንጋቱ አሰፋ ገለጹ።
Next articleጀማራት ተብሎ የሚጠራው የመጀመርያው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ወይም የመስዋዕትነት በዓል በመላው ዓለም እየተከበረ ነው፡፡