
ሽንቁሩን በኢትዮጵያ ባሕላዊ እሴቶች የሚሰፉ እጆች
እነዚህ እጆች መልካምነትን የሚጋግሩ አይደክሜ የበጎነት ብዕር ማረፊያ ናቸው፡፡ እነዚህ የብዕር እጆች በሚለበልበው ራስ ወዳድ የፖለቲካ ነበልባል ውስጥ ‹ጎራችሁን ለዩ› እየተባሉ የተለበለቡ ዝንጣፊ በረከቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እጆች ባልሰለጠነ ፖለቲካ ውስጥ ሁሉም ፖለቲከኛ በሆነባት ሀገር ውስጥ እሴቶቻችን፣ ቅርሶቻችን… እያሉ የባዘኑ የሰላም አርበኞችም ናቸው፡፡ እነዚህ እጆች ማኅበራዊ መገናኛ የትስስር ገፆችን ዘመኑን በዋጀ መንገድ በመጠቀም ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ አዕምሮን ከማወክ ይልቅ የሰላም እርሻን በብዕራቸው አለስልሰው መልካምነትን እና ዕውነትን የዘሩ ናቸው፡፡ አዎ! እነዚህ እጆች ባልኖሩበት ትናንት፣ ባላዩት ታሪክ፣ በተባለላቸው ተረክ፣ እሳት ከሚተፉ የጥፋት ስሜት ጋላቢዎች የሚወጣውን ኃይል ማርከሻ የተስፋ ፍኖት ናቸው፡፡
የማወራችሁ ስለ አንድ ለብዙዎች አዕምሮ ሰላም ስለሚታትር ኢትዮጵያዊ ሰው ነው፡፡ ወንጂ ነው የተወለደው፤ አብዛኛዎቹ ወንጂዎች በወንጂ ስኳር ፋብሪካ አማካኝነት ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅር ተሳስረው የተጋመዱ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ሁሉም ወንጂዎች ናቸው፤ እናም በወንጂዎች ጣት የሚቀሰርበት እሱ (እነሱ) የሚባሉ ወገኖች የሉም፡፡ በበርካታ ኢትዮጵያዊ መልካም እሴቶች የተወለዱ እና ያደጉ ኢትዮጵያውያን በፍቅር የሚኖሩባት አከባቢ ናት፤ ወንጂ፡፡ እንዲያውም የወንጂዎች ኢትዮጵያዊነት እንደ ስኳራቸው ለሁሉም የሚዳረስ በረከት መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ይህ አስተዳደጉ ሁሌም በኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴቶች እንዲማረክ እና ይህንንም እንዲያቀነቅን አድርጎታል፡፡
ባሕላዊ እሴቶችን ለጥላቻ መሳሪያነት የሚያውሉትን፣ ዝቅ ዝቅ የሚያደርጓቸውን ደግሞ በብዕሩ ይሞግታል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን የሥልጣኔ መገለጫዎች፣ ቅርሶች እና ባሕሎች በመልካም እሴቶች በማዘመን እና በመጠበቅ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ የገቢ ምንጭ ዘርፍ ሊያደርገው እንደሚያስፈልግ በማመን በማኅበራዊ ትስስር ገፆች የላቀ የአስተምህሮ ማዕድ ሆኗል፤ የዛሬ ባለታሪካችን አቶ ቁምነገር ተከተል፡፡ የራሱ እሴቶች ያልዘመኑለት ትውልድ፤ ልጓም የሌላቸው፣ ያልተገሩ ባሕላዊ እሴቶች፣ ተረኮች ለሰው ልጆች እኩልነት እና አንድነትን ዘብ መቆም አይችሉም ብሎ ያምናል፡፡ ትውልዱ ሩቅ ከማማተር እንዲያቆም ለዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴቶቸን እና ቅርሶችን መንከባከብ እና ማስተዋወቅ እንዲቻል በማኅበራዊ መገናኘ መረቦች ሰርቷል፡፡ አቶ ቁምነገር ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር አውሏል፤ ለአዕምሮ ሰላምና ለኢትዮጵያዊነት ከፍታም ሳይታክት ሰርቷል፡፡
አዳዲስ ሆቴሎች ሲገነቡ ኢትዮጵያዊ እሴቶች መልክ እንዲይዙ አድርጎል፤ ከመስተንግዶ እስከ ሆቴል ፋሽን ሾው ድረስ በሀገሪቱ እንዲለመድ ምክንያት ሆኗል፡፡ ባሕላዊ እሴቶች በህይወት ፍጥነት ልክ እየዘመኑ፣ ከማንነት መገለጫ አልፈው የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ የሚሠራው ቁምነገር ላበረከተው አስተዋፅኦ ሦስት ጊዜ በአፍሪካ መድረኮች ተመስግኗል፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 2017 ማይስ አይከን አፊሪካ አዋርድ፣ በ 2018 አፍሪካ ቱሪዝም ሌጀንድ እና በ 2019 የቱሪዝም ፐርሰናሊቲ አዋርድን አሸንፏል፡፡ እነዚህን ሁሉ ክብሮች የተቀዳጀው ቁምነገር በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ስለ ባሕል እና ስለ ቅርስ ጥበቃ ባከናወነው የማስተዋዎቅ ሚና ነው፡፡ ማኅበራዊ የትስስር ገፆች እነ ቁምነገርን ለመሳሰሉ ልበ ሙሉ ሰዎች የሀገር አንድነት ማስተሳሰሪያ ገመዶች ናቸው፡፡ ባሕላዊ እሴቶች ደግሞ የአንድ ማኅበረሰብ እሳቤ ውጤቶች ብቻ ሳይሆኑ ነገን መተንበያ እና መስሪያ ኃይል ናቸው፡፡ ቁምነገር የራሱን የማያውቅ ትውልድ የሌላው ያጓጓዋል ብሎ ያስባል፡፡ ባሕሉ ይዘቱን ሳይለቅ ማዘመን ለዚህ ፍቱን መድኃኒት ቢሆንም ይህን ዕውን ለማድረግ ብዙ ጥረት ይፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ በሥራዎቹ ውስጥ በርካታ ትችቶችን እና ውግዘቶችን ማስተናገዱንም ያስታውሳል፡፡ ነገን ከሚያሻግረው ሀቅ እና እሴት ይልቅ ባልተኖረ የታሪክ ሳንካ ወደ ኋላ መንሸራተትን ብቸኛ ምርጫ የሚያደርጉ ሰዎች ስለሌሎች ታሪክ እና ባሕል ማዳመጥ አለመፈለጋቸው እንደሚያሳዝነውም ነግሮናል፡፡
በጥላቻ ወደ ኋላ የሚንሸራተት ትውልድ ህልውናውን የሚጠራጠር፣ አዕምሮውም በደመነፍስ የሚዘወር ነው፤የተንሻፈፈ ተረክን ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደርግ ትውልድ የማንነት እና የእውነት ምርኮኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ባሕል በእጅጉ ያስተሳስረናል ብሎ የሚያምነው ቁምነገር ተከተል መጥፎ የሚባል ባሕል ባለመኖሩ ወደ ኋላ ከሚጎትቱን አስተምህሮዎች ይልቅ ወደ ፊት የሚያስፈነጥሩን ባሕሎቻችንን፣ ታሪኮቻችንን እና ቅርሶቻችንን በማዘመን ተጠቃሚ መሆንን መጀመር እንደሚያስፈልግ ያምናል፡፡ ለክፍለ ዘመናት ሳይዘምን የመጣውን የባሕል ክዋኔ ለዚህ ትውልድ በሚመጥን ልክ በመሥራት ለሌላ ትውልድ የተሻለች ዓለምን መፍጠር የሚችለው የዚህ ትውልድ መሠረት ነውም ይላል፡፡ ውጭ ሀገር ደርሶ በመጣ ቁጥር በውስጡ ያሉትን ባሕላዊ እሴቶችን የማዘመን እሳቤን በተግባር ለማየት በቁጭት የሚሰራው ቁምነገር የባሕል፣ የታሪክ እና የቅርስ ሀብቶች ከፉክክር ፖለቲካ መጠቀሚያ እሳቤነት እንዲወጡ ሰርቷል፡፡
ከፍ ባለ እሳቤ በዘመነ መንገድ እያንዳንዳቸውን ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ለማስተሳሰርም ተግቷል፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በሚያደርገው የማስተዋወቅ እና የማስተማር ሥራ ተከታዮቹ የሌሎችን ታሪክ፣ ባሕል፣ መስህቦችን ለማወቅ አለመፈለግ፣ የራስ ብቻ እንዲቀርብ መፈለግ፣ ለተቃርኖ አስተሳሰቦች መጠቀም እና የጥላቻ ትርክቶች ፈተና እንደሆኑበትም ተናግሯል፡፡ ፈተናዎቹ በሽታውን በሚገባ እንዳውቅ አድርገውኛል የሚለው ቁምነገር ፈዋሽ መድኃኒቱም ዕውነት እና ፍቅር ከጥላቻ እና ከየእኔ ይበልጣል ባይነት ከፍ ብለው እንዲታዩ ማድረግ እንደሆነ ያምናል፡፡ የ41 ዓመቱ ቁምነገር ተከተል ለዘጠኝ ዓመታት ያለመታከት ባከናወናቸው ተግባራት ማኅበራዊ የትስስር መረቦችን በመጠቀም መልካሙን የኢትዮጵያ ገጽታ እና የኢትዮጵያውያንን እሴቶች ለተከታዮቹ አበርክቷል፡፡ ከትጋቱ ውጤቶች መካከልም በኢትዮጵያውያን ትልልቅ ሆቴሎች ላይ ኢትዮጵያዊ ገጽታን አንጸባራቂ መለያዎች እንዲኖሩ ማድረጉ ይጠቀሳል፡፡ ባሕላዊ አሠራሮች፣ መስተንግዶዎች፣ ቁሳቁስ እና አልባሳት የኢትዮጵያውያንን ስነ ልቦና ተከትለው በመዘመን የገቢ ምንጭ መሆን እንዲችሉ አሻራውን እንዳሳረፈ ይነገራል፡፡
በዚህ ተግባሩ የተነሳ የ2012 ዓ.ም ሦስተኛው የጣና ሽልማት በባሕል እና ባሕላዊ እሴቶች አስተዋፅዖ ቁምነገር ተከተልን ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ ቁምነገርም “ይህ ሽልማት በሀገሬ በኢትዮጵያውያን እጅ የተሰጠኝ በመሆኑ በአፍሪካ መድረኮች ሦስት ጊዜ ከተሰጡኝ ሽልማቶች ሁሉ በእጅጉ ይልቃል” ብሏል፡፡ ወደፊትም የኢትዮጵያን ባሕል እና ቅርስ ጥበቃ ለአፍሪካውያን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ የአፍሪካውያንን ባሕልም ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የትስስር ገመድ የማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቁ ኤግዚቢሽኖችን ለማዘጋጀት እየሠራ እንደሆነም ከአብመድ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡ በሚዛናዊ አመለካከት የተገራ ትውልድ እንዲኖር ባሕላዊ እሴቶች መሠረት ናቸው፡፡
ያልሰለጠነ አዕምሯቸው የጋገረውን የጥፋት እንጀራ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚመግቡ እንዳሉ ሁሉ እነቁምነገርን አይነት ጥቂቶች ደግሞ የጥላቻ እና የመለያዬት አሜኬላውን ለመንቀል፣ ሽንቁሩን ለመድፈን ፣ አሮጊውን ለማደስ፣ ነገን ብሩህ ለማድረግ ዛሬም እየታገሉ ነው… እናንተስ ?
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ